ተተኪ የዩኬ ጠቅላይ ሚኒስትር ለመሆን ሁለት እጩዎች እየተፎካከሩ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
የዩናይትድ ኪንግደም ገዢ የሆነው ወግ አጥባቂ ፓርቲ አመራር ውስጥ ያሉ ሁለት እጩዎችን የጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰንን ተተኪ ለሚመርጡ የፓርቲ አባላት ዕቅዳቸውን እያሰሙ ነው።
ረቡዕ ዕለት በነበረው የፓርላማ አባላት የመጨረሻ ድምፅ አሰጣጥ መሰረት ሪሺ ሱናክ እና ሊዝ ትሩስ ቀጣዩን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመተካት ከፍተኛ ድምፅ ያገኙ ሆነዋል።
ሪሺ ሱናክ ቀጣዩ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የሚመረጡ ከሆነ “በ1980ዎቹ ማርጋሬት ታቸር እንዳደረጉት ስር ነቀል ማሻሻያዎችን “ እንደሚያመጡ በዴይሊ ቴሌግራፍ ላይ ጽፈዋል።
ሌላኛው ዕጩ ተወዳዳሪ ሊዝ ትሩስ በበኩላቸው “ግብር ቅነሳ፣ ኢንተርፕራይዞንችን ማበረታታት፣ ለንግድ ተስማሚ የሆነ የወግ አጥባቂ ፖሊሲ” ላይ እንደሚሰሩ በዴይሊ ሜል ባሰፈሩት ፅሁፍ ላይ ቃል ገብተዋል።
ሪሺ ሱናክና ሊዝ ትሩስ የፓርላማ አባላቱን ከፍተኛ ድምፅ ማግኘት ችለዋል። በአንድ ወቅት የፖርቲው አባላት ተመራጭ የነበሩት የንግድ ሚኒስትሯ ፔኒ ሞርዳውንትን ያገኙትን ድምፅ በመብለጥ ሊዝ ትሩስ በ113 ድምፅ ሁለተኛ ተመራጭ ሆነዋል።
እስካሁን ድረስ ያለማቋረጥ እየመሩ ያሉት የቀድሞው ቻንስለር ሪሺ ሱናክ በ137 ድምፅ በምርጫው ቀዳሚውን ስፍራ አግኝተዋል።
ሁለቱ የመጨረሻ እጩዎች በዩናይትድ ኪንግደም ዙሪያ የሚደረጉ ጉባኤዎችን ያዘጋጃሉ። የመጀመሪያው ከሳምንት በኋላ በሊድስ ከተማ የሚዘጋጀው ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በለንደን ነሐሴ መጨረሻ ላይ ይደረጋል ተብሏል።
በተጨማሪም ሁለት የቴሌቪዥን ክርክሮች የሚያካሂዱ ሲሆን አንደኛው ሀምሌ 18፣ 2014 ዓ.ም ሲሆን ይህም የሚዘጋጀው በቢቢሲ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሐምሌ መጨረሻ ላይ የሚደረግ ሲሆን በስካይ ኒውስ መዘጋጀቱም ተገልጿል።
ወደ 160 ሺህ የሚጠጉ የፓርቲው አባላት በኦንላይን ወይም በፓስታ ድምፃቸውን ይሰጣሉ። ድምፃቸውንም እስከ ሐምሌ መጨረሻ ድረስ ሰጥተው ማጠናቀቅ የሚጠበቅባቸው ሲሆን የመጨረሻው ውጤት ነሐሴ 30፣ 2014 ዓ.ም ይገለጻል።
በአሁኑ ባለው የህዝብ አስተያየት መሰረት ሪሺ ሱናክ ቻንስለር በነበሩበት ጊዜ ግብርን ቆልለዋል ሲሉ የተቹት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ሊስ ትሩስ ተመራጭ እጩ እንደሆኑ ይጠቁማሉ።












