ኢሰመኮ በኢትዮጵያ በሚወሰዱ እርምጃዎች እና ጥቃቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት አደጋ ላይ ወድቋል አለ

እየተጓዘ ያለ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኢሰመኮ ከሚያዚያ 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ወራት ባካሄደው ምርመራ የመዘዋወር ነጻነት አደጋ ላይ ነው አለ

ኢሰመኮ በኢትዮጵያ በሚወሰዱ እርምጃዎች እና ጥቃቶች የሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት አደጋ ላይ ወድቋል አለ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በተለይም በአራት ክልሎች መንግሥት እና ታጣቂ ኃይሎች በሚወስዷቸው እርምጃዎች እና ጥቃቶች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነጻነት መብት አደጋ ላይ መውደቁን ተገንዝቢያለሁ ብሏል።

ኮሚሽኑ ይህን ያለው ከሚያዚያ 2017 ዓ.ም. እስከ መስከረም 2018 ዓ.ም. ድረስ ለስድስት ወራት አካሄድኩት ባለው የምርመራ ሪፖርቱ ነው።

በአማራ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በጋምቤላ እና በኦሮሚያ ክልሎች "አሳሳቢ" የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች አንዱ የሆነውን የሰዎችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነትን መመርመሩን ገልጿል።

ምርመራው የሰዓት እላፊ ገደቦች፣ በታጠቁ ኃይሎች እና በመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች የሚዘረጉ ኬላዎች፣ የመንገድ መዝጋት ትዕዛዞች እና እርምጃዎች እንዲሁም በመንገዶች ላይ በሚደርሱ ጥቃቶች፣ እገታዎች፣ የንብረት ዘረፋዎች እና ውድመቶች በነጻነት የመዘዋወር መብት አደጋ ላይ ከመጣል ባሻገር በሕይወት የመኖር፣ የአካል እና የንብረት ደኅንነት መብቶች ላይም ጥሰቶችን ማስከተላቸውን አረጋግጧል።

ከአሶሳ ከተማ በኦሮሚያ ክልል በኩል አድርጎ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው እና ከከማሽ ዞን ወደ ኦሮሚያ ክልል የሚወስደው መንገድ የኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) መዘጋቱን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ከአሶሳ ዞን ወደ መተከል ዞን የሚወስደውም መንገድ በእርቅ ወደ ሰላም ባልተመለሱ የጉሙዝ ታጣቂዎች የጥቃት ስጋት ምክንያት ዝግ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም የቤንሻንጉል ጉሙዝ ነዋሪዎች በነጻነት መንቀሳቀስ አለመመቻላቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ይህም በሕዝቡ ላይ ከፍተኛ እንግልት እያስከተለ ነው ብሏል።

በተሽከርካሪዎች እና በመንገደኞች ላይ የሚፈፀመውን እገታ የመረመረም ሲሆን፤ በኦሮሚያ ክልል በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች ላይ ከሚያዚያ እስከ ሐምሌ ባሉት ወራት የተፈፀሙ ሰባት እገታዎች ዘርዝሯል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች የዞን እና የወረዳ ባለሥልጣናትን ጨምሮ 69 ሰዎች መታገታቸውን የገለፀው ኢሰመኮ፤ እገታዎቹ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (በተለምዶ ኦነግ ሸኔ) እና በተለምዶ "ፋኖ" ተብሎ በሚጠራ ታጣቂ ቡድን እንደሚፈጸም አስታውቋል።

በሪፖርቱ በተዘረዘሩ ሰባት የእገታ ጥቃቶች ሰባት ሰዎች ወዲያው እና ለማምለጥ ሲሞክሩ በተከፈተባቸው ተኩስ ተገድለዋል ብሏል።

ማስለቀቂያ ገንዘብ እየከፈሉ አብዛኞቹ ታጋቾች ተለቀዋል።

ሪፖርቱ ተደጋጋሚ የተሽከርካሪ ላይ እገታ የሚፈፀምበትን እና ሚሊዮን ለማስለቀቂያ የሚጠየቅበትን ከአዲስ አበባ ጎጃም ባለው መስመር የተፈጸሙ እገታዎች ስለመኖራቸው አልጠቀሰም።

በአማራ ክልል ደግሞ በአብዛኛው በጎንደር ዞኖች ሦስት እገታዎችን የዘረዘረው ሪፖርቱ፤ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ 2017 ዓ.ም. ባሉት ወራት የተፈፀሙ ናቸው ብሏል።

በጥቃቱ 13 መንገደኞች መታገታቸውን የገለፀው ኢሰመኮ፤ እገታው በቅማንት ታጣቂዎች እና ማንነታቸው ባልታወቁ ታጣቂዎች መፈፀሙን ገልጿል።

