ልዑል ሃሪ እና ሜጋን ‘ፓፓራዚዎች’ ኒው ዮርክ ውስጥ “በመኪና አሳደዱን” አሉ

ልዑል ሃሪ እና ሜጋን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ልዑል ሃሪ፣ ሜጋን እና እናቷ ኒው ዮርክ ውስጥ ‘ለአደጋ የቀረበ መኪና ማሳደድ’ እንደደረሰባቸው የጥንዶቹ ቃል አቀባይ ገልጸዋል።

የሰሴክስ መስፍን እና ሶፋኒት [ዱክ እና ደቼስ] በመባል የሚታወቁት ጥንዶች ኒው ዮርክ ውስጥ አንድ የሽልማት ሥነ-ሥርዓት ታድመው ሲመለሱ ነው ነው ይህ የገጠማቸው።

ቃል አቀባያቸው የመኪና ማሳደዱ ለሁለት ሰዓት ያህል እንደዘለቀ እና “በርካታ የመኪና አደጋዎች ሊፈጠሩ እንደነበር” ጠቅሰዋል።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ዲፓርትመንት አደጋም ሆነ በቁጥጥር ሥር የዋለ ግለሰብ እንደሌለ ይፋ አድርጓል።

ቢቢሲ ተፈጠረ የተባለውን ክስተት ሙሉ በሙሉ እውነት ስለመሆኑ በግሉ ማጣራት አልቻለም። ነገር ግን ረቡዕ ዕለት በርካታ መረጃዎች ሲወጡ ነበር።

የኒው ዮርክ ከተማ ፖሊስ ጥንዶቹን በተመለከተ አንድ ክስተት መግጠሙን ይፋ አድርጎ ፎቶ አንሺዎች “መንገዳቸውን ፈታኝ እንዳደረጉባቸው” ገልጧል።

የባኪንግሃም ቤተ-መንግሥት በዚህ ጉዳይ እስካሁን መግለጫ አልሰጠም።

የመዝናኛ ፎቶዎችን በመልቀቅ የሚታወቀው ባክግሪድ በለቀቀው መግለጫ በርካታ ፎቶ አንሺዎችን እየመረመረ ቢሆንም አብዛኛዎቹ የሚሉት ከጥንዶቹ ጋር የሚመሳሰል አይደለም።

መግለጫው እንደሚለው “ፎቶ አንሺዎቹ ምንም ዓይነት አደጋ ውስጥ አልነበሩም።”

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ግማሽ ደርዘን መኪኖች ተከታትለው ሲሄዱ፤ አንዳንዶች በግድ የለሽነት ሲያሽከረክሩ እና የትራፊክ ሕግ ሲጥሱ ነበር የሚሉ መረጃዎች ወጥተዋል።

ቢቢሲ እንደተረዳው ሃሪ እና ሜጋን ለጊዜው ጓደኛቸው ቤት ያረፉ ሲሆን ለደኅንነታቸው በመስጋት ወደ ቤታቸው አልተመለሱም።

ጥንዶቹና የሜጋን እናት ዶሪያ ራግላንድ ‘ከፓፓራዚ’ በመሸሽ ወደ ማንሃታን ፖሊስ ጣቢያ አቅንተው ነበር።

መጀመሪያ ጥንዶቹ እና የሜጋን እናት በቢጫ ታክሲ ለመሄድ አቅደው የነበረ ቢሆንም ፎቶ አንሺዎችን በመፍራት ወደ ግላቸው መኪና ተመልሰዋል።

የታክሲ ሾፌሩ ሱክቻርን ሲንግ ለቢቢሲ እንደተናገረው አራት መንገደኞችን አሳፍሮ ጉዞ ጀምሯል።

“አንድ የጥበቃ ሠራተኛ አስቆመኝ። ከዚያ ልዑል ሃሪ እና ሚስቱ ወደ መኪናዬ መግባት ጀመሩ” ሲል ያጋጠመውን ይናገራል።

“ትንሽ እንደተጓዝን ከፊት ለፊታችን ቆሻሻ የጫነ መኪና ሲያግደን ድንገት ፓፓራዚዎች መጥተው ፎቶ ማንሳት ጀመሩ። ወደየት እንደሚሄዱ ሊነግሩኝ ነበር ድንገት ሐሳባቸውን ቀይረው ወደ ፖሊስ ጣቢያ እንድሄድ አዘዙኝ።”

ሲንግ እንደሚለው ተሳፋሪዎቹ “መልካም ሰዎች ናቸው” ነገር ግን በሆነው ነገር “ተረብሸው ነበር።”

ሾፌሩ አክሎም “ለአደጋ የቀረበ” የሚለው ክስ ትንሽ የተጋነነ ሲሆን ፓፓራዚዎቹ ያን ያህል “አስቸጋሪ” አልነበሩም።

“ፓፓራዚዎቹ ከኋላችን ነበሩ። ነገር ግን ርቀታቸውን ጠብቀው ነበር ሲያሽከረክሩ የነበሩት።”

ሲንግ ያሳፈራቸው ሰዎች 50 ዶላር ከፍለው እንደወጡ ተናግሮ ያጋጠመው ነገር አስር ደቂቃ ብቻ እንደፈጀ ቢያስረዳም የጥንዶቹ ቃል አቀባይ ግን ክስተቱ ከሁለት ሰዓት በላይ ወስዷል ይላሉ።

ምንም እንኳ የታክሲ አሽከርካሪ ይህን ቢልም የጥንዶቹ ደኅንነት ኃላፊ የሆነው ክሪስ ሳንቼዝ ሲኤንኤን ላይ ቀርቦ ያጋጠመው ነገር “እጅግ የሚረብሽ” እንደነበር ተናግሯል።