በኢትዮጵያ ትምህርት ቤቶች ስልክን ጨምሮ ማንኛውንም የኤሌክትሮኒክስ ቁስ ይዞ መግባት ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ ታብሌት እና የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ይዞ መግባት እንደማይቻል ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
የትምህርት ሚኒስቴር በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ቅዳሜ፣ ጳጉሜ 1 2017 ዓ.ም. እንዳስታወቀው የ2018 ዓ.ም. ትምህርት መስከረም 2 በመምህራንና ተማሪዎች ውይይት ይጀመራል።
እንዲሁም ከመስከረም 5 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ የ2018 የመማር ማስተማር ሥራ እንደሚጀመር የአጠቃላይ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ አየለች እሸቴ መናገራቸው ሚኒስቴሩ በፌስቡክ ገፁ ላይ አስፍሯል።
ከ2018 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን ጀምሮ በሁሉም ከቅድመ መደበኛ እስከ 12ኛ ክፍል ትምህርት ቤቶች የሚገኙ ተማሪዎች፣ ተንቀሳቃሽ ስልክ፣ታብሌትና በትምህርት ሥራ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩና አዋኪ የኤሌክትሮኒክስ ቁሶችን ወደ ትምህርት ቤት ይዘው እንዳይገቡ በጥብቅ መከልከሉን ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ ለዚህ ክልከላ መነሻ ስለሆነው ምክንያት ምንም ያለው ነገር የለም።
በቅርቡ ደቡብ ኮሪያ በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን እና ሌሎች የግል የኤሌክትሮኒክ መገልገያዎችን መጠቀምን የሚከለክል ሕግ አውጥታለች።
ደቡብ ኮሪያ ያወጣችው ሕግ ከሚቀጥለው ዓመት መጋቢት ወር ጀምሮ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ የስልክ ሱስን ለመግታት ያለመ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስትር ክልከላውን ያስተላለፈበት ምክንያት ባይገለጽም ከጥቂት ዓመታት በፊት ኩረጃን ለመከላከል በሚል የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚወስዱ ተማሪዎች በዩኒቨርስቲዎች ውስጥ እንዲፈተኑ መወሰኑ ይታወሳል።
በአንዳንድ አገራት የተማሪዎች የሞባይል ስልክ አጠቃቀም የትምህርት አቀባበል ብቃታቸውን እየጎዳው መሆኑ፣እንዲሁም በጥናት ሊያሳልፉ የሚችሉትን ጊዜ እንደሚሻማ ይገልጻሉ።
አብዛኞቹ የደቡብ ኮሪያ ትምህርት ቤቶች አንዳንድ የስማርት ስልኮች እገዳን አገሪቱ ሕግ ከማውጣቷ አስቀድመው ተግባራዊ አድርገዋል።
እንደ ፊንላንድ እና ፈረንሣይ ያሉ አገራት ታዳጊ ልጆች በትምህርት ቤቶች ውስጥ ስልኮችን እንዳይጠቀሙ በተወሰነ መልኩ እገዳ ጥለዋል።
ሌሎች እንደ ጣሊያን፣ ኔዘርላንድስ እና ቻይና ያሉ አገራት ደግሞ በሁሉም ትምህርት ቤቶች የስልክ አጠቃቀምን ገድበዋል።
ኢትዮጵያም የእነዚህን አገራት አርዓያነት በመከተል ስልክን ጨምሮ የትኛውንም የኤሌክትሮኒክስ ቁስ ወደ ትምህርት ቤት ይዞ መግባት ከልክላለች።
ክልከላው ስልክ ይዘው የተገኙ ተማሪዎች ላይ ትምህርት ቤቶች መውሰድ ስላለባቸው እርምጃ፣ በኮምፒውተርና ሌሎች ቴክኖሎጂ መማሪያ ክፍለ ጊዜዎች ውስጥ የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ይዞ መምጣት ስለሚቻልበት አግባብነት፣ በቴክኖሎጂ የሚታገዙ አካል ጉዳተኞችን በተመለከተ ልዩ ሁኔታዎች ይኑሩ አይኑሩ መመሪያው ለጊዜው ያለው ነገር የለም።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በርካታ የአውሮፓ አገራት ተመሳሳይ እርምጃዎችን ወስደዋል።
ኔዘርላንድስ ለምሳሌ የሞባይል ስልኮችን ጨምሮ የመማር ማስተማር ተግባርን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ የተባሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶች በትምህርት ቤቶች ማገዷ ተዘገቧል።
በመማሪያ ክፍሎች ውስጥ የሞባይል ስልኮችን መጠቀም ያገደችው ኔዘርላንድስ ዕቅዱን ከትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረች ሰነባብታለች።
ሆኖም ልዩ የሕክምና ፍላጎት ወይም አካል ጉዳተኛ የሆኑ ተማሪዎች ይህ እገዳ አይመለከታቸውም።
በተጨማሪ በዲጂታል ክህሎቶች ላይ በሚያተኩሩ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት ላይ እነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች እንደሚፈቀዱም ተጠቁሟል።
የተለያዩ ጥናቶች የልጆችን የስክሪን ቆይታ ጊዜ መገደብ ከግንዛቤ እና ትኩረት መሻሻል ጋር እንደሚያያዝ አሳይተዋል።
የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር ግን የአካል ጉዳተኞችን እና የልዩ ፍላጎት ተማሪዎችን በሚመለከት ምንም ያለው ነገር የለም።
እንዲሁም በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ክፍለ ጊዜ ወቅት ስለሚኖር አጠቃቀም መመሪያው ምንም ያለው ነገር የለም።















