የልጆች የስክሪን ጊዜ አንጎል ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከሚታየው በላይ ውስብስብ ነው

ስዕል፤ ስክሪን ላይ ያቀረቀረ ህጻን ልጅ ሰዓት ላይ ቁጭ ብሎ

የአፕል ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበረው ስቲቭ ጆብስ የሚመራው ኩባንያ አይፓድን ለገበያ ባቀረበበት ወቅት ልጆቹ ይህ ቴክኖሎጂ እንዲኖራቸው አልፈቀደም ነበር።

ቢል ጌትስ፤ ልጆቹ ለቴክኖሎጂ ያላቸውን ቅርበት እንደገደበ ተናግሯል።

ብዙውን ጊዜ ከመጥፎ ዜና ጋር ተያይዞ የሚነሳው ረጅም ጊዜ ስክሪን ላይ መቆየት፤ በድብርት የሚጠቁ ወጣቶች ቁጥር ለመጨመሩ፣ ከባህርይ ጋር ለተያያዙ ችግሮች እና የእንቅልፍ እጦት መከሰት ተጠያቂ ተደርጎ ይጠቀሳል።

ታዋቂዋ የኒውሮሳይንስ ተመራማሪ ባሮኔስ ሱዛን ግሪንፊልድ ደግሞ፤ ኢንተርኔትን መጠቀም እና የኮምፒውተር ጨዋታዎች (games) በአስራዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ ልጆች አንጎልን ይጎዳል እስከ ማለት ትደርሳለች።

በአውሮፓውያኑ 2013 ባደረገችው ጥናት ረጅም የስክሪን ጊዜን የሚያስከትለው ጉዳትን ስለ የአየር ንብረት ለውጥ ጉዳይ ሲነሳ ከነበረባቸው የመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ጋር አነጻጽራለች።

በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የአየር ንብረት ለውጥ ሲሰጠው እንደነበረው አነስተኛ ትኩረት ሁሉ፤ ረጅም የስክሪን ጊዜም ሰዎች በቁም ነገር ያልተመለከቱት ነገር ግን ጉልህ ለውጥ የሚያመጣ ጉዳይ እንደሆነ አሳይታለች።

አሁን ላይ ግን ብዙ ሰዎች ጉዳዩን በቁም ነገር እየተመለከቱት ነው። ነገር ግን ስለ ጉዳቱ የሚነገሩ ማስጠንቀቂያዎች ብቻ ሙሉውን ታሪክ ላያሳዩን ይችላሉ።

በብሪቲሽ ሜዲካል ጆርናል ላይ የወጣ አንድ ርዕሰ አንቀጽ፤ ባሮኔስ ግሪንፊልድ ስለ አንጎል ያቀረበችው ሀሳብ "በሳይንሳዊ ማስረጃዎች ላይ የተመሠረተ አይደለም... እንዲሁም ለወላጆችም ሆነ ለጠቅላላው ሕዝብ አሳሳች ነው" በማለት ተከራክሯል።

አሁን ደግሞ ሌላ የዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች ቡድን፤ ረጅም የስክሪን ጊዜ ጉዳቶችን በተመለከተ ተጨባጭ ሳይንሳዊ ማስረጃ ይጎድላል ብሏል።

እናም ስለ ልጆቻችን የስክሪን ጊዜ መጨነቃችን እንዲሁም ታብሌት እና ስማርት ስልኮችን የሚያገኙበት መጠን እንዲገደብ ማድረጋችን ስህተት ነበር ማለት ነው?

