የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሎስ አንጀለስ የኢምግሬሽን መኮንኖች ያለገደብ ፍተሻ እንዲያደርጉ ፈቀደ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፌደራል ዳኞች በሎስ አንጀለስ ከተማ የኢምግሬሽን መኮንኖች "ያለ ምክንያታዊ ጥርጣሬ" ፍተሻ እንዳያደርጉ ጥሎት የነበረውን እግድ አንስቷል።
የሰኞው የፍርድ ቤት ብይን ሕገ ወጥ ስደተኞችን ለማባረር ወጥኖ የተነሳውን የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር አሸናፊ ያደረገ ነው።
ወግ አጥባዊዎች አብላጫ ድምፅ በያዙበት ጠቅላይ ፍርድ ቤት የኢምግሬሽን መኮንኖች በዘር፣ በቋንቋ ወይንም ሥራን መሰረት አድርገው ፍተሻ እንዲያደርጉ 6 ለ 3 በሆነ ድምፅ ወስኗል።
ለዘብተኛ የሆኑ ዳኞች በበኩላቸው ውሳኔው ሕገ መንግሥታዊ ነፃነትን አደጋ ላይ የሚጥል ነው ብለዋል።
ወግ አጥባቂ ዳኛ የሆኑት ብሬት ካቫኖ ውሳኔው ላይ ባሳፈሩት ጽሑፍ የታችኛው ፍርድ ቤት የኢምግሬሽን እና የጉሙሩክ አስከባሪ መኮንኖች ተጠርጣሪ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በሚመለከት ፍተሻቸውን እንዴት ማከናወን እንዳለባቸው መገደብ ከአቅሙ በላይ ነው ብለዋል።
"በግልፅ ለመናገር የዘር ማንነት ብቻውን ለጥርጣሬ ምክንያት አይሆንም" ያሉት ዳኛው፤ "ነገር ግን ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተጨባጭ ጥርጣሬ የሚያሳድር ሊሆን ይችላል" ሲሉ በብይኑ ላይ አስፍረዋል።
ሦስቱ ለዘብተኛ ዳኞች በዳኛ ሶኒያ ሶቶሜየር ተወክለው ጠንካራ ተቃውሞ አሰምተዋል።
"በሎስ አንጀለስ ተቆጥረው የማያልቁ ሰዎች ታፍሰው፤ መሬት ላይ ተጥለው፣ በቆዳ ቀለማቸው ብቻ፣ በአነጋገር ዘያቸው ብቻ እና በጉልበት ሥራ በመሰማራታቸው ብቻ እጃቸውን በካቴና ታስረዋል" በማለት ውሳኔውን ተችተዋል።
ዋይት ሐውስ ውሳኔን በመልካም የተቀበለው ሲሆን፤ ባወጣው መግለጫ ሕገ ወጥ ስደተኞችን በቁጥጥር ስር አውሎ ለማባረር የተሰጠውን ኃላፊነት መወጣቱን እንደሚቀጥል ገልጿል።
ዲሞክራት የሆኑት የሎስ አንጀለስ ከተማ ከንቲባ ካረን ባስ እና የካልፎርኒያ ግዛት ገዥ ጋቨን ኒውሰም ውሳኔውን ተቃውመውታል።
ከንቲባ ባስ ባወጡት መግለጫ "የዛሬው ውሳኔ አደገኛ ብቻ አይደለም፤ ፀረ አሜሪካ እና በዩናይትድ ስቴትስ የግለሰብ ነፃነትን ስጋት ላይ የጣለ ነው" ብለዋል።
ጋቨን ኒውሰም በበኩላቸው "የትራምፕ የግል የፖሊስ ኃይል ቤተሰባችሁን ለማሳደድ ፈቃድ አግኝቷል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ያነሳው በሎስ አንጀለስ ዳኛ ማም ኢ ፍሪምፖንግ የኢምግሬሽን ፍተሻዎች የአሜሪካን ሕገ መንግሥት የሚጥስ ለመሆኑ ግዙፍ ማስረጃ አለ በማለት የወሰኑትን ውሳኔ ነው።
ይህ ውሳኔ ፍተሻዎችን የገታ ሲሆን ዳኛዋ የትራምፕ አስተዳደር በግልፅ የዘር ወይም የብሔር አሊያም ስፓኒሽ ቋንቋ የሚናገሩ ግለሰቦችን ለማስቆም እና ጥያቄ ለመጠየቅ ብቸኛ ምክንያት ማድረግ አይችልም ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢምግሬሽን መኮንኖች እንደ አውቶብስ መቆሚያ ባሉ ግለሰቦች በሚታዩባቸው ስፍራዎች ወይም በሚሰሩት ሥራ አይነት በመጠርጠር ፍተሻ እንዳያደርጉ እግድ ጥለው ነበር።
ጊዜያው እግዱ የተጣለው የኦምግሬሽን ተሟጋች ቡድኖች ባቀረቡት አቤቱታ ሲሆን፤ ተሟጋቾች የኢምግሬሽን መኮንኖች በሎስ አንጀለስ በዘር ማንነት እየለዩ ፍተሻ ማድረጋቸውን እና ከጠበቃ ጋር እንዳይገናኙ መከልከላቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የአገር ውስጥ ደኅንት መስሪያ ቤት ጠበቆች በበኩላቸው የኢምግሬሽን መኮንኖች ፍለሻ የሚያካሂዱት ግለሰቦችን በቆዳ ቀለማቸው፣ በዘራቸው አሊያም በብሔራቸው ሳይሆን በአሜሪካ ባላቸው ሕጋዊ ሁኔታን መሰረት ነው ሲሉ ተከራክረዋል።















