ፑቲን የሩሲያ ጦር ሠራዊት አባላት ቁጥርን ከ1.3 ሚሊዮን በላይ ለማሳደግ ወሰኑ

የፎቶው ባለመብት, EPA
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የአገራቸውን ጦር ሠራዊት ቁጥር በ15 በመቶ ከፍ በማድረግ ከ1.3 ሚሊዮን በላይ የሚያደርሰው አዋጅ ላይ ፊርማቸውን በማኖር አጸቁ።
ይህም የአገሪቱ መንግሥት በቀጣይ ተጨማሪ 170 ሺህ ወታደሮችን ወደ ጦር ኃይሉ በመቀላቀል አጠቃላይ የሩሲያ ጦር ሠራዊት አባላት ቁጥርን ወደ 1.32 ሚሊዮን ያደርሰዋል ተብሏል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር የጦር ሠራዊት አባላት ቁጥርን መጨመር ያስፈለገው የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) መስፋፋትን ጨምሮ በሩሲያ ላይ የተደቀኑ አደጋዎች እየተጠናከሩ በመሆናቸው ነው ብሏል።
ሩሲያ ለ18 ወራት ያህል በቆየው የዩክሬን ጦርነት ቀላል የማይባል ወታደራዊ ኪሳራ እንደደረሰባት ይገመታል።
ምንም እንኳ የሩሲያ ጦር በዚህ ጦርነት የሞቱበትን የሠራዊቱን አባላት ቁጥር ባይገልጽም በ10 ሺዎች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር የሠራዊቱን ቁጥር ከፍ ለማድረግ በያዘው ዕቅድ አዲስ አባላት በቅጥር እንጂ አስገዳጅ በሆኑ ምልመላ ጦሩን እንደማይቀላቀሉ በመግለጫው አስታውቋል።
“የሩሲያ ፌዴሬሽን ጦር ኃይሎች አባላት ቁጥርን የመጨመር ሂደት ፍላጎት ያላቸውን ዜጎች በውል በመቀጠር በየደረጃው ተግባራዊ እየተደረገ ነው” ብሏል።
የመከላከያ ሚኒስቴሩ በሩሲያ ዙሪያ የኔቶ አባላት ቁጥር መጨመራቸው የፈጠረው የደኅንነት ስጋት እንዲሁም “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻ” ብሎ በሚጠራው የዩክሬን ጦርነት ምክንያት የጦሩን አባላት ቁጥር ለመጨመር እንደ ምክንያት አድርጎ አቅርቦታል።
ኔቶ በቅርቡ ከሩሲያ ጋር ከ1300 ኪሎ ሜትር በላይ ድንበር የምትጋራውን ፊንላንድ በቅርቡ አባል አድርጎ የመዘገበ ሲሆን፣ ስዊድንም አባል ለመሆኑ ጥያቄ አቅርባለች።
ኔቶ ከሩሲያ ጋር ጦርነት ውስጥ ያለችው ዩክሬንም “ሁኔታዎች ሲፈቅዱ” የጥምረቱ አባል ትሆናለች ማለቱ በሩሲያ በኩል የደኅንነት ስጋት አጭሯል።
ከሶቪየት ኅብረት ዘመን ጀምሮ የሩሲያ ተቀናቃኝ የሆነው የምዕራባውያኑ የጦር ኃይሎች ኅብረት የሆነው ኔቶ፣ የሩሲያ አጎራባች የሆኑ አባላትን እየጨመረ መሄዱ ያላስደሰታት ሩሲያ ተቃውሞዋን ስታሰማ ቆይታለች።
በተጨማሪም ሩሲያ ከአንድ ዓመት በፊት በዩክሬን ላይ ወረራ እንድትፈጽም ካደረጓት ጉዳዮች መካከል የኔቶ መስፋፋትን ለመግታት በማሰብ እንደሆነ ይነገራል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ዩክሬን የሩሲያን ወረራ እንድትከላከል እና እንድትቀለብስ ለማስቻል የኔቶ አባል አገራት በቢሊዮኖች ዶላር የሚያስወጡ እጅግ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን ማስታጠቃቸው ይታወቃል።
የሩሲያ ጦር አባላት ቁጥር ይጨምራል የሚለው ዜና የተሰማው የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቭሎደሚር ዜሌንስኪ በድንበር ላይ የሚገኘውን የአገሪቱን ጦር ማጠናከር ያስፈልጋል ካሉ በኋላ ነው።
በሩሲያ እና በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ያለው የቅዝቃዜ መጠን በአሁኑ ጊዜ ከዜሮ በታች እየወረደ ሲሆን፣ በድንበር አካባቢዎች መሠረተ ልማቶችን በማጠናከር ጦሩን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ ዜሌንስኪ ተናግረዋል።
ባለፉት ቀናት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምታካሂደውን ጥቃት ያጠናከረች ሲሆን፣ ሠራዊቷም በምሥራቃዊ ዩክሬን የምትገኘውን አቭዲቨካ ከተማ ለመክበብ ጥረት እያደረገ ነው ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም የሩሲያ ጦር በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙትን በኼርሶን እና በዛፖሬዢያ ግዛቶች ላይ ትኩረት ማድረጉ ተገልጿል።
ዩክሬን ከትናንት በስቲያ ሐሙስ ዕለት 18 የሩሲያ ድሮኖችን እና ሁለት ሚሳኤሎችን መትታ መጣሏን አስታውቃ ነበር።