ታብሌት ላይ እያረቀረች ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Arthur Debat/ Getty Images

እርግጥ እንደሚታሰበው መጥፎ ነው?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በባዝ ስፓ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆኑት ፒት ኤቸልስ፤ ጠንካራ ማስረጃ ይጎድላል በማለት ከሚከራከሩ ምሁራን አንዱ ነው።

የስክሪን ጊዜ እና የአእምሮ ጤንነትን በተመለከተ የተጻፉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥናቶችን እንዲሁም ከወጣቶች እና የስክሪን ልምዶቻቸው ጋር የተያያዙ ብዙ መረጃዎችን መርምሯል።

'Unlocked: The Real Science of Screen Time' በተሰኘው መጽሐፉ፤ የዜና አርዕስ ከሆኑት ድምዳሜዎች ጀርባ ያለው ሳይንስ ጥሩም መጥፎም ጉዳዮች የተቀላቀሉበት፤ ብዙውን ጊዜም ደግሞ የተሳሳተ ነው በማለት ተከራክሯል።

"በቀላሉ ለመናገር፤ ስለ ስክሪን ጊዜ አስከፊ መዘዞች የሚናገሩ ታሪኮችን የሚደግፍ ተጨባጭ ሳይንሳዊ ማስረጃ የለም" ሲል ጽፏል።

የአሜሪካ የሥነ ልቦና ማኅበር በ2021 ያሳተመው አንድ ጥናትም ተመሳሳይ ነገር አንስቷል።

በዓለም ዙሪያ ካሉ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ 14 ፀሐፊዎች፤ ከ2015 እስከ 2019 ባሉት ዓመታት ውስጥ የታተሙ 33 ጥናቶችን ተንትነዋል።

ስማርት ስልኮችን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እና የቪዲዮ ጨዋታዎችን ጨምሮ አጠቃላይ የስክሪን አጠቃቀም "በአእምሮ ጤንነት ስጋቶች ውስጥ ያለው ሚና ትንሽ ነው" ሲሉ ግኝታቸውን አስፍረዋል።

አንዳንድ ጥናቶች ከስክሪን የሚመነጨው ሰማያዊ ጨረር የእንቅልፍ ጊዜ መድረሱን ሰውነታችን እንዲረዳ የሚያደርገውን ሜላቶኒን የሚባለውን ሆርሞን ስለሚቀንስ እንቅልፍን አስቸጋሪ እንደሚያደርግ አሳይተው ነበር።

ባለፈው ዓመት ከዓለም ዙሪያ በተገኙ 11 ጥናቶች ላይ የተደረገው ግምገማ፤ ሰዎች ከመተኛታቸው አንድ ሰዓት በፊት ከሚያዩት ስክሪን የሚፈነጥቀው ብርሃን እንቅልፍን አስቸጋሪ እንደሚያደርግ የሚያሳይ ማስረጃ አልተገኘም።

ሳይንስ ያለበት ችግር

ፕሮፌሰር ኤቸልስ እንደሚናገረው፤ አንዱ ትልቅ ችግር ከስክሪን ጊዜ ጋር የተያያዘው ዳታ የሚሰበሰበው "በራስ ሪፖርት" ላይ መመሥረቱ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በሌላ አገላለጽ ተመራማሪዎች መረጃውን የሚሰበስቡት፤ ወጣቶች ምን ያህል ጊዜ ስክሪን ላይ አሳልፈናል ብለው እንደሚያስቡ እና ምን እንደተሰማቸው እንዲያስታውሱ በማድረግ ነው።

እነዚህን ከፍተኛ መጠን ያላቸውን ዳታዎች (መረጃዎች)፤ ከበርካታ ሌሎች ጉዳዮች ጋር ተያይዘው ሊተነተኑ የሚችሉበት መንገድ እንዳለ በመጥቀስ ይከራከራል። የነገሮችን "ተዛማጅነት ስንመለከት ጥንቃቄ ማድረግ አለብን" ይላል።

በበጋ ወቅት ከሚጨምረው የአይስክሬም ገዢዎች ቁጥር እና የቆዳ ካንሰር ተጠቂዎች ቁጥር ጋር የተያያዘውን ምሳሌም በማሳያነት ያነሳል።

