አሜሪካ ቀደም ሲል ቪዛ በሰጠቻቸው 55 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ምርመራ እያደረገች ነው

 ማርኮ ሩቢዮ ጥቁር ኮት ለብሰው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በአሜሪካ ቪዛ አሰጣጥ ላይ ተከታታይ እርምጃዎችን እየወሰዱ ያሉት የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ

የአሜሪካ መንግሥት ከ55 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካ ቪዛ ያላቸው ሰዎች ወደ አገሪቱ ለመግባት ወይም ለመቆየት የተቀመጡ ቅድመ ሁኔታዎችን ጥሰው ከሆነ በሚል ሰነዶችን እየመረመረ መሆኑ ተገለጸ።

የአሜሪካ ቪዛ ያገኙ ሰዎች "ቀጣይነት ያለው የማጣራት ሥራ" እንደሚካሄድባቸው የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ለአሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ እንዳሉት "ከተፈቀደው ጊዜ በላይ መቆየትን፣ የወንጀል ድርጊትን፣ የሕዝብ ደኅንነትን አደጋ ላይ የመጣል ስጋትን፣ በማንኛውም ዓይነት የሽብር ተግባር ውስጥ መገኘትን ወይም ለአሸባሪ ድርጅቶች ድጋፍ መስጠትን የሚጠቁሙ ምልክቶች ካሉ ቪዛው ይሰረዛል።"

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የፀረ ስደተኝነት አቋማቸውን የሁለተኛው ዙር የሥልጣን ዘመናቸው ዋነኛ አጀንዳ በማድረግ፤ አስካሁን ሕገወጥ ያሏቸውን ስደተኞች በጅምላ ማባረር፣ በአገራት ላይ የጉዞ እገዳ መጣል እና 6,000 የሚደርሱ የተማሪዎች ቪዛን የመሰረዝ እርምጃ ወስደዋል።

ወደ አሜሪካ በሚመጡ ተማሪዎች እና ጎብኚዎች ላይ "ለአገሪቱ ዜጎች፣ ባህል፣ መንግሥት፣ ተቋማት ወይም ዩናይትድ ስቴትስ በተመሠረተችበት መርሆች ላይ የጥላቻ ምልክቶችን" የሚመረምሩ ባለሥልጣናት በቪዛ ጠያቂዎች የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ ማጣራት ይካሂዳሉ።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ሠራተኞች "የውጭ አገር አሸባሪዎችን የሚደግፉ፣ ወይም የተፈረጁ አሸባሪዎችን እና የብሔራዊ ደኅንነት ስጋቶችን የሚደግፉ፣ ወይም ሕገ-ወጥ የፀረ ሴማዊነት ትንኮሳ ወይም ጥቃት የሚፈጽሙ" ግለሰቦችን እንዲለዩ ታዝዘዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የዜግነት እና የኢሚግሬሽን አገልግሎት ቃል አቀባይ ማቲው ትራጄሰር በሰጡት መግለጫ "አገሪቱን የሚጠሉ እና ፀረ አሜሪካ ርዕየተ ዓለምን የሚራመዱ ሰዎች ከአሜሪካ ከምትሰጠው ጥቅም ተጋሪ ሊሆኑ አይገባም" ብለዋል።

ባለሥልጣኑ አክለውም የኢሚግሬሽን አገልግሎት ክፍሉ "ፀረ አሜሪካዊነትን ለማስወገድ የተቀመጡ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ለማድረግ" ቁርጠኛ መሆኑን ተናግረዋል ።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ ቀደም ሲል በተሰጡ ቪዛዎች ላይ ምርመራ የማካሄዱ ውሳኔ ይፋ የሆነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ማርኮ ሩቢዮ ዩናይትድ ስቴትስ ለከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የምትሰጠው የሠራተኛ ቪዛን "በአስቸኳይ" እንደምታቆም መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

"በአሜሪካ መንገዶች ላይ ከባድ መኪኖችን የሚያሽረክሩ የውጭ አገር ሹፌሮች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱ የአሜሪካውያንን ሕይወት አደጋ ላይ የሚጥል እና የአሜሪካውያን አሽከርካሪዎችን መተዳደሪያ እያሳጣ ነው" ሲል ሩቢዮ ሐሙስ ዕለት በኤክስ ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።

ትራምፕ ሥልጣን ከያዙ ከጥር ወር ጀምሮ በአሜሪካ የሚደገፈውን እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የምታደርገውን ጦርነት በመቃወም በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ የተሳተፉ በርካታ የውጭ አገራት ተማሪዎች ከአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ ግቢዎች ተይዘው ታስረዋል።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ደግሞ ወደ አሜሪካ ለመግባት ቪዛ የሚጠይቁ የማላዊ እና የዛምቢያ ዜጎች ለቱሪስት ወይም ለቢዝነስ ቪዛ 15,000 ዶላር ቅድሚያ ማስያዝ እንደሚጠበቅባቸው አስታውቃለች።

ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ ከ12 አገራት የሚመጡ ዜጎች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ ክልከላ ያጣሉ ሲሆን፣ በሌሎች ሰባት አገራት ላይ ደግሞ ከፊል እገዳ ጥለዋል።

በተጨማሪም ለበርካታ አገራት ዜጎች የሚሰጠው የአሜሪካ መግቢያ ቪዛ የአገልግሎት ጊዜ ወደ ሦስት ወራት እንዲያጥር ተደርጓል።

ባለፈው ግንቦት ወር የትራምፕ አስተዳደር በአሜሪካ የሚኖሩ ከ500 ሺህ በላይ ስደተኞች የሕጋዊነት ፈቃድን በጊዜያዊነት እንዲሰርዝ ተፈቅዶለታል።

እንዲሁም ፕሬዝዳነቱ በአሜሪካ ውስጥ በመወለድ የአገሪቱ ዜጋ መሆን የሚያስችለውን ድንጋጌ እንደሚያስቀሩ በተደጋጋሚ ከመናገራቸው በተጨማሪ ጥረት እያደረጉ ነው።