ዘመዶቻቸውን ፍለጋ አጽም ማገላበጥ እና መቃብር መቆፈር የጀመሩት ሶሪያዊያን

ኻሊድ መሐመድ መቃብር እየቆፈረ ወንድሞቹን ሲፈልግ

አድራ እንግዳ የሚባል ዓይነት የመቃብር ስፍራ ነው። ሁለት ሐውልቶች ብቻ ቆመዋል። የቀረው ሰፊ ቦታ ላይ ደግሞ እዚህም እዚያም ጉብ ጉብ ያሉ የአፈር ቁልሎች አሉበት። አንዳንዶቹ ሳር በቅሎባቸዋል።

ይህ አካባቢ ለዓመታት በፕሬዚዳንት በሻር አል አሳድ ጦር በጥብቅ ይጠበቅ ነበር።

አሁን የአሳድ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ በዚህ ባዶ የመቃብር ሥፍራ አንድ ጥግ ላይ ያለው የተከመረው የኮንክሪት ንጣፍ ሲነሳ ግማሽ ደርዘን የሚጠጋ አስከሬን ይዟል። በእያንዳንዱ ላይ ስም እና የእስር ቤት ቁጥሮች ተለጥፎባቸዋል።

በአካባቢው ነዋሪ የሆነው ኻሊድ አል ሃማድ ከረጢቶቹን አንድ በአንድ ያወጣል።

አስቀድሞ ያወጣቸውን ሦስቱን ከፍቶ አሳየ። ሁሉም የሰው አጽም ይዘዋል። የተጻፈባቸው መረጃ የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ አስከሬኖች መሆናቸውን ይጠቁማል።

እንዴት እንደሞቱ ግልጽ አይደለም። በአሳድ መንግስት ለተፈጸመው የወንጀል ማስረጃ ስለመሆኑም በተመሳሳይ ግልጽ አይደለም።

ኻሊድ ሌላ አሳማኝ አያስፈልገውም። ከአስር ዓመታት በፊት በአሳድ የአየር ኃይል የተወሰዱትን ሁለቱ ወንድሞቹን ጂሃድ እና ሁሴንን እየፈለገ ነው። ከተወሰዱ በኋላ ስለወንድሞቹ ምንም አልሰማም።

በመቃብር ስፍራው የተገኙ አስከሬኖች

"አንዳንድ ሰዎች 'የመንጃ ፈቃድ ትምህርት ቤት' ተብሎ ወደሚጠራው አካባቢ በጭካኔ ተወስደው ተገድለዋል። ይህ በወንድሞቼ ላይም እንደደረሰ አምናለሁ። ምናልባትም እዚህ ከተቀበሩት ውስጥ ሊሆኑ ይችላሉ" ብሏል።

ቢቢሲ ጉዳዩን በሶሪያ ለሚገኘው ሂውማን ራይትስ ዎች አካፍሏል። በሌላ ቦታ በተመሳሳይ መልኩ ስለተቀበሩ እስረኞች መረጃ ደርሷቸው እያጣሩ መሆኑን ገልጸዋል።

የአሳድ ውድቀት በዘመዶቻቸው ላይ ምን እንደደረሰ ለማወቅ ዕድል ሳያገኙ ለብዙ አሥርት ዓመታት የተቀመጡ ቤተሰቦች ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል።

"(በአሳድ ጊዜ) በዚህ ካለፍክ ማቆም አትችልም። ቀና ብለህ ማየትም አትችልም" ይላል ኻሊድ።

"መኪኖች በፍጥነት ያልፉ ነበር። ካቆምክ መጥተው በፕላስቲክ ፊትህን ሸፍነው ይወስዱሃል።"

በተመሳሳይ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በታዋቂዎቹ የአሳድ እስር ቤቶች ወይም በወታደራዊ የምርመራ ማዕከላት ውስጥ የተሰወሩ ዘመዶቻቸውን እየፈለጉ ነው።

አንዳንዶቹ ደማስቆ ወደሚገኘው ማዜህ ወታደራዊ የጦር ሰፈር ተወስደዋል።

የኤችቲኤስ አዛዥ አቡ ጃራህ

ጣብያው አሁን ባዶ ሆኗል። የተጣሉ ወታደራዊ ጫማዎች በየቦታው ወዳድቀዋል። ሮኬትም ይገኛል። አዲስ ጠባቂዎች ብቻ ናቸው ናቸው በአካባቢው የሚታዩት።

ጠባቂዎቹ የሃያት ታህሪር አል ሻም (ኤችቲኤስ) ወጣት ሚሊሻዎች ናቸው። ኤችቲኤስ ባለፈው ሳምንት ሶሪያን የተቆጣጠረው ቡድን ነው።

የአሳድ ኃይሎች የሚጠቀሙበትን የማሰቃያ ክፍል ለቢቢሲ አሳይተዋል። ለእስረኞች ግርፋት የሚያገለግል የብረት ዘንግ እና ከኤሌክትሪክ ማብሪያ እና ማጥፊያ ጎን የሚገኙ ሽቦዎች ይጠቀሳሉ።

"እነሆ እስረኞችን በኤሌክትሪክ ያሰቃያሉ። እነዚህ የኤሌክትሪክ ሽቦዎች ናቸው - መርማሪው እዚህ ይቀመጣል። ጠባቂዎቹ በእስረኛው አካል ላይ ሽቦዎቹን አስቀምጠው ኃይሉን ያበሩታል" ሲል የጠባቂዎቹ አዛዥ አቡ ጃራህ ተናግሯል።