የአስይስክሬም ገበያም ሆነ የቆዳ ካንሰር ታማሚዎች ብዛት የሚጨምረው ከሞቃታማ አየር ጋር ስለሚያያዙ እንጂ ሁለቱ ጉዳዩች ተዛማጅነት ስላላቸው እንዳልሆነ ይጠቅሳል። አይስክሬምም የቆዳ ካንሰር አያስከትልም።

ሜዳ ላይ የምትገለበጥ ህጻን

የፎቶው ባለመብት, Universal Archive/Universal Images Group via Getty Images

ሁለት ነገሮችን ባስተዋለ አንድ ጠቅላላ ሐኪም የተነሳ የተካሄደ አንድ የምርምር ፕሮጀክትም ያስታውሳል። ድብርት እና ጭንቀትን በተመለከተ ከወጣቶች ጋር ውይይት እየተደረገ የነበረ ሲሆን፣ ተራቸው ያልደረሰ መጠባበቂያ ክፍሎች ውስጥ የነበሩ ብዙ ወጣቶች ደግሞ ስልኮቻቸውን እየተጠቀሙ ነበር።

የሁለቱን ጉዳዮች ግንኙነት ለመረዳት መረጃዎችን እንደሰበሰቡ ፕሮፌሰር ኤቸልስ ይናገራል። ሁለቱ ጉዳዮች ግንኙነት ያላቸው ቢሆንም ድብርት እና ጭንቀት ያለባቸው ወጣቶች ምን ያህል ጊዜ ብቻቸውን ያሳልፋሉ የሚለው ሌላ ዋነኛ ምክንያት ነበር።

በመጨረሻም ጥናቱ ወጣቶቹ በአእምሮ ጤንነት ችግር እንዲሰቃዩ ያደረጋቸው የስክሪን ጊዜ ሳይሆን ብቸኝነት እንደሆነ አሳይቷል።

እንዲሁ 'ስክሮል' ማድረግ ወይስ ጠቃሚ የስክሪን ጊዜ

የስክሪን ጊዜ የሚለው ሀሳብ በራሱ የሚጎድሉት ዝርዝር ጉዳዮች እንዳሉት የሚናገረው ፕሮፌሰር ኤቸልስ፤ ቃሉ በራሱ እጅጉን የተምታታ ነው ሲል ይከራከራል።

ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ የሚያነቃቃ ነበር? ጠቃሚ ነበር? መረጃ ሰጪ ነበር? ወይስ እርባና የለሽ ነበር? ይህንን የሚያደርገው ወጣት ብቻውን ነበር? ወይስ ኦንላይን ላይ ከጓደኞቹ ጋር እያወራ ነበር?

እያንዳንዱ ሁኔታ የተለየ ውጤት አለው።

በአሜሪካ እና ዩናይትድ ኪንግደም ተመራማሪዎች የተደረገ አንድ ጥናት፤ ከ9 እስከ 12 ዓመት ዕድሜ ያላቸው 11,500 ሕፃናትን አንጎል ምርመራን፤ ከጤና ግምገማዎች እና ራሳቸው ከተናገሩት የስክሪን ጊዜ ጋር አንድ ላይ በማድረግ ተመልክቷል።

ጥናቱ የስክሪን አጠቃቀም ልምድ የአንጎል ክፍሎች እስር በራሳቸው የሚገናኙበትን መንገድ እንደሚቀይር ቢያሳይም፤ የስክሪን ጊዜ ከደካማ የአእምሮ ዕድገት ወይም ከግንዛቤ ችግሮች ጋር እንደሚገናኝ የሚያሳይ ማስረጃ አላገኘም። በቀን ውስጥ ለበርካታ ሰዓታትን ስክሪን ላይ በሚያሳልፉ ልጆች ላይ እንኳ ይህ አልታየም።

ከ2016 እስከ 2018 ድረስ የተካሄደ አንድ ጥናት ደግሞ የቪዲዮ ጨዋታዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ በአእምሮ ጤንነት ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ መርምሯል።

