የደቡብ ኮሪያ መንግሥት በትራምፕ አስተዳደር የታሰሩበትን ዜጎቹን በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ አደረገ

የአይስ ባልደቦች በሥራ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የአይስ ፖሊሶች በሃዩንዳይ ባትሪ ማምረቻ፣ ጆርጂያ አሜሪካ

የትራምፕ አስተዳር በመቶ የሚቆጠሩ የደቡብ ኮሪያ ዜጎችን በቁጥጥር ሥር መዋሉን ተከትሎ የደቡብ ኮሪያ መንግሥት አስቸኳይ ስብሰባ አደረገ።

የትራምፕ አስተዳደር የደቡብ ኮሪያዊያኑ እስር በሕገ ወጥ ስደተኞች ላይ እያደረገ ያለው ዘመቻ አካል ነው ብሏል።

በዚህም በሃዩንዳይ ባትሪ ፋብሪካ ይሠሩ የነበሩ 475 ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል። ከነዚህ ብዙዎቹ የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ናቸው።

የደቡብ ኮሪያ መንግሥት ድርጊቱን ያወገዘ ሲሆን ለዜጎቹ ጥብቅና እንደሚቆም አስታውቋል።

በጉዳዩ ዙርያ ለመነጋገር ዲፕሎማቶችን ወደ ጆርጂያ ግዛት ልኳል።

ዋይት ሐውስ ድርጊቱ ሕገወጥ ስደተኞችን ለማደን የተደረገ ነው፤ የውጭ ኢንቨስትመንትን የሚጎዳ ድርጊት አይደለም ሲል ተከላክሏል።

ዶናልድ ትራምፕ ዐርብ ዕለት እንደተናገሩት በምሕጻሩ አይስ (ICE) ተብሎ የሚጠራው የስደተⶉችና ጉምሩክ ጉዳዮች ግብረ ኃይል "ሥራውን እየሠራ ነው፤ሰዎቹም ሕገ ወጥ ስደተኞች ነበሩ" ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያ የሚሰራጩ ተንቀሳቃሽ ምሥሎች አይስ ደቡብ ኮሪያዊያኑ የኩባንያቸው የኤልጂ እና የሃዩንዳይ አርማዎች ያሉባቸውንቢጫ የሥራ ልብሳቸውን ለብሰው፣ የፊጢኝ እያሰረ ወደ ፖሊስ መኪና ሲያግዛቸው ይታያል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ይህ ኦፕሬሽን የቪዛ ሥርዓትን የሚበዘብዙ እና የአሜሪካዊያኑን ሥራ የሚቀሙ ሰዎች በሕግ እንደሚጠየቁ ግልፅ መልእክት ያስተላልፋል" ሲል የሀገር ውስጥ ደኅንነት ምርመራ ቢሮ ባልደረባ ስቲቨን ሽራንክ ቅዳሜ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።

'አይስ' በበኩሉ በጉዳዩ ዙርያ እንዳለው የውጭ ዜጎች በጎብኚ ቪዛ ወይም የአጭር ጊዜ ቆይታ ቪዛ ይዘው ሥራ መሥራት አይችሉም፤ "ይህም የአሜሪካውያንን የሥራ ዕድል ለመከላከል የሚደረግ ጥረት ነው። "

የአሜሪካ ሁነኛ አጋር የሆነችው ደቡብ ኮሪያ በአሜሪካ ምድር በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ኢንቨስትመንት ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር።

ይህም ትራምፕ በየአገሩ እየጣሉ ያሉትን የታሪፍ ቅጣት ለማለሳለስ የተደረገ እንደሆነ ይታመናል።

የደቡብ ኮሪያዊያኑ ሠራተኞች በቁጥጥር ሥር መዋል ደቡብ ኮሪያና አሜሪካ በንግድ ዙርያ ውይይት እያደረጉ ባለበት ወቅት መሆኑ በተለይ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣናትን አሳስቧል።

ዜጎቹን ለማስለቀቅ ማንኛውንም አስፈላጊ ጥረት ከማድረግ አንቆጠብም ብለዋል ባለሥልጣናቱ።

የኤልጂ ኢነርጂ ሶሉሽን ዋና የሰው ኃይል ሥራ አስኪያጅ ኪም ኪ ሱ እሑድ ወደ ጆርጂያ እንደሚጓዙ ታውቋል።

ኩባንያው ወደ አሜሪካ የሚደረጉትን አብዛኛዎቹን የንግድ ጉዞዎች እያቆመ መሆኑና ሠራተኞቹ በአሜሪካ ለሥራ በተመደቡበት ጊዜ አጠናቀው ወደ ደቡብ ኮሪያ እንዲመለሱ አሳስቧል።

ይህ በጆርጂያ ግዛት የሚገኘው የኤሌክትሪክ መኪና ፋብሪካ ለ1200 ሰዎች የሥራ ዕድል በመፍጠሩ በግዛቲቱ እንደራሴዎች ሲሞካሽ የነበረ ነው።

የታሰሩት ደቡብ ኮሪያዊያኑ እጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ለጊዜው የተወሰነ ውሳኔ የለም።

"ከድርጅታችን እና ከአጋር ድርጅቶች የታሰሩ ግለሰቦችን በፍጥነት እንዲፈቱ ሁሉንም ጥረቶችን እያደረግን ነው" ብሏል የደቡብ ኮሪያ መንግሥት መግለጫ።

የደቡብ ኮሪያ መገናኛ ብዙኃን እስሩን "አስደንጋጭ" ሲሉ በሰፊው የገለጹ ሲሆን ዶንግ-ኤ ኢልቦ የተባለው ጋዜጣ "በዩናይትድ ስቴትስ ባሉ የንግድ ድርጅቶቻችን እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል" ሲል አስጠንቅቋል።

አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን የሚያመርተው ፋብሪካው በጆርጂያ ሪፐብሊካኑ ገዥ በግዛቱ ታሪክ ትልቁ የኢኮኖሚ ልማት ፕሮጀክት ተብሎ ተወድሶ ነበር።