ደቡብ ኮርያ በሃዩንዳይ ፋብሪካ በኢሚግሬሽን የተያዙ ዜጎቿን ለማስፈታት ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ ደረሰች

በቁጥጥር ስር የዋሉ ሰራተኞች ፊታቸውን ወደ አዙረው እጃቸው መኪና ላይ በመዘርጋት ቆመው

የፎቶው ባለመብት, EPA/US Immigration and Customs Enforcement handout

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት፤ በጆርጂያ በሚገኘው የሃዩንዳይ ፋብሪካ ላይ በተካሄደ ግዙፍ የኢሚግሬሽን ዘመቻ የተያዙ ዜጎቹን ለማስለቀቅ ከአሜሪካ ጋር ስምምነት ላይ መድረሱን አስታወቀ።

የደቡብ ኮሪያ ፕሬዝዳንት የጽህፈት ቤት ኃላፊ፤ የአስተዳደር ሂደቶች ከተጠናቀቁ ታሳሪዎቹን ወደ ቤታቸው ለማምጣት ቻርተር አውሮፕላን ወደ አሜሪካ እንደሚላክ ተናግረዋል።

የጽህፈት ቤት ኃላፊው ካንግ ሁን ሲክ፤ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ወደፊቱ እንደዚህ አይነት ክስተቶችን እንዳይፈጠሩ ለመከላከል የቪዛ ሥርዓቱን ለማሻሻል እየሞከሩ መሆኑን ገልጸዋል።

ደቡብ ኮርያ እዚህ ስምምነት ላይ የደረሰችው፤ የአሜሪካ ባለስልጣናት በሀገሪቱ ከሚገኙ ግዙፍ የውጭ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች አንዱ በሆነው የሀዩንዳይ የመኪና ማምረቻ ውስጥ በህገወጥ መንገድ ሲሠሩ ተገኝተዋል ያሏቸውን ሰዎች በቁጥጥር ስር ካዋሉ በኋላ ነው።

በአሜሪካ የጸጥታ ኃይሎች ከተያዙት 475 ሰዎች መካከል ከ300 በላይ የሚሆኑት የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ናቸው።

ሰኞ ዕለት የደቡብ ኮሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቾ ሂያን ወደ አሜሪካ እንደሚጓዙ የሁለቱም አገራት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

ዋይት ሀውስ፤ በሃዩንዳይ ፋብሪካ ላይ የተፈጸመው የጸጥታ አካላት ዘመቻ የውጭ ኢንቨስትመንት እንዲቋረጥ ሊያደርግ ይችላል በሚል የቀረበውን ወቀሳ ውድቅ በማድረግ እርምጃውን ተከላክሏል።

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማህበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ፅሁፍ፤ የውጭ ኩባንያዎች አሜሪካውያንን እንዲቀጥሩ ጥሪ አቅርበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ትራምፕ እሁድ ዕለት በለጠፉት ጽሁፍ፤ "አሜሪካ ውስጥ ኢንቨስት የሚያደርጉ ሁሉም የውጭ ኩባንያዎች የሀገራችንን የኢሚግሬሽን ህጎች እንዲያከብሩ እጠይቃለሁ" ብለዋል።

አሜሪካ፤ የውጭ ኩባንያዎች "ታላላቅ የቴክኒክ ባለተሰጥኦዎቻቸውን" በህጋዊ መንገድ የሚያመጡበትን ሂደት ቀላል እንደሚያደርግ ተናግረዋል። ነገር ግን በምላሹ እነዚህ ኩባንያዎች "አሜሪካዊ ሠራተኞችን ይቀጥራሉ፣ ያሰለጥናሉ" ብለዋል።

በወረራው ወቅት ስለነበረው ሁኔታ ለቢቢሲ የተናገረ አንድ የፋብሪካው ሠራተኛ፤ ከተያዙት ሠራተኞች አብዛኛዎቹ በኮንትራክተር የተቀጠሩ ሜካኒኮች እንደሆኑ ገልጿል።

በቁጥጥር ሥር ከዋሉት መካከል ጥቂቶቹ ከሴኡል ዋና መስሪያ ቤት ተልከው ስልጠና በመስጠት ላይ የነበረ እንደሆኑም ተናግሯል። ይሁን እንጂ ቢቢሲ ይህንን ማረጋገጥ አልቻለም።

በትራምፕ አስተዳደር የድንበር ጠባቂ መስሪያ ቤት ኃላፊ የሆኑት ቶም ሆማን እሁድ ዕለት በተካሄደው የሲኤንኤን 'ስቴት ኦፍ ዘ ዩኒየን' ላይ ባደረጉት ንግግር ፋብሪካው ላይ እንደተካሄደው አይነት የኢሚግሬሽን ዘመቻዎች በስፋት ሊደረጉ እንደሚችሉ ገልጸዋል።

"በሥራ ቦታ ላይ የሚካሄዱ ተጨማሪ የህግ ማስከበር ስራዎችን እናከናውናለን" ብለዋል።

"ከልብ በሚመነጭ በጎነት ህገ ወጥ ስደተኛን የሚቀጥር አንድም ሰው የለም። የሚቀጥሯቸው የበለጠ እንዲሠሩላቸው፣ አነስተኛ [ገንዘብ] ስለሚከፍሏቸው፣ የአሜሪካ ዜጋ ሠራተኞችን የሚቀጥርበትን ውድድር ለማዳከም ስለሚችሉ ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።

በኢሚግሬሽን ጉምሩክ ማስከበር መስሪያ ቤት ባለሥልጣናት የተለቀቀ አንድ ቪዲዮ፤ ከህንጻ ፊት ለፊት በሰንሰለት የታሰሩ እስያውያን ሠራተኞችን ያሳያል። ከእነዚህ ውስጥ አንዳንዶቹ "ሃዩንዳይ" እና "ኤልጂ ሲኤንኤስ" የሚሉ ስሞች የተጻፉባቸው ቢጫ ሰደርያዎችን ለብሰዋል።

መስሪያ ቤቱ፤ "የአጭር ጊዜ ወይም የመዝናኛ ቪዛ ያላቸው ሰዎች አሜሪካ ውስጥ እንዲሰሩ አልተፈቀደላቸውም" ያለ ሲሆን ዘመቻው የአሜሪካውያን ሥራዎችን ለመጠበቅ አስፈላጊ እንደሆነ አክሏል።

የሀገር ውስጥ ደኅንነት ምርመራ ልዩ ወኪል የሆኑት ስቲቨን ሽራንክ ቅዳሜ ዕለት በሰጡት መግለጫ፤ "ይህ ዘመቻ ሥርዓቱን በሚበዘብዙ እና የሠራተኞቻችንን ኃይል የሚያዳክሙ ተጠያቂ እንደሚሆኑ ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል" ብለዋል።

የአሜሪካ የቅርብ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ፤ በዋሽንግተን የማኑፋክቸሪንግ ኢንቨስትመንት ላይ በአስር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ለማፍሰስ ቃል ገብታለች።

ይህንን ቃል የገባችበት አንዱ ምክያትን የፕሬዝዳንት ትራምፕ ታሪፍ የሚያስከትለውን ተጽዕኖ በከፊል ለመከላከል ነው።

የሁለቱ አገራት መንግሥታት ሚስጥራዊ የንግድ ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት የተካሄደው የፋብሪካው ዘመቻ፤ ሴኡል ውስጥ ስጋት ፈጥሯል።