በቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረ የ22 ዓመት ወጣት በቤተሰቡ ጥቆማ ተያዘ

ታይለር ሮቢንሰን

የፎቶው ባለመብት, Handout

የምስሉ መግለጫ, ተጠርጣሪው ታይለር ሮቢንሰን በፖሊስ የተነሳው ፎቶ

በታዋቂው አሜሪካዊ ወግ አጥባቂ አክቲቪስት ቻርሊ ከርክ ግድያ የተጠረጠረ አንድ ወጣት በደኅንነት ሰዎች ቁጥጥር ስር መዋሉ ተገለጸ።

የፕሬዝዳንት ትራምፕ ወዳጅ በሆነው ቻርሊ ከርክ ላይ የተፈጸመው ግድያ በመላዋ አሜሪካ ድንጋጤን ፈጥሮ አስካሁን ድረስ ዋነኛ የመነጋገሪያ ርዕስ ሆኗል።

በዩታህ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ዩኒቨርስቲ ግቢ ውስጥ ለተማሪዎች ንግግር እያደረገ እንዳለ በተተኮሰበት ጥይት የተገደለው ከርክ በሃይማኖታዊ አቋሙ እና በፖለቲካ ተሳትፎው ከፍተኛ ዝናን ያገኘ ወጣት ነው።

ጥቃቱን የፈጸመውን ግለሰብ ለመያዝ ፖሊስ አና የአሜሪካ የደኅንነት ተቋማት ከፍተኛ አሰሳ ሲያደርጉ ቆየተወ ዛሬ አርብ በግድያው የተጠረጠረው ሰው በቁጥጥር ስር መዋሉን ይፋ አድርገዋል።

በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኘው የግድያው ተጠርጣሪ ታይለር ሮቢንሰን የተባለ የ22 ዓመት ወጣት መሆኑን እና በቤተሰቦቹ ጥቆማ መያዙ ተገልጿል።

ኤፍቢአይ ጉዳዩን ይፋ ለማድረግ በጠራው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የዩታህ ግዛት አገረ ገዢ ስፔንሰር ኮክስ "አግኝተነዋል" ሲሉ ተጠርጣሪው በቁጥጥር ስር መዋሉን አሳውቀዋል።

ታይለር ሮቢንሰን ሊያዝ የቻለው ጥቃቱን መፈጸሙን ወይም ያንን የሚያመለክት ነገር መናገሩን በመጥቀስ የቤተሰቡ አባል ለአንድ ወዳጁ ካሳወቀ በኋላ ይህ መረጃ ለፖሊስ እንዲደርስ በመደረጉ ነው።

ተጠርጣሪው ወጣት በተያዘበት ጊዜ በደኅንነት ካሜራ ተይዞ በተሠራጨው ቪዲዮ ላይ የሚታየው ዓይነት ልብስ ለብሶ እንደነበር ተገልጿል።

ተጠርጣሪው ታይለር ሮቢንሰን ግድያው በተፈጸመበት የዩታህ ቫሊ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ያልነበረ ሲሆን፣ ከአእምሮ ጤና ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለበት የሚያመለክት ምንም ዓይነት መረጃ እንደሌለ ስፔንሰር ኮክስ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አሳውቀዋል።

ሮቢንሰን ጥቃቱ ከተፈጸመበት ዩኒቨርስቲ ሦስት ሰዓት መንገድ ርቆ በሚገኘው በደቡብ ምሥራቅ ዩታህ ክፍል ውስጥ ከቤተሰቦቹ ጋር እንደሚኖር ተነግሯል።

የግዛቲቱ አገረ ገዢ ኮክስ በተጠርጣሪው ላይ የክስ ሰነዶች በሚቀጥለው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ይቀርባሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አሳውቀዋል።