የፍሬንድስ ፊልም ተዋናይ ማቲው ፔሪ በ54 ዓመቱ አረፈ

 ማቲው ፔሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቻንድለር ቢንግ የተሰኘ ገጸ ባህርይን በመጫወት ዕውቅና ያገኘው የፍሬንድስ ተከታታይ ፊልም ተዋናይ ማቲው ፔሪ በ54 ዓመቱ አረፈ።

ተዋናዩ ሎስ አንጀለስ በሚገኘው መኖሪያ ቤቱ ሞቶ መገኘቱንም የህግ አስከባሪ ምንጮች ለአሜሪካ ሚዲያ ተናግረዋል።

ማቲው ፔሪ በሌሎች ፊልሞች ላይ ቢተውንም ከፍተኛ ዝናን ያተረፈው ለአስር ዓመታት ከአውሮፓውያኑ 1994- 2004 በታየው ተወዳጁ ሲትኮም ‘ፍሬንድስ’ ነው።

በስድስት ጓደኞች ላይ የሚያተኩረው ‘ፍሬንድስ’ በጓደኝነት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን ከተሰራበት አሜሪካ ውጪም በርካታ የዓለማችን የፊልም አፍቃሪዎች ተወዳጅነትን አግኝቷል።

የመጨረሻው የፊልሙ ክፍል በ52.5 ሚሊዮን ህዝብ የታየ ሲሆን በ2000ዎቹ በከፍተኛነት በመታየት የመጀመሪያ ደረጃ ተቀምጧል።

ማቲው ፔሪ ለመጀመሪያ ጊዜ መሞቱን የዘገቡት ኤልኤ ታይምስ እና ቲኤምዚ በቤቱ ውስጥ በሚገኝ ገንዳ ራሱን ስቶ መገኘቱን አስነብበዋል።

የሎስ አንጀለስ የእሳት አደጋ ቢሮ ቃለ አቀባይ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የመጀመሪያ እርዳታ ሰጪዎች በፓስፊክ ፓሊሳዴስ አካባቢ ከውሃ ድንገተኛ አደጋ ጋር በተያያዘ እርዳታ ለመስጠት መሄዳቸውን ቢናገሩም የተዋናዩን ስም አልጠቀሱም።

የፍሬንድስ ፊልም ተዋናዮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፍሬንድስን የሰራው ዋርነር ብራዘርስ የተሰኘው የፊልም ኩባንያም “ በውድ ወዳጃችን ማቲው ፔሪ ሞት ከፍተኛ ኃዘን ተሰምቶናል” የሚል መግለጫ አውጥቷል።

“ማቲው ድንቅ ተሰጥኦ የነበረው እና የማይጠፋ አሻራንም በዋርነር ኩባንያ ትቷል” ሲልም መግለጫው አክሏል።

“አስደናቂ በሆነ ሁኔታ በበርካቶች ዘንድ ፈገግታን ማምጣት የቻለው ገጸ ባህርዩ መላው አለም ተመልክቶታል። የተዋናዩም ትሩፋት በብዙዎች ልብ ውስጥ የሚኖር ነው። ይህ በጣም ልብ የሚሰብር ቀን ነው። ለቤተሰቦቹ፣ ለወዳጆቹ፣ እና ለሚወዱት አፍቃሪዎቹ ሐዘናችንን እንገልጻለን” ብሏል።

ቻንድለር (ማቲው ፔሪ) የተወለደው በማሳቹስተስ ሲሆን ያደገው በካናዳዋ ከተማ ኦታዋ ነው። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱንም ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶ ጋር ነው የተከታታለው። ማቲው በአስራዎቹ ዕድሜው ነው ወደ ሎስ አንጀለስ የመጣው። ቻዝ ረስል፣ ቦይስ ዊል ቦይስ በተሰኙ ፊልሞች ቢተውንም ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ፍሬንድስ በተሰኘው ተከታታይ ፊልሙ ነው።