ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአማራ ክልል ባለፉት ሳምንታት ግጭቱ መባባሱን ተከትሎ የሰብዓዊ ድጋፉን ማጠናከሩን ገለጸ

የሰብዓዊ አቅርቦት

የፎቶው ባለመብት, ICRC

የምስሉ መግለጫ, "ባለፉት ቀናት በሰሜን ወሎ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል አሊያም ቆስለዋል"።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአማራ ክልል በተለይም በሰሜን ወሎ ዞን ከመስከረም አጋማሽ ጀምሮ በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ኃይሎች መካከል ውጊያው መባባሱን ገልጿል።

የፋኖ ኃይሎች የተቀናጀ ዘመቻ መክፈታቸውን እና በዚህም ድል እየተቀናጁ መሆኑን ሲገልፁ፤ የአካባቢው አስተዳደር ግን ግጭቶች እንደነበሩ ጠቅሶ፤ ለቢቢሲ "በሚለወራው ልክ" አይደለም ብሏል።

በተለይም የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ከተማ የሆነችውን ወልዲያን ለመያዝ ለቀናት የዘለቀ ትንቅንቅ እንደነበር ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ባለፈው ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ለመንግሥታቱ ድርጅት በፃፈው ደብዳቤ ወልዲያን ለመያዝ በተደረገው ውጊያ የፋኖ ኃይሎችን በመደገፍ ህወሓትን ጨምሮ ኤርትራ መሳተፏልን በመጥቀስ ከስሷል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ ትናንት አርብ መስከረም 30/3018 ዓ. ም. አመሻሽ ላይ ያወጣው መግለጫ በአካባቢው የተካሄደውን ግጭት ጥልቀት እና የደረሰውን ጉዳት የሚጠቁም ነው።

ለአንድ ሳምንት ያህል የቀይ መስቀል ቡድን ግጭቱ በርትቶባቸው በነበሩ የሰሜን ወሎ ዞን ዋና ዋና ከተሞች እና አካባቢዎች ባደረገው ቅኝት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ምርኮኞች መያዛቸውን እና ከባድ የሰብዓዊ ጉዳት መድረሱን አስታውቋል።

ኮሚቴው በግጭቱ የተጎዱት ሰላማዊ ሰዎች ይሆኑ ተፋላሚ ወገኖች በግልፅ ለይቶ አልዘረዘረም።

በላሊበላ የኮሚቴውን ቡድን የሚመሩት ማርቲን ታልማን በግጭቱ "ክፉኛ" ከተጎዳው ኩልመስክ እና ሙጃ አካባቢ ሲመለሱ "ባለፉት ቀናት በሰሜን ወሎ በርካታ ሰዎች ተገድለዋል አሊያም ቆስለዋል" ብለዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"የጤና ጣቢያ ባልደረቦች ለቆሰሉ ወታደሮች እና ንፁሃን ሰዎች በተገደበ ግብዓት ያክማሉ።16 ከባድ ጉዳት የደረሰባቸው እስረኞች ቀዶ ሕክምና እንዲያገኙ በአስቸኳይ እንዲወጡ ተደርጓል፤ ከእነዚህም ውስጥ አምስቱ ሕይወታቸውን ለማዳን የሰዓታት ጉዳይ ነው" ሲሉ የጉዳቱን ክብደት ገልፀዋል።

በላሊበላ፣ ወልዲያ እና በአካባቢው ለስድስት የጤና ተቋማት የድንገተኛ ሕክምና እርዳታ መስጫ ቁሳቁስ ማቅቡን የገለፀው ኮሚቴው፤ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸው 250 ሰዎች የቀዶ ጥገና እና የሕክምና እርዳታ መስጠት የሚችል ድጋፍ ማቅረቡን ተናግሯል።

መስከረም 28/2016 ዓ.ም. አስቸኳይ የቀዶ ጥገና ሕክምና ያስፈልጋቸዋል የተባሉ 16 የከባድ ጉዳት ቁስለኞችንም ወደ ሕክምና ተቋማት ማድረሱን ገልጿል።

እነዚህ ቁስለኞች የመንግሥት ወታደሮች እንደሆኑ የጠቆመው ኮሚቴው፤ በፋኖ ኃይሎች "የተናጠል እርምጃ" ተላልፈው ከተሰጡት በኋላ በወልዲያ ለመንግሥት ኃይል ማድረሱን አስታውቋል።

በማግስቱ መስከረም 28፤ የቀይ መስቀል ባልደረቦች በሰሜን ወሎ በፋኖ ኃይሎች በቁጥጥር ስር የተያዙ "እስረኞችን" መጎብኘታቸውን ገልጿል።

የፋኖ ኃይሎች ከፈትነው ባሉት ዘመቻ በርካታ ወታሮችን መማረካቸውን በልሳኖቻቸው በኩል ሲያሳውቁ ሰንብተዋል።

ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በስድስት ልዑኮች በፋኖ ኃይሎች የተያዙ ወታደሮችን የአያያዝ ሁኔታ እና ሕክምና አቅርቦት ምልከታ ማድረጉን ጠቁሞ፤ ወታደሮቹ ከቤተሰቦቻቸው ጋር ግንኙነት ስለመፍጠራቸው ቅኝት ማድረጉን አስታውቋል።

ማርቲን ታልማን "በግጭቱ በጣም የተጎዱ ማኅበረሰቦች መዘንጋት የለባቸውም። ብዙ ሰዎች ወደ ጤና አገልግሎት፣ ወደ ገበያ እና ወደ እርሻ ቦታቸው መሄድ አልቻሉም" ብለዋል።

በአማራ ክልል ግጭት እየተሳተፉ ያሉ ተፋላሚ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግን ማክበር እንዳለባቸው ያሳሰበው ኮሚቴው፤ ይህም በግጭት እየተሳተፉ ያልሆኑ ምርኮኞች እና ቁስለኞች [ተዋጊዎች ይሁኑም ሰላማዊ ሰዎች] መጠበቅ አለባቸው ሲል አሳስቧል።