"እስረኛው አእምሮውን ስቶ ሁሉንም ነገር ይናዘዛል። መርማሪው ስቃዩን ያቆማል በሚል ተስፋ የፈለገውን እንዲጽፍም ይነግሩታል።"

በስፍራው የተያዙ 400 ሴቶች በመደበኛነት ይደፈሩ እንደነበር አቡ ጀራህ ተናግሯል። በእስር ቤቱ ውስጥ ልጆች መወለዳቸውን አክሏል።

ዘመዶችዎን እዚህ ካሉት መዝገቦች ውስጥ ከማግኘት የበለጠ የሚያሰቃየው ብቸኛው ነገር አለማግኘታቸው ነው።

ከጎን ባለው ሕንፃ ውስጥ ቤተሰቦች ወለል ላይ የተዘረገፉ ፎቶግራፎችን እያገላበጡ ዘመዶቻቸውን ይፈልጋሉ።

ወለል ላይ የተበታተኑ ፎቶዎች

ፎቶዎቹን እያለቀሱ ከሚያገላብጥቱት መካከል ከአልቃሚሽሊ የመጣቸው የመሐሙድ ሰኢድ ሁሴን እናት አንዷ ናት።

"ትናንት በአየር ኃይል እስር ቤት ተመዝግቦ እንደነበር አይተናል። እዚህ ብንፈልገውም ልናገኘው አልቻልንም። 11 ዓመት ሙሉ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው እስር ቤት እየዞርኩ እየፈለግኩት ነው" ብላለች።

"እነዚህ ሁሉ ልክ እንደ ልጄ ናቸው" ብላ የተከመረውን ፎቶ እያሳየች አለቀሰች። "አሳድ የእኛን ልብ እንዳቃጠለ ፈጣሪ ልቡን ያቃጥልልን።" ትላለች

ቀጥሎ ባሉት ሦስት ክፍሎች እስከ ጣራው የታጨቁ ፋይሎች እርስ በእርሳቸው ተነባብረው ተቀምጠዋል። በርካታ ሰዎች ወለሉን ከሸፈነው የሰነድ ተራራ ላይ ተደፍተዋል።

የአሳድ መንግስት ጭካኔውን በመመዝገብ ረገድ በትኩረት ሠርቶ ነበር። ሰፊው የሽብር ቢሮክራሲ የእርምጃውን ስፋት በጣም ግልጽ ቢያደርገውም ግን የግለሰቦች ታሪክ የሚጠፋበት ወይም የሚቀላቀልበት አጋጣሚ ብዙ ነው።

ለዓመታት ልጃቸው ፈለጉት የመሐመድ ሰዒድ እናት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"እነዚህ ማስታወሻዎች ምንድን ናቸው?" ስትል አንዲት ሴት በንዴት ጠየቀች። "ማንም ሰው አይረዳንም። አንድ ሰው መጥቶ እነዚህን ሰነዶች ከእኛ ጋር እንዲያጣራ እንፈልጋለን። እንዴት ከዚህ ሁሉ የእስር ቤት መዝገቦች ውስጥ ላገኘው እችላለሁ?"

የተቀናጀ የፍለጋ ስርዓት ባለመኖሩ በሶሪያ በሚገኙ ጣቢያዎች ውስጥ በየቀኑ ወሳኝ የሚባሉ ማስረጃዎች እንዲጠፉ ምክንያት ሆኗል።

ስለጎደሉት ብቻ ሳይሆን በአሳድ አገዛዝ እና እንደ አሜሪካ ወይም ዩናይትድ ኪንግደም ባሉ መንግስታት መካከል ያለው ግንኙነት ሊኖር ይችላል።

የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የዩናይትድ ኪንግደም መንግስት የፀረ ሽብር ጦርነት እየተባለ በሚጠራው ወቅት አሜሪካ፤ ሶሪያን ጨምሮ ወደ በርካታ የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እስረኞችን እንዲሰቃዩ ስትልክ ነበር ሲሉ ከሰዋል።

ከህንጻው ውጭ የአየር ኃይሉ ፀጥ ያለ ግቢ ባለፈው ሳምንት በተፈጸመ የእስራኤል ተደጋጋሚ የአየር ድብደባ ምክንያት በሩስያ ሰራሽ በሆኑ አውሮፕላኖች እና ራዳር ላይ ኣደረሰውን ጉዳት ያሳያሉ።

የአሳድ አገዛዝ ማክተም በሶሪያ ውስጥ በሚጋጩ ቡድኖች እና እንደቱርክ፣ ኢራን እና አሜሪካ ያሉ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ደጋፊዎቻቸው መካከል ያለውን የሃይል ሚዛን ቀይሮታል።

ይህ የሶሪያ ጦርነት ብቻ አልነበረም። የውጭ ኃይሎች አሁንም በአገሪቱ በሚሆነው ነገር ድርሻ አላቸው።

ሶሪያውያን ምን ማድረግ እንዳለባቸው ማንም ጣልቃ ሳይገባባቸው ራሳቸውን በራሳቸው የሚያስተዳድሩበት ጊዜ ላይ እንደደረሱ አጥብቀው ይናገራሉ።

አንድ ወጣት የኤችቲኤስ ተዋጊ ከህንፃ በላይ የተሰቀለውን የአሳድን ፎቶ ለመቅደድ ጣሪያው ላይ ወጣ።

ፎቶዎቹን በመቀደድ ላይ ሳለ ከታች የሚመለከቱትን አዛዦቹን ተመልክቶ ፈገግ አለ።

የአሳድ ውድቀት እስካሁን ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎችን ደቅኗል። ስላለፉት ጊዜያትም ቢሆን ብዙ ጥያቄዎችን መመለስ አልተቻለም።