በሱዳን የሲቪል አስተዳደር እንዲመለስ በሠራዊቱ እና በተቃዋሚዎች መካከል ስምምነት ተደረሰ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የሱዳን የዴሞክራሲ አቀንቃኞች ጥምር ኃይል እና ወታደራዊ ኃይሉ አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ ስምምነት ተፈራረሙ።
‘ፎርስስ ኦፍ ፍሪደም ኤንድ ቼንጅ’ የተባለው የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ጥምረት እና የሱዳን ወታደራዊ ኃይል የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ተፈራርመዋል።
አምና ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ወዲህ ስምምነቱን ተከትሎ ምርጫ እስከሚካሄድ ድረስ፣ ለሁለት ዓመታት የሚዘልቅ የሲቪል የሽግግር አስተዳደር እንደሚኖር ተገልጿል።
ስምምነቱን የሚቃወሙ ሰልፎች መዲናዋ ካርቱምን ጨምሮ በሌሎችም አካባቢዎች እየተካሄዱ ሲሆን፣ ተቃውሞዎች እንደሚቀጥሉም ይጠበቃል።
መፈንቅለ መንግሥቱን የመሩ ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ ተቃዋሚዎች እየጠየቁ ይገኛሉ።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ፣ ሱዳን ላለፉት አራት ዓመታት የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ ቆይታለች።
የአፍሪካ ኅብረት፣ የአረብ አገራት እንዲሁም ምዕራባውያን አገራት በሱዳን ወታደራዊ ኃይል እና በሲቪል አመራሩ መካከል ስምምነት ተደርሶ በአገሪቱ ሰላም እና መረጋጋት እንዲሰፍን ሲገፋፉ ቆይተዋል።
ሕዝባዊው ተቃውሞ የሱዳን ምጣኔ ሀብት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል።
አሁን የተደረሰውን ስምምነት በተለያዩ አካባቢዎች በንቃት የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎች እና የተቃውሞ አስተባባሪዎች ነቅፈውታል።
መፈንቅለ መንግሥቱን በመቃወም አደባባይ የወጡ ሰዎች ግድያን በተመለከተ ጄኔራል አብደል ፋታህ አልቡርሃንን ጨምሮ ሌሎችም ወታደራዊ አመራሮች ተጠያቂ እንዲደረጉም ተቃዋሚዎቹ አሳስበዋል።
ስምምነቱ የደኅንነት ዘርፉ ላይ የሚደረግ ለውጥን እንደማያካትት እና ወታደራዊ ኃይሉ ከዚህ በኋላም ኃያል ሆኖ እንዲቀጥል እንደሚያስችል ተቃዋሚዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሆኖም ግን አመራሮች እንዳሉት፣ የፍትሕ እና የለውጥ ጥያቄዎች በቀጣይ በሚደረጉ ውይይቶች አማካይነት ምላሽ ያገኛሉ።
በሲቪል ጥምር ኃይሉ እና በወታደራዊ ኃይሉ መካከል የተደረሰው ስምምነት በሱዳን ሰላምና መረጋጋት ያሰፍናል ተብሎ ይጠበቃል።
በተለይም እአአ ጥቅምት 2015 ዓ.ም. ላይ ከተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት ጋር በተያያዘ ሱዳን በተቃውሞ እየተናጠች ትገኛለች።
የዴሞክራሲ አቀንቃኝ ጥምር ኃይሉ እንዳለው፣ ስምምነቱ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ አክትሞ አገሪቱ በሽግግር መንግሥት እንድታመራ መንገድ ይከፍታል።
ጥምር ኃይሉ “ቅድሚያ የምንሰጠው ለፍትሕ፣ የ1989ኙን አስተዳደር አፍርሶ ለመገንባት፣ የሕዝብ ንብረት ለማስመለስ እና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ነው” ብሏል።
በአገሪቱ የሚካሄደውን ተቃውሞ የሚያስተባብረው ‘ሱዳኒዝ ሬዚስታንስ ኪሚቴስ’ በበኩሉ፣ ጥምር ኃይሉ የደረሰበት ስምምነት የሱዳን ወታደራዊ አመራሮች ተጠያቂ ሳይሆኑ ከሥልጣን እንዲወርዱ የሚፈቅድ ነው ሲል ተችቷል።
የተቃውሞ ሰልፎች እንዲካሄዱም ጥሪ እየቀረበ ቢሆንም፣ ጥምር ኃይሉ ግን ክሱን አጣጥሏል።
ከስምምነቱ ቀድሞ የሱዳን አመራሮች ታዋቂውን ፖለቲከኛ ዋጂድ ሳሊህን ከእስር ለቀዋል።
የቀድሞው የፀረ ሙስና ኃላፊ የነበረ ሲሆን፣ የኦማር አልበሽርን አስተዳደር ከሥልጣን በማውረድ ሚና ተጫውቷል።












