በምያንማር ታጣቂዎች እጅ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን መካከል 41 ያህሉ ወደ ሀገራቸው መመለስ ጀመሩ

በምያንማር ከሚገኙ የሳይበር ወንጀል ካምፖች ወጥተው በሀገሪቱ ታጣቂዎች እጅ ካሉ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 41 ያህሉ ወደ ታይላንድ ተሻገሩ። አሁንም በታጣቂዎች እጅ ከሚገኙ ከ700 በላይ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 300 ያህሉ በሁለት ሳምንት ወደ ሀገራቸው ይመለሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ በታይላንድ የሚገኙ ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በደቡብ ምሥራቅ እስያዋ ምያንማር በሚገኙ የማጭበርበር ወንጀል ካምፖች ታግተው የነበሩ ኢትዮጵያውያን ከማዕከላቱ በመውጣት በታጣቂዎች እጅ የገቡት ባለፈው የካቲት 2017 ዓ.ም. ነበር።
"ዴሞክራቲክ ካረን ቤነቮለንት አርሚ" (DKBA) እና "ቦርደር ጋርድ ፎርስ" (BGF) በተባሉ ሁለት የተለያዩ ታጣቂዎች እጅ የሚገኙት ኢትዮጵያውያን፤ በተጠለሉባቸው ካምፖች ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ እያሳለፉ ነው።
ተጎጂዎቹ፤ የካቲት ላይ ከካምፖቹ ወጥተው በታጣቂዎች እጅ ከገቡት የአፍሪካ እና የተለያዩ ሀገራት ዜጎች ውስጥ ወደ ሀገራቸው መመለስ ያልቻሉት ኢትዮጵያውያን ብቻ መሆናቸውን በመጥቀስ ተማጽኗቸውን ሲያቀርቡ ነበር። ኢትዮጵያውያኑ ከምያንማር ወደ ሀገራቸው ለመመለስ በመጀመሪያ ጎረቤት ወደ ሆነችው ታይላንድ መሻገር አለባቸው።
በዚህም ምክንያት ተጎጂዎቹን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ተግባር የምያንማር፣ የታይላንድ እና የኢትዮጵያ መንግሥታትን ቅንጅት የሚጠይቅ ነው።
የሦስት ሀገራትን ትብብር የሚጠይቀው ይህ ተግባር በምያንማር በተፈጠረው የመሬት መንቀጠቀጥ ምክንያት መጓተቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው በታይላንድ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምንጮች ገልጸዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኢትዮጵያን በታይላንድ ያላትን የዲፕሎማቲክ ሥራዎች የሚሸፍነው እና በሕንድ ኒው ዴልሂ የሚገኘው ኤምባሲ "በቶሎ ተወካዮችን አለመላኩ" ተጎጂዎቹ በቶሎ ወደ ሀገራቸው እንዳይመለሱ እንቅፋት መሆኑን ምንጮቹ አስረድተዋል።
እንደ ምንጮቹ ገለጻ ኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች በቶሎ ወደ ታይላንድ ያልተጓዙት "ሁሉም ተጎጂዎች በአንድ ጊዜ በሚወጡበት ጊዜ የመምጣት ፍላጎት ስለነበራቸው" ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተጎጂዎች ወላጆች ኮሚቴ አስተባባሪ ወ/ሮ አበበች ሲመል ደግሞ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር በነበራቸው ንግግር "የበጀት እጥረት" ጉዳይ እንደተነሳላቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኒው ዴልሂ ከሚገኘው ኤምባሲ የተላኩ የኢትዮጵያ መንግሥት ተወካዮች ትናንት ሰኞ ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም. ታይላንድ በመድረሳቸው ተጎጂዎቹን ወደ ሀገራቸው የመመለስ ሥራ መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል።

