በቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠው ወጣት ለፖሊስ እየተባበረ አይደለም ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የፖለቲካ ተሟጋች የሆነው ቻርሊ ከርክ ተጠርጣሪ ገዳይ ለፖሊስ ትብብር እያደረገ አለመሆኑን እና ግድያውን ስለመፈፀሙ እስካሁን አለማመኑን ዩታህ ግዛት አስተዳዳሪ ስፔንሰር ኮክስ አስታወቁ።
ታይለር ሮቢንሰን የተባለው የ22 ዓመት ወጣት የቀኝ ዘመም ፖለቲካ ተሟጋች በሆነው ቻርሊ ከርክ ግድያ ተጠርጥሮ ግድያው ከተፈፀመ ከ33 ሰዓታት በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።
የዩታህ ግዛት አስተዳዳሪ ከኤቢሲ ኒውስ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በግድያው ምርመራ የተጠርጣሪው የቅርብ ሰዎች ከአካባቢው ባለሥልጣናት ጋር እየተባበሩ ነው ብለዋል።
በበርካታ መገናኛ ብዙኃን እሁድ ዕለት የቀረቡት ስፔንሰር ኮክስ ከ31 ዓመቱ ተሟጋች ግድያ በኋላ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች እየወጡ ያሉ መልዕክቶች እንዳሳሰቧቸው አፅንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ገዥው ኒው ዮርክ ታይምስ ተጠርጣሪው ከግድያው በኋላ በመልዕክት መላኪያ መድረክ ከሰዎች ጋር መነጋገሩን እና ጥቃቱን ስለመፈፀሙ በቀልድ መልክ መናገሩን መዘገቡን በሚመለከት ተጠይቀዋል።
"ያረጋገጥነው ሁሉም ነገር እነዚህ ንግግሮች በእርግጠኝነት መደረጋቸውን እና [ተጠርጣሪው] እርሱ ስለመሆኑ እንዳላመኑት ነው።
"ራሱ መሆኑን እስኪገልፅ ድረስ ቀልድ ነበር" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
ታይለር ሮቢንሰን ባለፈው ሐሙስ ምሽት ለፖሊስ እጁን ከሰጠ በኋላ በቁጥጥር ስር ውሏል።
ቻርሊ ከርክ ከሌሎች ጋር በጥምረት በመሰረተው 'ተርኒንግ ፖይንት ዩኤስኤ' በተባለው ድርጅቱ በዩታህ ቫሊ ዩኒቨርስቲ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ንግግር እያደረገ እያለ ነበር በጥይት ተመትቶ ሕይወቱ ያለፈው።
የግዛቱ አስተዳዳሪ ኮክስ ከዚህ ቀደም ለዎል ስትሪት ጆርናል የዩታህ ግዛት ተወላጅ የሆነው ታይለር "በግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም አስተሳሰብ በጥልቀት የሰረፀበት" ነው ብለው ነበር።
ይህን በተመለከተ በሲኤንኤን የተጠየቁት ገዢው መረጃውን ከተጠርጣሪው ጓደኞች እና ቤተሰቦች ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል።
"በጣም ብዙ እያወቅነው ያለ ነገር አለ፤ እና በቀጣይም ብዙ የምናውቀው ይኖራል" ብለዋል።
"የተለያዩ ሰዎችን እየጠየቅን ነው፤ ሁሉም የሚያውቁትን ሰዎች እና የጥቃቱ ምክንያት ምን እንደሆነ ለማወቅ እየሞከርን ነው" ሲሉም አክለዋል።
ግድያውን ተከትሎ የዩታህ ግዛት አስተዳዳሪ ስፔንሰር ኮክስ ለአንድነት ጥሪ ሲያቀርቡ እና የፖለቲካው ውጥረት እንዲረግብ ሲወተውቱ የቆዩ ሲሆን፤ በማኅበራዊ የትስስር ገፆች የሚሰራጩ አስተያየቶችንም በተደጋጋሚ ተችተዋል።
በቻርሊ ከርክ ላይ የተፈፀመውን ግድያ "በአሜሪካ ላይ የተፈፀመ ጥቃት" ሲሉ የገለፁት ገዢው፤ አሜሪካውያን ራሳቸውን በመስታወት አይተው ነገሮችን ለማሻሻል ወይስ ለማባባስ እየሞከርን ነው የሚለውን መወሰን አለባቸው ብለዋል።
ቻርሊ ከርክ በአሜሪካ ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ የሆነ ተሟጋች የነበረ ሲሆን ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቅርብ አጋር ነበር።
'ተርኒንግ ፖይንት ዩኤስኤ' የተባለው ድርጅቱ ለዘብተኛ የትምህርት ስርዓት አላቸው በተባሉ የአሜሪካ ኮሌጆች የወግ አጥባቂ አስተሳሰቦችን በማሰራጨት እና ወጣቶች ዶናልድ ትራምፕን እንዲመርጡ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።
ከርክ የጦር መሳሪያ የመታጠቅ መብት ብርቱ ደጋፊ እና የፅንስ ማቋረጥ እና የፆታ ቅየራ ተቃዋሚ የነበረ ሲሆን፤ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ላይ የተሳሳቱ መረጃዎችን በማሰራጨትም ይታወቃል።