የጥናቱ ውጤት የቪዲዮ ጨዋታዎች እና ማኅበራዊ ሚዲያ አእምሮን ከመጉዳት ይልቅ ዕድገቱን ከፍ ሊያደርጉ እንደሚችሉ አሳይቷል።

ስልክ የምትመለከት ሴት

የፎቶው ባለመብት, Matt Cardy/Getty Images

"መጥፎው የአዕምሮ ጤንነት ቀመር"

የኦክስፎርድ ተመራማሪው ፕሮፌሰር አንድሪው ፕዝቢልስኪም ሆነ ፕሮፌሰር ኤቸልስ፤ ለልቅ እና ጎጂ ይዘቶች እንደመጋለጥ ያሉ የኦንላይን ልምምዶች የሚደቅኑትን ከባድ ጉዳይ አይክዱም።

ነገር ግን ሁለቱም በስክሪን ጊዜ ዙሪያ ያለው ክርክር ተጠቃሚዎች ልምዳቸውን እንዲደብቁት ሊያደርጋቸው ይችላል የሚል ስጋትን ያነሳሉ።

ዲቫይሶችን [ስልኮችን] ለመገደብ ወይም ጭራሽኑ ለመከልከል የሚቀርቡ ክርክሮች ላይ ያለውን ስጋት የሚገልጸው ፕሮፌሰር ፕዝቢልስኪ፤ የስክሪን ጊዜ የበለጠ ቁጥጥር በሚደረግበት ጊዜ ነገርየው የበለጠ "የተከለከለ ፍሬ" ሊሆን ይችላል የሚል እምነት አለው።

ብዙዎች ግን በዚህ አይስማሙም። 'ስማርትፎን ፍሪ ቻይልድሁድ' የተባለው የዩናይትድ ኪንግደም ተሟጋች ቡድን፤ ከ14 ዓመት በታች ለሆኑ ሕፃናት ዘመናዊ ተንቀሳቃሽ ስልኮችን ለመከልከል እና እስከ 16 ዓመታቸው ድረስ የማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ ለማድረግ በሚደረገው ዘመቻ ላይ 150 ሺህ ሰዎች ፊርማቸውን እንዳኖሩ ገልጿል።

የሳን ዲዬጎ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቦና ፕሮፌሰር የሆነችው ጂን ትዌንጅ፤ በአሜሪካ ታዳጊዎች ውስጥ እየጨመረ የመጣውን ድብርትን ማጥናት ስትጀምር ዓላማዋ ማኅበራዊ ሚዲያ እና ስማርት ስልኮች ክፉኛ ጎጂ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳልነበር ትናገራለች።

ግኝቷ ያመለከተው ግን በሁለቱ ጉዳዮች የሚያስተሳስራቸው የጋራ መለያ እንዳላቸው ነው።

አሁን ላይ፤ ልጆችን ከስክሪን መለየት ጥርጣሬ የሚያሻው ጉዳይ አይደለም ብላ ታምናለች። ወላጆች በተቻለ መጠን ልጆቻቸውን ከስማርት ስልክ እንዲለዩ ትወተውታለች።

የወጣቶች የስክሪን አጠቃቀምን በተመለከተ በሚደረጉ ጥናቶች ላይ የሚሰበሰበው መረጃ በአብዛኛው በራስ ሪፖርት የተደረገ መሆኑን ብትስማማበትም፤ ይህ ብቻውን ማስረጃውን ውድቅ አያደርገውም ትላለች።

89 ቤተሰቦች 181 ልጆችን ያካተተ አንድ የዴንማርክ ጥናት በ2024 ታትሞ ነበር። ከጥናቱ ተሳታፊዎች ግማሾቹ፤ ለሁለት ሳምንት የስክሪን ጊዜያቸው በሳምንት ለሦስት ሰዓታት ብቻ እንዲሆን ተገድቦ፤ ታብሌቶቻቸውን እና ስማርት ስልኮቻቸውን አስረክበዋል።