ኢሰመኮ የጠቀሰው አንደኛው የእገታ ድርጊት ከወራት በፊት ቢቢሲ የዘገበው ሦስት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ሠራተኞች ጉዳይ ሲሆን፤ ከታጋቾች መካከል የሦስት ልጆች አባት የነበሩት አቶ ሆነልኝ ፋንታሁን በታጣቂዎች በደረሰባቸው ድብደባ እና በቅዝቃዜ ምክንያት ከእገታው በተለቀቁ በሰዓታት ውስጥ ሕይወታቸው አልፏል።

በክልሉ የፋኖ ታጣቂዎች ሦስት ነዳጅ የጫኑ ቦቴዎች ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን የገለፀው ሪፖርቱ፤ አንደኛው ተሽከርካሪ ነዳጁ ሲዘረፍ ሁለቱን ቦቴዎች ደግሞ ማቃጠላቸውን ጠቁሟል።

የተዘጉ መንገዶችንም ሁኔታ ያወጣው አዲሱ የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት፤ በአማራ ክልል ከመካነ ሰላም (ደቡብ ወሎ) ወደ መርጦ ለማርያም (ምሥራቅ ጎጃም) የሚወስደው መንገድ "ከጸጥታ ጋር በተያያዘ" በመንግሥት ከመጋቢት 2017 ዓ.ም. ጀምሮ (ለስምንት ወራት ያህል) መዘጋቱን ገልጿል።

በተመሳሳይ በክልሉ የአዴት-ሞጣ-ብቸና መንገድ ከሐምሌ ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ጀምሮ መዘጋቱን የገለፀ ሲሆን፤ የባሕር ዳር-ደብረ ማርቆስ መንገድ ከነሐሴ 1 እስከ ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአንድ ሳምንት ያህል በፋኖ ኃይሎች ተዘግቶ እንደነበር ጠቁሟል።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ, የኢትዮጵያ የመንገድ ደኅንነት እጦት እና ገበያው የደራው የአገር ውስጥ በረራ

ከግንቦት እስከ ሰኔ 2017 ዓ.ም. ባሉት ጊዜያት ከአማራ ክልል ለሥራ ጉዳይ ወደ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚጓዙ መንገደኞች መታወቂያቸው እየታየ "የአማራ ብሔር ተወላጆች" ተለይተው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ሲደረግ ነበር ብሏል።

ኢሰመኮ ያነጋገራቸው የመንግሥት ኃላፊዎች "ሕገ ወጥ የመሬት ወረራን ለመከላከል እና በተለምዶ "ፋኖ" ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ከኅብረተሰቡ ጋር በመቀላቀል የጸጥታ ስጋት እንዳይሆን ለማድረግ የሚወሰድ መሆኑን" መሆኑን ተናግረዋል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ ኬላ ዘርግተው ገንዘብ ለመቀበል ሲንቀሳቀሱ በነበሩ የቅማንት ታጣቂዎች እና ተሽከርካሪዎችን አጅበው ሲጓዙ በነበሩ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት በርካታ ሹፌሮች እና ተሳፋሪዎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገልጿል።

ሰኔ 16/2017 ዓ.ም. በተፈፀመው በዚህ ጥቃት የአፈር ማዳበሪያ ጭነው ሲጓዙ የነበሩ ቢያንስ 16 ሹፌሮች መገደላቸውን እና ቁጥራቸው በውል ያልታወቁት ደግሞ መታገታቸውን ቢቢሲ ዘግቦ ነበር።

በዚህ ጥቃት ሦስት ሹፌሮች ታግተው መለቀቃቸውን የጠቀሰው ሪፖርቱ፤ ሰኔ 18/2017 ዓ.ም. በታጣቂዎች ላይ እርምጃ ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ የመንግሥት ኃይሎች "በርካታ ሰዎችን" እንደገደሉ አረጋግጫለሁ ብሏል።

የኢሰመኮ የምርመራ ሪፖርት ጋምቤላ ክልልን ጨምሮ በቤንሻንጉል ጉሙዝ እና አማራ ክልሎች በታጣቂዎች እንቅስቃሴ፣በጸጥታ ስጋት እና ወንጀልን ለመቆጣጠር በሚል የሰዓት እላፊዎች እንደታጣሉ እና የሕክምና አገልግሎትን ጨምሮ ለዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እያሳደረ መሆኑን ገልጿል።

የመንገድ መዘጋት፣ የሰዓት እላፊ ገደብ፣ እገታ፣ ንብረት ዝርፊያ እና ውድመት ኢሰመኮ፤ "አጠቃላይ ማኅበረሰቡ በሕግ ሥርዓት ላይ ያለውን እምነት የመሸርሸር አደጋ [በመሆኑ]" እንዳሳሰበው ገልጿል።

መንግሥት ወንጀሎችን ለመከላከል እና አጥፊዎችን ተጠያቂ ለማድረግ "ሙሉ በሙሉ በሕግ እና ሥርዓትን በተከተለ እንዲሁም ሰብዓዊ መብቶችን ባከበረ መልኩ ሊመራ ይገባል" ሲል አሳስቧል።