የተመድ ጠቅላላ ጉባኤ የፍልስጤምን አባልነት የሚደግፍ ውሳኔ አሳለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ፍልስጤምን 194ኛ የድርጅቱ አባል ለማድረግ የቀረበውን የድጋፍ የውሳኔ ኃሳብ በከፍተኛ ድምጽ አሳለፈ።
ጠቅላላ ጉባኤው የመጨረሻውን የአባልነት ጥያቄ ለሚወስነው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት የፍልስጤምን የአባልነት ጥያቄ እንደገና እንዲያጤነው ጠይቋል።
በአረብ አገራት እና በፍልስጤም የተደገፈው ይህ የውሳኔ ሃሳብ በ143 የድጋፍ ድምጽ፣ በ9 ተቃውሞ እና በ25 ድምጸ ተአቅቦ ጸድቋል።
አሜሪካን ጨምሮ እስራኤል፣ አርጀንቲና፣ ቼቺያ፣ ሃንጋሪ ፣ ማይክሮኔዥያ፣ ናኡሩ፣ ፓላው እና ፓፑዋ ኒው ጊኒ ተቃውመውታል።
ፍልስጤም ከአውሮፓውያኑ 2012 ጀምሮ የታዛቢነት ስፍራ የተሰጣት ሲሆን ይህም ሙሉ አባል አገራት በድርጅቱ ውስጥ ካላቸው መብት የተገደበ ነው።
የድርጅቱ አባልነት የሚወሰነው በተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ብቻ ነው።
አሜሪካ በቅርቡ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን በመጠቀም ጥያቄ ውድቅ ብታደርግም አርብ በነበረው የድምጽ መስጠት ይህንን መብቷን አልተጠቀመችም።
የፍልስጤም ፕሬዚዳንት ማህሙድ አባስ የውሳኔ ኃሳቡን በደስታ ተቀብለው ይህም ሁኔታ በጸጥታው ምክር ቤት ለሚወሰነው ውሳኔ ድምጽ በመሆን እንደሚደግፍ ተናግረዋል።
“ፍልስጤም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ውስጥ ሙሉ አባል ለመሆን የምታደርገውን ጥረት አጠናክራ ትቀጥላለች” ሲሉም በመግለጫቸው ተናግረዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የእስራኤል አምባሳደር ጊላድ ኤርዳን በበኩላቸው ይህንን በጽኑ በመቃወም “የሽብር መንግሥትን” መቀበል ሲሉ ፈርጀውታል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ቻርተር ቅጂ የቀዳደዱት አምባሳደሩ አገራቱ ይህንን ውሳኔውን በማሳለፋቸው ይህንን የማድረጋቸው ተምሳሌት ነው ሲሉ ከሰዋል
የተባበሩት መንግሥታት ይህንን ውሳኔ ማሳለፉ የተሰማው በርካታ የአውሮፖ አገራት ለፍልስጤም መንግሥት እውቅና ለመስጠት ማቀዳቸው እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው።
የአውሮፓ ህብረት የውጭ ፖሊሲ ኃላፊ ጆሴብ ቦሬል ስፔን በያዝነው ወር ለፍልስጤም እውቅና እንደምትሰጥ ለስፔኑ ሚዲያ አርቲቪኢ ተናግረዋል። ቀደም ሲል አየርላንድ፣ ስሎቬኒያ እና ማልታ ይህንኑ እርምጃ እንደሚወስዱ መግለጻቸው ይታወሳል።
አርብ ዕለት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ያሳለፈው ውሳኔ ለፍልስጤም ተጨማሪ መብቶችን የሚሰጥ ሲሆን ይህም በክርክሮች ላይ እንድትሳተፍ፣ አጀንዳዎች እንድታቀርብ እና ተወካዮቿ በኮሚቴነት እንዲመረጡ ያስችላቸዋል።
ነገር ግን አጠቃላይ ጉባኤው ይህ ውሳኔን ቢያሳልፍም ፍልስጤምን በአባልነት ለመቀበል በጸጥታው ምክር ቤት ድጋፍ ማግኘት ይኖርበታል።
የፍልስጤም የአገርነት ጥያቄ አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለበርካታ አስርት ዓመታት ሲያከራክር ቆይቷል።
የፍልስጤምን አገርነት ከ193 የተባበሩት መንግሥታት አባል አገራት 139ኙ እውቅና ቢሰጡትም በአብዛኛው ተምሳሌታዊ ነው።
እንደ ዌስት ባንክ ያሉ የፍልስጤም ግዛቶችን እስራኤል በኃይል ተቆጣጥራቸው የምትገኘው ሲሆን የፍልስጤም ነጻ አውጭ ድርጅት ሙሉ በሙሉ አያስተዳድርም።












