በቤኒሻንጉል ጉሙዝ በርበር ከተማ በሦስት ወር ልዩነት ሁለተኛ የመንግሥት ቢሮ በታጣቂዎች ተቃጠለ

መሳሪያ የያዙ ሶስት ታጣቂዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሦስት ወራት ገደማ በፊት የከተማ ማዘጋጃ ቢሮ በታጣቂዎች በተቃጠለባት የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሏ በርበር ከተማ በተፈጸመ አዲስ ጥቃት የቀበሌ ቢሮ መቃጠሉን ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ገለጹ።

የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት በከተማዋ ለተፈጸመው ጥቃት በአጎራባቹ ኦሮሚያ ክልል የሚንቀሳቀሰውን 'የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት' ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርገዋል።

ታጣቂዎች በመተከል ዞን የምትገኘው ድባጤ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው በርበር ላይ ጥቃት የፈጸሙት ባለፈው አርብ መስከረም 30/2018 ዓ.ም. ለቅዳሜ አጥቢያ ሌሊት 10 ሰዓት ገደማ እንደሆነ የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ መንግሥቱ ያዴሳ እና ሁለት ነዋሪዎች ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

አቶ መንግሥቱ እንደሚገልጹት የተቃጠለው መሥሪያ ቤት በውስጡ የበርበር ቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ እንዲሁም የፖሊስ አዛዥ ቢሮዎችን እንዲሁም የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት እና የማኅበራዊ ፍርድ ቤትን የያዘ ነው።

በግቢው ውስጥ የተያያዙ "ስድስት" ቤቶች እንደሚገኙ የሚገልጹት የማዘጋጃ ቤት ኃላፊው፤ በቅዳሜ አጥቢያው እሳት ጉዳት የደረሰበት "የቀበሌ ዋና አስተዳዳሪ ቢሮ" መሆኑን ገልጸዋል። እሳቱን የተመለከቱ ነዋሪዎች ደርሰው ሌሎች ቢሮዎችን ማትረፋቸውን ኃላፊው እና ነዋሪዎች ገልጸዋል።

"ወደ 40 ዓመት አገልግሎት የሰጠ ቢሮ ነው። በዚያ ውስጥ ያለው ንብረት፣ ዶሴ፣ ብዙ ወንበሮች፣ ብዙ ሼልፎች ነበሩ። ያ ሁሉ ወድሟል" የሚሉት አቶ መንግሥቱ፤ የደረሰው ጉዳት ቢሮውን "ከአገልግሎት ውጪ የሚያደርግ" መሆኑን አስረድተዋል። በቃጠሎው የቀበሌው ወሳኝ ኩነት መዛግብት ጭምር መውደማቸውን አክለዋል።

በአካባቢው የፌደራል ፖሊስ አባላት ካምፕ የነበረ ቢሆንም የፀጥታ ኃይሎች ከጥቃቱ በፊት መድረስ አለመቻላቸውን ኃላፊው እና ነዋሪዎች ተናግረዋል። አቶ መንግሥቱ፤"[የፀጥታ ኃይሎች] ጥቃቱ ከተከሰተ በኋላ ተደራጅተው ወደ ጫካ ሲሄዱ [ታጣቂዎቹ] ሸሽተው ሄደዋል" ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንድ የአካበቢው ነዋሪ ደግሞ ጥቃቱ ተፈጸመው "በሌሊት በመሆኑ የፌደራል ፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት አለመውጣታቸውን" ተናግረዋል። የድባጤ ወረዳ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ብርሃኑ እጀታ ቢሮው መቃጠሉን ቢያረጋግጡም ተጨማሪ መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።

የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ መንግሥቱ እና አንድ ነዋሪ ለደረሰው ጥቃት "ሸኔ" ሲሉ የሚጠሯቸውን የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት አባላት ተጠያቂ አድርገዋል።

የበርበር ከተማ "የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት" ታጣቂዎች ይህ ዓይነቱ ጥቃት ሲደርስባት ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ታጣቂዎች ባለፈው ዓመት ሰኔ ላይ ባደረሱት ጥቃት 11 ቢሮዎችን የያዘው የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት "ከባድ" ቃጠሎ እንደደረሰበት አቶ መንግሥቱ ገልጸዋል።

በዚህም የተነሳ እርሳቸው የሚመሩት መሥሪያ ቤት አገልግሎት አቋርጦ መቆየቱን እና መስከረም ላይ "የግለሰብ ቤት" በመከራየት "በከፊል" ሥራ መጀመሩን ገልጸዋል።

ማዘጋጃ ቤቱ ከተቃጠለ ከቀናት በኋላ በከተማዋ በተፈጸመ ሌላ ጥቃት ደግሞ "ብድርና ቁጠባ ተቋም"፣ "የግለሠብ ሞባይል ቤት እና ሱቆች" እንደተዘረፉ እንዲሁም ሰዎች እንደገደሉ የድባጤ ወረዳ አስተዳደር አስታውቆ ነበር።

የወረዳ አስተዳደሩ በወቅቱ ለደረሰው ጥቃት ተጠያቂ ያደረገው "ሸኔ" ሲል የጠራውን ታጣቂ ቡድንን ነበር።