ስፔን የአውሮፓ ኅብረት አባል ያልሆኑ ዜጎች ላይ መቶ በመቶ የቤት ግብር ልትጥል ነው

የስፔን አፓርትማዎች

ስፔን ዩናይትድ ኪንግደምን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት አባል ሀገራት ያልሆኑ ዜጎች ላይ መቶ በመቶ የመኖሪያ ቤት ግብር ልትጥል አቅዳለች።

ዕቅዱን ይፋ ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ፔድሮ ሳንቼዝ እንዳሉት ይህ "ያልተጠበቀ" እርምጃ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የቤት እጥረት ለመቅረፍ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

"የምዕራቡ ዓለም አጣብቂኝ ውስጥ ገብቷል። በሁለት መደቦች የተከፈለ ማኅበረሰብ ሊፈጠር አይገባም፡ ሀብታም አከራዮች እና ድሀ ተከራዮች" ብለዋል።

በአውሮፓውያኑ 2023 ስፔናዊ ያልሆኑ ሰዎች 27 ሺህ ቤቶች ገዝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአንድ የምጣኔ ሀብት ስብሰባ ላይ እንዳሉት ግለሰቦቹ ቤቶቹን የገዟቸው "ሊኖሩበት ሳይሆን፤ ገንዘብ ሊያገኙበት ነው።"

"አሁን ባለንበት የቤት እጥረት ሁኔታ እንዲህ ዓይነት ተግባር አንፈቅድም" ሲሉ አክለዋል።

ሳንቼዝ አሁን "ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ቤቶችን ለሀገሩ ሰው ማቅረብ" እንደሆነ ገልፀዋል።

ይህ አዲሱ የቤት ግብር መቼ ለፓርላማው እንደሚቀርብ ግልፅ አይደለም። እንዴትስ ተግባራዊ ይሆናል የሚለው ጥያቄ አልተመለሰም።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ረቂቅ አዋጁ እንዲፀድቅ የሚያስችል ድጋፍ ያገኙ ይሆን የሚለው ጊዜ የሚፈታው ነው።

ነገር ግን የፔድሮ ሳንቼዝ መንግሥት አዋጁን ይፋ የሚያደርገው "በጥንቃቄ ካጠናው በኋላ" መሆኑን አስታውቋል።

የቤት ግብር ሳንቼዝ ሰኞ ዕለት በሀገራቸው ያለውን የቤት እጥረት ለመቅረፍ ይፋ ካደረጓቸው መካከል አንዱ ሲሆን ሌሎች መፍትሔ ይሆናሉ ያሏቸውን ሐሳቦችም አካፍለዋል።

ተመጣጣኝ የቤት ኪራይ ለሚያስከፍሉ አከራዮች ከግብር ነፃ ማድረግ፤ 3 ሺህ ቤቶችን ለመንግሥት ማስተላለፍ፤ እንዲሁም ለቱሪስቶች የሚከራዩ ቤቶች ላይ ጥበቃ ማድረግ እና ግብር መጫን እንደ መፍትሔ ተነስተዋል።

"ሶስት፣ አራት ወይም አምስት አፓርትማ ያላቸው ሰዎች ከሆቴሎች ያነሰ ግብር መክፈላቸው ፍትሐዊ አይደለም" ብለዋል።