ዓለም ዋንጫ፡ በሜሲ ድንቅ ጎል ታግዛ አርጀንቲና ወደ ድል ተመለሰች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሜሲ የተለመደበትን ድንቅ ብቃት አሳይቶ ጎል ባስቆጠረበት ምሽት አርጀንቲና ከፍተኛ ውጥረት የነበረበትን ጨዋታ በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ዕድሏን አለምልማለች።
በሳዑዲ አረቢያ ከደረሰባት አስደንጋጭ ሽንፈት በኋላ አርጀንቲና ሌላ ሽንፈት ቢያጋጥማት ከጥሎ ማለፉ ውጭ መሆኗን ታረጋግጥ ነበር።
ሜክሲኮዎች በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ ሜሲን እና ጓደኞቹ ተጭነው ለመጫወት ችለዋል።
ሜሲ በ64ኛው ደቂቃ ያገኛትን የግብ ዕድል ተጠቅሞ በተዓምረኛ ግራ እግሩ ኳሷን ጉሌርሞ ኦቾአ መረብ ላይ አሳርፏል።
ሜሲ በተለይም በመጀመሪያው አጋማሽ በጨዋታው ውስጥ ያለው ተሳትፎ ዝቅ ብሎ ነበር።
ሃይል የተቀላቀለበት ጨዋታ መረጋጋት ሲጀመር አጥቂው ተጽዕኖውን ማሳየቱን የጀመረው።
ኤንዞ ፈርናንዴዝ ጨዋታው መገባደጃ ላይ ለቡድኑ እፎይታ የሰጠች ጎል አስቆጥሯል።
አርጀንቲና ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን ለማረጋገጥ ከፖላንድ ጋር ጠንካራ ፍልሚያ ይጠብቃታል።
በሌላ የምድቡ ጨዋታ ፖላንድ ሳዑዲ አረቢያን በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር የማለፍ ተስፋዋን አሳድጋለች።
ጨዋታው በፖላንድ 2 ለ 0 አሰናፊነት ተጠናቋል።
ፒዮትር ዚየለንስኪ በመጀመሪያው አጋማሽ ፖላንድ ቀዳሚ ማድረግ ቻለ።
በሁለተኛው አጋማሽ የሳዑዲ ተጫዋቾች የሰሩትን ስህተት ተጠቅሞ አምበሉ ሮበርት ሌዋንዶꬅውስኪ ሁለተኛ ኳስ ከመረብ ላይ አሳረፈ።
ይህቺ ጎል ለጎል ቀበኛው ሌዋንዶውስኪ የመጀመሪያ የዓለም ዋንጫ ጎሉ ሆና ተመዝግባለች።
የፖላንዱ አጥቂ ከጎሏ በኋላ ደስታውን በእንባ ታጅቦ ገልጿል።
ሳዑዲዎች ያገኙትን ፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጎል መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል።
ከሁለት ጨዋታ በኋላ ፖላንድ ምድብ ሦስትን በአራት ነጥብ መምራት ጀምራለች።
አርጀንቲና እና ሳዑዲ አረቢያ በእኩል ሦስት ነጥብ ሁለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃን ይዘዋል።
በሚቀጥለው ሳምንት የሚደረጉ የምድቡ የመጨረሻ ጨዋታዎች ወደ ቀጣዩ ዙር የሚያልፉ ሃገራትን ይለያል።
በምድብ ሦስት ደግሞ ፈረንሳይ ዴንማርክን በማሸነፍ ለጥሎ ማለፉ መብቃቷን አረጋግጣለች።
ፈረንሳይ ዴንማርክን 2 ለ 1 በማሸነፍ ነው ሦስት ነጥብ ያሳካችው።
ክሊያን ምባፔ የሰማያዊዎቹን ሁለት ጎሎች ከመረብ ማሳረፍ ችሏል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ እስከ 61ኛው ደቂቃ ድረስ ጎል አላስተናገደም።
ምባፔ በ61ኛው ደቂቃ ፈረንሳይ ቀዳሚ አደረገ።
አንድሪያስ ክርስቲያንሰን ከሰባት ደቂቃዎች በኋላ ዴንማርክን አቻ ማድረግ ቻለ።
ጨዋታው በዚህ ውጤት ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ ሲጠበቅ ምባፔ በ86ኛው ደቂቃ ሁለተኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፎ ቡድኑን አሸናፊ ማድርግ ችሏል።
በሌላ የምድቡ ጨዋታ ቱኒዝያ አውስትራሊያ ተሸንፋለች።
ሚቼል ዱክ ብቸኛዋን ጎል ከመረብ አሳርፏል።
በበርካታ ደጋፊዎች ታጅባ ወደ ሜዳ የገባችው ቱኒዝያው ውጤቱን መቀልበስ ሳትችል ቀርታለች።
ከዚህኛው ምድብ ፈረንሳይ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፏን አረጋግጣለች።
አውስትራሊያ በሦስት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዛለች።
ዴንማርክ እና ቱኒዝያ አንድ አንድ ነጥብ አላቸው።
ፈረንሳይ ከቱኒዝያ እና ዴንማርክ ከአውስትራሊያ በሚያደርጉት ጨዋታ የምድቡ ሁለተኛ አላፊ ቡድን ይለያል።
የዓለም ዋንጫው ዛሬም ቀጥሎ ይከናወናል።
ዛሬ የምድብ አምስት እና የምድብ ስድስት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
ጃፓን ከኮስታሪካ በሚያደርጉት ጨዋታ የምድብ አምስት ጨዋታ ውድድሩ ይቀጥላል።
ስፔን ከጀርመን የሚያድርጉት የምድቡ ሌላኛው ጨዋታ በጣም ተጠባቂ ነው።
ጀርመን ጨዋታውን ከተሸነፈች ከምድቡ መውደቋን ታረጋግጣለች።
በምድብ ስድስት ደግሞ ቤልጂየም ከሞሮኮ እና ክሮሽያ ከካናዳ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ።