የጥናቱ ውጤት፤ የስክሪን ጊዜን መቀነስ "በሕፃናት እና በጉርምስና ዕድሜ ላይ ባሉ ወጣቶች ላይ አዎንታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር" እና "ማኅበራዊ ባህርይን" እንደሚያጠነክር ደምድሟል። በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ምርምር እንደሚያስፈልግም ግን ጠቁሟል።

ተሳታፊዎች የስክሪን ጊዜያቸውን እንዲመዘግቡ የተደረገበት ሌላ የዩናይትድ ኪንግደም ጥናት ደግሞ፤ ከፍተኛ የማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በሴቶች ላይ ከፍ ባለ የድብርት ስሜትን አብሮ መመዝገቡን ገልጿል።

ስልክ ወደ ፊቷ አቅርብ የምታይ ሴት

የፎቶው ባለመብት, Matt Cardy/Getty Images)

ፕሮፌሰር ትዌንጅ፤ "ቀመሩን ውሰዱ፤ ብዙ የኦንላይን ጊዜ እና አብዛኛውን ስክሪን ላይ ለብቻ መሆን፤ እንቅልፍን ይቀንሳል፣ ከጓደኞች ጋር በአካል የሚገናኙበት ጊዜን ይቀንሳል። ለአእምሮ ጤንነት ይህ መጥፎው ቀመር ነው" በማለት ያስረዳሉ።

"ይህ ጉዳይ ለምን እንደሚያወዛግብ አይገባኝም" ይላሉ።

የዓለም ጤና ድርጅት ከአንድ ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ምንም የስክሪን ጊዜ እንዲኖራቸው አይመክርም። ከአራት በታች የሆኑ ልጆች ደግሞ በቀን ከአንድ ሰዓት በላይ ስክሪን ላይ እንዳያሳልፉ ያሳስባል። የድርጅቱ ፖሊሲ በጥልቅ ሲታይ፤ ይህንን የሚመክረው ለልጆች አካላዊ እንቅስቃሴን ቅድሚያ በመስጠት ነው።

የስክሪን ጊዜም በተመለከተ ትክክለኛውን ምክር ለመስጠት በቂ ሳይንሳዊ ምርምር የለም፤ ጉዳዩም የሳይንስ ማኅበረሰቡን ከፋፍሏል። ማኅበረሰቡ በአንጻሩ ልጆች ለስክሪን ያላቸው ቅርበት እንዲገደብ ግፊት እያደረገ ነው።

ግልጽ መመሪያ በሌለበት በዚህ ሁኔታ ውስጥ፤ ሲያድጉ ቴክኖሎጂን በእጅጉ በሚጠቀሙ እና በተከለከሉ ልጆች መካከል እኩል ያልሆነ የመጫወቻ ሜዳ እየተፈጠረ ይሆን? አከራካሪ ቢሆንም ክልከላ የሚደረግባቸው ልጆች በመጨረሻም ይበልጥ የሚጎዱት መሆናቸው የሚቀር አይመስልም።

በሁለቱም መንገድ መሄድ አደጋው ከፍተኛ ነው። እርግጥም ስክሪን ልጆችን የሚጎዳ ከሆነ ሳይንስ ይህንን ለማረጋገጥ ዓመታትን ሊወስድ ይችላል። ወይም በመጨረሻም ጎጂ አይደለም ብሎ ይደመድማል።

በዚህ ጊዜ ደግሞ ልጆችን በጣም ጠቃሚ ሊሆን ከሚችል ነገር ለማራቅ መሞከራች እና ለዚህም ያወጣነው ገልበት እና ገንዘብ ብክነት ይሆናል።

እናም ስክሪኖች መነጽር ሆነው ዓይን ላይ እየመጡ ባሉበት እና ሰው ሰራሽ አስተውሎት (ኤአይ) ለበርካታ ጉዳዮች ጥቅም ላይ እየዋሉ ባሉበት በዚህ ጊዜ፤ ልጆቻችን ገደብንም አልገደብንም ቴክኖሎጂው እኛን ሳይጠብቅ የፍጥነት መንገዱን መቀጠሉ አይቀሬ ነው።