በተያዘው እና በሚቀጥለው ሳምንት ውስጥ የሚመለሱት "አውሮፕላን ትኬት ያላቸው" ኢትዮጵያውያን ናቸው። "300 ገደማ ኢትዮጵያውያን ጊዜ ያለፈበት" ቢሆንም የመመለሻ ትኬት እንዳላቸው የሚናገሩት ምንጮቹ፤ ኢትዮጵያ አየር መንገድ በተጓዦቹ ላይ ይጣል የነበረውን ቅጣት ለማስቀረት መስማማቱን ጠቅሰዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ ተጎጂዎቹ ከምያንማር ተነስተው ወደ ታይላንድ በመሻገር ዋና ከተማዋ ባንኮክ ድረስ የሚጓዙበትን የአውቶብስ ወጪ እየሸፈነ መሆኑ ተገልጿል። ከምያንማር ወደ ታይላንድ ባንኮክ ከተማ ለሚደረግ የአንድ ሰው ጉዞ፤ 35 ሺህ ባት (የታይላንድ ገንዘብ) ወይም 1,100 ገደማ የአሜሪካ ዶላር ያስፈልጋል።
በዚህ አሠራር መሠረት የመጀመሪያዎቹ 41 ኢትዮጵያውያን ተጎጂዎች ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 28/2017 ዓ.ም. ከምያንማር ወደ ታይላንድ መሻገራቸውን ምንጮች እና የቤተሰቦች ኮሚቴ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
ሦስት ሴቶች እና 37 ወንዶችን የያዘው የመጀመሪያው ቡድን ወደ ታይላንድ ዋና ከተማ ባንኮክ እየተጓዘ እንደሚገኝ እና ዛሬ [ማክሰኞ] ምሽት ወደ ኢትዮጵያ እንደሚበርርም ምንጮች ተናግረዋል።
"80 ተጎጂዎችን" የሚይዘው ሁለተኛው ቡድን በመጪው ሐሙስ እንደሚበርር ተገልጿል። ትኬት ያላቸው ኢትዮጵያውያንን ወደ ሀገር ቤት የመመለስ ተግባር በሚቀጥለው ሳምንት ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅም አክለዋል።
ተጎጂዎቹን በመመለስ ላይ የተሰማሩት በታይላንድ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምንጮች እንደሚናገሩት፤ ትኬት የሌላቸው ቀሪዎቹ ከ400 በላይ ኢትዮጵያውያ የሚመለሱበት መንገድ እስካሁን ቁርጥ ያለ መፍትሔ አልተገኘለትም።
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተጎጂዎች ወላጆች ኮሚቴ አስተባባሪ ወ/ሮ አበበች፤ ትኬት የሌላቸው ኢትዮጵያውያን 80 በመቶ ወጪያቸው መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፤ ቀሪው 20 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሚሸፈን በመንግሥት እንደተነገራቸው ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው በታይላንድ የሚገኙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምንጮች ግን ይህንን አይስማሙበትም። መንግሥታዊ ያልሆኑት ድርጅቶች ለኢትዮጵያውያኑ ትኬት ለመግዛት አሁንም ድረስ ገንዘብ እያሰባሰቡ እንደሆነ ተናግረዋል።
አንድ ምንጭ፤ "አሁን ላይ 400 እና 500 ገደማ የሚሆኑ [ኢትዮጵያውያንን] ትኬት ወጪ ለመሸፈን የሚያስችል ገንዘብ የለንም። ገና እያሰባሰብን ነው" በማለት ለቢቢሲ ተናግረዋል። "ብዙ ትኬቶችን ቀጥታ ከአየር መንገዱ የምንገዛ ከሆነ 20 በመቶ ቅናሽ እንደሚያደርጉ ነግረውናል" ሲሉም ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ስለሚገኘው ቅናሽ አብራርተዋል።
ደላሎች ሥራ እናስቀጥራችኋላን በማለት በርካታ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ የሌሎች አገራት ዜጎችን በምያንማር ወደበሚገኙ የማጭበርበር ካምፖች በመውሰድ የወንጀል በበይነ መረብ አማካይነት ወንጀል እንዲፈጽሙ እንሚያደርጓቸው መዘገቡ ይታወሳል።
በተጨማሪም የወንጀል ቡድኖቹ ተጎጂዎቹ ላይ አካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶችን በመፈጸም እንሚያሰቃይዋቸው ቢቢሲ ከዚህ ቀደም ያናገራቸው ኢትዮጵያውያን አመልክተዋል።












