የኢትዮጵያዊቷን ሬስቶራንት በእንግሊዝ አረጋውያን ተወዳጅ ያደረገው ምንድን ነው?

ቱቱ መላኩ በእንግሊዟ ሬዲንግ ከተማ ፓልመር ፓርክ አካባቢ ካፌ እና ሬስቶራንት አላት።
አብዛኞቹ ደንበኞቿ የዕድሜ ባለፀጋዎች ናቸው። አንድ ሳምንት ከምግብ ቤቷ ከጠፉ አያስችላትም። ስልኳን አንስታ ጤንነታቸውን ትጠይቃለች።
ቱቱ የቢቢሲ ራድዮ የበርክሸር የማለዳ እንግዳ ነበረች። "አረጋዊያንን እንንከባከባቸው" ትላለች።
ኢትዮጵያ ውስጥ የዕድሜ ባለፀጋ ወላጆች "ምንም ቢሆን" ከልጆቻቸው ጋር እንደሚኖሩ ትናገራለች።
"እንደ ማኅበረሰብ [አረጋዊያንን] ልንከባከብ ይገባል" የቱቱ መልዕክት ነው።
"እባካችሁ በራቸውን አንኳኩተን እንጠይቃቸው፤ እንደውልላቸው። ከአጠገባቸው እንዳለን እንንገራቸው።"
ቱቱ ባለፈው መስከረም ለዚህ ተግባሯ ሽልማት ተችሯታል። "ዋናው ነገር ለሰዎች ቦታ እንዳለን" ማሳየት ነው ትላለች።
"ሰዎች የራሳቸው ችግር አለባቸው" ስትል ታስገነዝባለች።
"እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ሳድግ የዕድሜ ባለፀጋ ወላጆቻችንን መንከባከብ ግዴታ ነው። ከእኛ ጋር ይኖራሉ። የአረጋዊያን መኖሪያ የሚባል ነገር አልነበረም። ለዚህ ይመስለኛል አረጋዊያንን መንከባከብ እንደ ሥራዬ አድርጌ የምቆጥረው።"

ከደንበኞቿ መካከል አንዱ የ95 ዓመቱ ኮሊን ዴኒስ ናቸው። ጤናማ እና ሳቂታ እንዲሁም "ራሳቸውን ችለው የሚንቀሳቀሱ" አረጋዊ መሆናቸውን ትመሰክራለች።
ኮሊን ከሴት ልጃቸው ቤት አጠገብ ነው የሚኖሩት። ይህ ደግሞ የሚደርስላቸው ሰው እንዳለ እንዲሰማቸው እንዳደረገ ቱቱ ትናገራለች።
"በጣም ደስ ይላል። ሁሌ አየዋለሁ። በጣም ደስተኛ ነው። ምክንያቱ ምን እንደሆነ አውቀዋለሁ።"
ዴኒስም ይህን ይመሰክራሉ። ከልጃቸው እና ከባሏ ጋር ማዕድ ይቋደሳሉ። አንዳንዴም ቴሌቪዥን ይመለከታሉ።
"ይንከባከቡኛል። ስለእሱ ምንም ጥርጥር የለኝም። ብቻዬን መሆን ሲያሰሰኝም ብቻዬን መሆን እችላለሁ" ይላሉ።

ቱቱ በአካባቢው በካፌ እና በሬስቶራንት ሥራ ለ18 ዓመታት ቆይታለች። ሥራዋ በአካባቢው ማኅበረሰብ ተወዳጅ እንደሆነም ትናገራለች።
"ማኅበረሰቡ ከሁሉም ቦታ የተውጣጣ ሰው ያለበት ነው። እኔ ሁሉንም ተቀብዬ አስተናግዳለሁ። ዕድሜ እና ዘር ለይቼ አላገልም። ሁሉን እኩል ነው የማየው" ስትል ለቢቢሲ ትናገራለች።
"ለዚህ ይመስለኛል ካፌው እስከ ዛሬ በሥራ ላይ የሚገኘው። ምክንያቱም ዋና ዓላማዬ ማኅበረሰቡን ማገልገል ነው።"
"ማኅበረሰብ የምናገለግል ከሆነ ቢዝነሳችን በራሱ ይንቀሳቀሳል" ስትልም ታክላለች።
ቱቱ እንደምትለው ማኅበረሰቡን ማገልገል ብቻ ሳይሆን እሷም ትጠቀምበታለች።
"ለእኔም ቢሆን ጥቅም አለው። ነብሴ ትረካለች፤ ልቤ ይደሰታል። ቤት ገብቼ መልካም ሥራ እንደሠራሁ ሳስብ ደስ ይለኛል" ትላለች።
"ለእኔ ሕይወት ይህ ነው። ለሰዎች እንክብካቤ ስናደርግ ሰዎች መልሰው ይንከቡናል።"












