አውስትራሊያ ከ16 ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት ማኅበራዊ ሚዲያን ልታግድ ነው

አንዲት ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስትራሊያ መንግሥት ከ16 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የትኛውንም ማኅበራዊ ሚዲያ እንዳይጠቀሙ የሚያግድ ሕግ ሊያወጣ ነው።

ለአገሪቱ ፓርላማ በሚቀጥለው ሳምንት የሚቀርበው ረቂቅ ሕግ ማኅበራዊ ሚዲያ በአውስትራሊያ ህጻናት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት “ለመከላከል” ያለመ እንደሆነ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ ተናግረዋል።

“ይህ ሕግ ለአባቶች እና ለእናቶች ነው። እንደእኔ ወላጆች በኢንተርኔት ላይ የልጆቻችን ደኅንነት አሳምሞናል። የአውስትራሊያ መንግሥት በዚህ ሕግ ከጀርባችሁ ነኝ እያለ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

የረቂቅ ሕጉ ዝርዝር ለፓርላማ ቀርቦ ክርክር የሚደረግበት ቢሆንም እገዳው ቀድሞውኑ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ባሉ ታዳጊዎች ላይ እንደማይተገበር መንግሥት አስታውቋል።

ሆኖም ወላጆች ፍቃድ ቢሰጧቸውም ከተጠቀሰው ዕድሜ በታች ያሉ ህጻናት ማህበራዊ ሚዲያን መጠቀም አይችሉም።

ህጻናቱ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን እንዳይጠቀሙ ለመከላከል ተገቢ እርምጃዎችን መውሰድ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለቤቶች ኃላፊነት እንደሚሆንም መንግሥት አስረድቷል።

አልባኔዝ በህጻናቱ ተጠቃሚዎች ላይ ምንም ዓይነት ቅጣት አይኖርም ቢሉም ሕጎቹን ማስከበር የአውስትራሊያ የኢንተርኔት ተቆጣጣጣሪ ኢ-ሴፍቲ ኮሚሽነር እንደሚሆን ገልጸዋል።

ይህ ታዳጊዎችን ከማኅበራዊ ሚዲያ የሚያግደው ሕግ ከጸደቀ ከ12 ወራት በኋላ ተግባራዊ ይሆናል የተባለ ሲሆን፣ በየጊዜውም ግምገማ ይደረግበታል ተብሏል።

አብዛኞቹ ባለሙያዎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች የታዳጊዎችን አዕምሯዊ ጤንነት ሊጎዱ እንደሚችሉ ቢስማሙም ሙሉ በሙሉ ይታገድ በሚለው ላይ ተከፋፍለዋል።

አንዳንዶች እገዳዎች ውስብስብ የሆነውን የኢንተርኔት ዓለም እንዴት ማሰስ እንደሚችሉ ከማስተማር ይልቅ እንደ ቲክቶክ፣ ኢንስታግራም እና ፌስቡክ ላሉ መተግበሪያዎች ያላቸውን ተጋላጭነት የሚያዘገይ እንደሆነ ይተቻሉ።

ቀደም ሲል የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ህጻናትን ከማኅበራዊ ሚዲያ ለመገደብ የተደረጉ ሙከራዎች አልተሳኩም ወይም አተገባበራቸው ፈታኝ ሆኗል።

ለዚህም ደግሞ አንደኛው ምክንያት የዕድሜ ማረጋገጫ መስፈርቶችን ሊያሳልፉ የሚችሉ መተግበሪያዎች በመኖራቸው ነው።

መንግሥት ያቀደውን እገዳ በአገሪቱ ካሉ የህጻናት መብት ተሟጋች ቡድኖች ትልቁ የሆነው የአውስትራሊያው የህጻናት መብቶች ግብረ ኃይል ተችቶታል።

ግብረ ኃይሉ ከ100 በላይ ምሁራን እና 20 የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የፈረሙበት ግልጽ ደብዳቤ ለመንግሥት ያስገባ ሲሆን፣ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ከማገድ ይልቅ “የደኅንነት መመሪያዎችን” እንዲያስተዋውቁ ጠይቋል።

ቡድኑ በተጨማሪም ኢንተርኔትን ለመቆጣጠር የተነደፉ “ብሔራዊ ፖሊሲዎች” ህጻናት የዲጂታል ከባቢያቸው ጋር እንዲገናኙ እና ደኅንነቱ በተጠበቀ መልኩ መረጃዎችን እንዲያገኙ ዕድል መስጠት መሆኑን የተባበሩት መንግሥታት ምክርን ጠቁሟል።