ሩሲያ ዘግታው የነበረውን የአውሮፓ የነዳጅ ማስተላለፊያ ባንቧን ከፈተች

የኖርድ ስትሪም የነዳጅ ማጓጓዣ ቧንቧ

የፎቶው ባለመብት, Alamy

ሩሲያ በየዓመቱ ለምታካሂደው የጥገና ሥራ ለአስር ቀናት ዘግታው የነበረውን ወደ አውሮፓ የሚሄደውን የነዳጅ ማስተላለፊያ ኖርድ ስትሪም 1 ቧንቧን ከፈተች።

የአውሮፓ ኅብረት በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለጣለው ማዕቀብ ምላሽ ለመስጠት ሩሲያ የጋዝ ቧምቧዋን ሙሉ በሙሉ በመዝጋት አቅርቦቷን ታቋርጣለች የሚል ፍራቻ ሰፍኖ ነበር።

በያዝነው ሳምንት ረቡዕ ዕለት ሩሲያ የጋዝ አቅርቦቷን የምታቋርጥ ከሆነ በሚል በሚቀጥሉት ሰባት ወራት አገራቱ የጋዝ አጠቃቀማቸውን 15 በመቶ እንዲቀንሱ የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን አሳስቧል።

ሩሲያ ባለፈው ዓመት 40 በመቶ የሚሆነውን የተፈጥሮ ጋዝ ለአውሮፓ አቅርባለች።

ጀርመን በአውሮፓውያኑ 2020 የአውሮፓ አህጉር ትልቁ የጋዝ አስመጪ የነበረች ቢሆንም ጦርነቱን ተከትሎ በሩሲያ ጋዝ ላይ ያላትን ጥገኝነት ከ55 በመቶ ወደ 35 በመቶ ዝቅ ማድረጓ ተሰምቷል።

ጀርመን ከሩሲያ ጋዝ ማስመጣቷን ሙሉ በሙሉ ማቆም ትፈልጋለች።

የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አውሮፓውያን የሰፈነባቸውን ፍራቻ ለመቅረፍ ሞክረዋል። የሩሲያ መንግሥት ተቋም የሆነው ጋዝፕሮም የውል ግዴታውን ሙሉ በሙሉ እንደሚወጣ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።

ቧንቧው ዛሬ ሐምሌ 14/2014 ዓ.ም. ማለዳ ላይ ሥራውን የጀመረ ሲሆን፤ ነገር ግን ቃለ አቀባዩ የአቅሙን 40 በመቶ ብቻ እያቀረበ ነው ብለዋል።

ይህም በሰኔ ወር አጋማሽ ላይ በጀርመን ሲመንስ ኢነርጂ ሊታደሱ የሄዱ መሣሪያዎች መዘግየታቸውን በመጥቀስ ጋዝፕሮም የጋዝ ፍሰትን በቀነሰበት ወቅት የነበረበት ተመሳሳይ ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል።

በቀነሰ አቅምም ቢሆን ነዳጅ ለአውሮፓ እየቀረበ ነው።

በሩሲያ ነዳጅ ከፍተኛ ጥገኛ የሆነችው ጀርመንም ሆነ ሌሎች የአውሮፓ አገራት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚያስፈልጋቸውን ነዳጅ ያቀርባሉ የሚል አመኔታ አጥተዋል።

በሙቀት ማዕበል በተመታችው አውሮፖ ያሉ አገራት ሚኒስትሮች አገሪቱ ለመጪው ቅዝቃዜ ወቅት በቂ የተከማቸ ጋዝ እንደሌላቸው ተረድተውታል።

አውሮፓውያን ዜጎቻቸው የኃይል አጠቃቀማቸውን እንዲቀንሱ እየተማጸኑ ነው። በተጨማሪም ከሌሎች አገራት ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝ አቅርቦትን ለማግኘት እንዲሁም በበርካታ አገራት እንዲቀር የተደረገውን ከድንጋይ ከሰል ኃይል ለማመንጨትም እየሞከሩ ነው።