የቀድሞው የአውስትራሊያ ፖለቲከኛ ሰላይ ነበሩ ሲል የአገሪቱ ደኅንነት ኃላፊ ይፋ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, ASIO
አንድ የቀድሞ አውስትራሊያዊ ፖለቲከኛ አገሩን አሳልፎ ለውጭ ሰላይ “ሸጧል” ሲል የአገሪቱ ደኅንነት መሥሪያ ቤት ይፋ አደረገ።
ይህን የገለጹት የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ማይክ በርገስ፤ የቀድሞው የሕዝብ እንደራሴ መረጃ አሳልፈው ሰጥተዋል ብለዋል።
አገሩን ሸጧል የተባሉት የፓርላማ አባልም ሆነ መረጃ ተቀብላለች የተባለችው አገር ስም ይፋ አልሆነም።
ይህ ዜና መውጣቱን ተከትሎ የአውስትራሊያ ዋና ከተማ እና የፖለቲካ ማዕከል የሆነችው ካንቤራ ተንጣለች።
በርካቶች የሕዝብ እንደራሴው ስም ይፋ እንዲሆን እየጠየቁ ይገኛሉ።
ረቡዕ ዕለት በዋና ከተማዋ ዓመታዊ መግለጫ እየሰጡ የነበሩት የአውስትራሊያ ፀጥታ እና ደኅንነት መሥሪያ ቤት ኃላፊ “ኤ ቲም” የተሰኘው ቡድን አውስትራሊያን “ቁጥር አንድ ዒላማ አድርጎ” ሲንቀሳቀስ ነበር ብለዋል።
“ሰላዮቹ እንደ አማካሪ፣ የመንግሥት ባለሥልጣን፣ ምሑራን፣ አጥኚዎች አሊያም ደግሞ ከአንድ ልብ-ወለዳዊ ኩባንያ እንደመጡ አስመስለው ነው ሲንቀሳቀሱ የቆዩ” ብለዋል ኃላፊው።
ተማሪዎች፣ ምሑራን፣ ፖለቲከኞች፣ ነጋዴዎች፣ የፀጥታ ሰዎች፣ የመንግሥት ሠራተኞችን እና ሌሎችን በርካታ ሰዎች ዒላማ አድርገው ብር በመስጠት መረጃ ሲሰበስቡ ነበር ተብሏል።
ስለ ንግድ፣ ፖለቲካ፣ የውጭ ጉዳይ እና የመከላከያ ፖሊሲ የመሳሰሉ መረጃዎችን ይሰበስቡ እንደነበር ኃላፊው ገልጠዋል።
አውስትራሊያ ከዩናይትድ ኪንግደም ጋር የፈረመችው የመከላከያ ስምምነት ዋነኛው ጉዳይ እንደነበር በርገስ ተናግረዋል።
ነገር ግን በዚህ ቡድን ውስጥ ከሚንቀሳቀሱ ሰዎች መካከል ጎልተው የወጡት የቀድሞው ፖለቲከኛ ሲሆኑ፣ “ስኬታማ በሆነ መልኩ ሰዎች ሲመለምሉ” ነበር ብለዋል።
እኒህ ፖለቲከኛ ለምን ያህል ጊዜ ሰላይ ሆነው ይሠሩ እንደነበር ኃላፊው አልተናገሩም።
“ፖለቲከኛው አገራቸውን ሸጠዋል፣ ፓርቲያቸውን እና የቀድሞው የሥራ አጋሮቻቸውን ክደዋል፤ የውጭ አገርን ፍላጎት አስቀድመዋል” ብለዋል በርገስ።
“በአንድ ወቅት እንዲያውም የቀድሞውን ጠቅላይ ሚኒስትር ለመመልመል ሙከራ ሲያደርጉ ነበር። ምንም እንኳ ይሄ ባይሳካላቸውም ሌላው ተሳክቶላቸዋል።”
ኃላፊው፤ እንደገለጡት የቀድሞው ፖለቲከኛ አሁን ከቡድኑ ጋር አይሠሩም ብለው፣ የአውስትራሊያ ደኅንነት መዋቅር ቡድኑን “በታትኖታል” አልፎም ሳያውቁ መረጃ እየሰጡ ያሉ ፖለቲከኞችም “እንዲያውቁት” ተደርጓል።
የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባለፈው ዓመት ይህ ቡድን መበታተኑን የገለጡት ኃላፊው፣ አውስትራሊያውያን እንዲያውቁት እያደረግን ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
“አውስትራሊያውያን ሊያውቁት የሚገባው ነገር ስጋቱ የምር ነው፤ አሁን እየሆነ ያለ ነገር ነው፤ ከምናስበው በላይ ጥልቅ ነው።”
በርገስ በቅርቡ የቻይና ሰላዮች አውስትራሊያ ላይ ሊደቅኑት ስለሚችሉት ስጋት ተናግረው ነበር። ባለፈው ዓመት ደግሞ የሰላዮች “መንጋ” መበተናቸውን ከገለጡ በኋላ መገናኛ ብዙኃን ሰላዮች ሩሲያውያን ናቸው ብለዋል።
ምንም እንኳ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ፖለቲከኛው ስማቸው ይፋ አለመሆኑ ቅር ቢላቸውም የደኅንነት ኃላፊውን ውሳኔ እናከብራለን ብለዋል።












