ከፕሬዝዳንት ባይደን የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዞ ምን ይጠበቃል?

ባይደን በአሁኑ ጉዟቸው እስራኤል በወረረቻቸው የፍልስጤም ክፍሎች ጉብኝት ያደርጋሉ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በመካከለኛው ምሥራቅ የሚያደርጉትን ጉዞ በወዳጅ አገር እስራኤል ጀምረው ዛሬ ረቡዕ ጠዋት ቴል አቪቭ ገብተዋል።

በተለይም በዓለማችን ኑኩሌር የታጠቁት ኃያል አገራትን ያፋጠጠው የሩሲያ እና የዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ የፕሬዝዳንቱም ሆነ የአስተዳደራቸው ትኩረት በዚሁ ጦርነት፣ በቻይና እንዲሁም በቅርቡ በሚካሄደው የአጋማሽ ዘመን ምርጫ ላይ ሆኖ ቆይቷል።

ታዲያ ይህ አንገብጋቢ ጉዳያቸው ወዳልሆነው የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዞ እንዲያደርጉ ካስገዷደቸው ምክንያቶች አንዱ በመጪውን ምርጫ ላይ ዲሞክራቶች የሚኖራቸው ውጤት በተለይ ከነዳጅ ዋጋ ጋር ስለሚያያዝ ነው።

የዩክሬኑ ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ በመላው ዓለም የናረው የነዳጅ ዋጋ የአሜሪካዊያንንም ኪስ ማናጋት ጀምሯል፤ ምንም እንኳን አሜሪካ ከውጭ የምታስገባውን የነዳጅ መጠን በመቀነስ ጥገኝነቷን ብትቀንስም።

ቻይና ዓለም አቀፍ ጫናዋ እየጨመረ በመጣበት እና የአሜሪካ ኃያልነት መቀነሱን በጉጉት በምትጠብቅበት በዚህ ወቅት፣ ባይደን በቁልፉ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያደርጉት ጉዞ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ሌሎችም እንቅፋቶች አሉበት።

በተለይም ባይደን የኦባማ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት በነበሩበት ወቅት በእስራኤል ጉዞአቸው በወቅቱ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሳይስማሙ መመለሳቸው ይታወሳል።

ይህም ባይደን እስራኤል በተቆጣጣረቻቸው የፍልስጤም አካባቢዎች የምትገነባውን የሰፈራ ሥራ እንድታቆም መጠየቃቸውን ተከትሎ ነበር። በእርግጥ ይህ የእስራኤል የሰፈራ ፕሮጀክት በዓለም አቀፍ ሕግ ተቀባይነት የለውም።

ባይደን በአሁኑ ጉዟቸው እስራኤል በወረረቻቸው የፍልስጤም ክፍሎች ጉብኝት ያደርጋሉ። ከዚያም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዝ የባሕረ ሰላጤው አገራት መሪዎች ከጆርዳን፥ ከግብፅ እና ከኢራቅ ጋር በጋራ በሚያደርጉት ጉባኤ ላይ ይሳተፋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ባይደን የፍልስጤም ነጻ መንግሥት እንዲቋቋም ብሎም የሁለት አገራት መፍትሔ በመባል የሚጠራውን መፍትሔ እንዲተገበር ጥሪ ማድረጋቸው የማይቀር ነው።

በአጠቃላይ የባይደን የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዞ አሜሪካ በቀጠናው ላይ እየቀነሰ የመጣውን ተጽዕኖዋን በድጋሚ የሚያንሰራራ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል።

ባይደን ከሳዑዲ አንድ ውለታ ይጠይቃሉ ተብሎም ይጠበቃል። ይህም የምታመርተውን ነዳጅ መጠን እንድትጨምር አና ዋጋ እንድትቀንስ።

ለዚህ ጥያቄ ይዘው የሚመለሱት መልስ እና በእያንዳንዱ በርሜል ላይ የሚደራደሯት ሳንቲም ፓርቲያቸው በሚያገኘው በእያንዳንዷ ድምጽ ላይ ጫና ይኖረዋል።

ባይደን ላይ ከአረብ አገራት ዘንድ ከሚኖሩ የጥርጣሬ ነጥቦች አንዱ አስተዳደራቸው ወደ ሥልጣን በመጣ ማግስት የጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ግድያን የተመለከተ የደኅንነት መረጃ ይፋ ማውጣቱ እና በዚህም የሳዑዲው ልዑል ሞሐመድ ቢን ሰልማንን ተጠያቂ ማድረጉ ነው።

በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅትም የሳዑዲ መንግሥት ተቺዎቹን የሚገድል እና ተቃዋሚዎቹን የሚያስር ነው ሲሉም ተደምጠው ነበር።

በአጠቃላይ ሳዑዲዎች ለአሜሪካ የምንመልሰው ምንም አይነት ውለታ የለም ብለው ያምናሉ። ይህንን ተከትሎም ፕሬዝዳንት ባይደን፣ ያለፈውን አስተያየቶቻቸውን ዋጥ አድርገው ውለታ እንደሚጠይቁ ይጠበቃል፤ ይህም ደጋፊዎቻቸውን ማስቆጣቱ አይቀርም።

ሌላው የ'አብረሃም አኮርድ' ተብሎ በሚጠራው ስምምነት እስራኤልን እና የተወሰኑ የአረብ አገራትን የያዘው ስምምነት በጋራ ጠላትነት የሚያየው ኢራንን ሲሆን፣ ይህ አሜሪካንንም የሚያስማማ ብሎም ባይደን በዚሁ ጉዟቸው አጀንዳ ከሚያደርጉት ጉዳይ መካከል ነው።

አስራኤል ከተለያዩ የአረብ አገራት ጋር ግንኙነት እንድትመሰርት የታለመው የአብራሃም አኮርድ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንዱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ስኬት ተደርጎ ይነሳል።

ባይደን እስራኤልን ደግፈው ከኢራን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባት በአሁኑ ወቅት በጭራሽ የማይፈልጉት ጉዳይ ነው። በዚህም ምክንያት እስራኤል ኢራን ላይ የከፈተችውን ተዘዋዋሪ ጦርነት እንድታቆም ሊጠይቁ ይችላሉ ተብሎ ይጠበቃል።