የተጠጋገኑ እና ኦሪጂናል ያልሆኑ የሞባይል ቻርጀሮች እኛንም ስልካችንንም እንደሚጎዱ ያውቃሉ?

ሊበጠስ የደረሰ ቻርጀር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሊበጠስ ጫፍ የደረሰ እና የተጠጋገነ የሞባይል ቻርጅ ማድረጊያን መጠቀም ብዙዎቻችን ምንም ጉዳት የሌለው ይመስለናል። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ ያልተጠበቀ ሲከፋም አሰቃቂ አደጋን ሊያስከትል ይችላል።

እንዲህ አይነት የተበላሹ እና የተጠጋገኑ ቻርጅ ማድረጊያ ገመዶች በስልካችን ወይም በእኛ ላይ ሊያስከትሉ የሚችሉትን የጉዳት መጠንን በተመለከተ ብዙዎች እርግጠኛ አይደሉም።

ከተበላሹ እና ተበጣጥሰው ከተጠገኑ የስልክ ቻርጀሮች በተጨማሪ ኦሪጂናል ያልሆኑ ቻርጀሮችም በተመሳሳይ በስልካችን እና በእኛም ላይ ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

በጥሩ ሁኔታ ላይ ያልሆኑ የሞባይል ቻርጀሮችን መጠቀም ምን ችግርን ሊያስከትሉ ይችላሉ?

1. በኤሌክትሪክ መያዝ

በተበጣጠሰ እና በተጠጋገነ የሞባይል ቻርጀር ስልካችን ኃይል እንዲያገኝ ስናደርግ ከሚያጋጥሙን ችግሮች ውስጥ አስከፊው በኤሌክትሪክ የመያዝ አጋጣሚ ሊፈጥር መቻሉ ነው።

በዚህም ምክንያት በዓለም ዙሪያ የበርካታ ሰዎች ሕይወት መጥፋቱን የወጡ ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

አንዳንድ ጊዜም እንዲህ ዓይነቱ አደጋ የሚከሰተው በተበላሹ ቻርጀሮች ብቻ ሳይሆን፣ ከስልካችን ጋር የማይሄዱ ወይም ኦሪጂናል ያልሆኑ ቻርጀሮችን ስንጠቀም ጭምር ሊሆን ይችላል።

በዩናይትድ ኪንግደም ለንደን ውስጥ መቀመጫውን ያደረገው እና በኤሌክትሪክ ደኅንነት ዙሪያ የሚሠራው ተቋም “ተመሳስለው የተሠሩ የስልክ ቻርጅ ማድረጊያዎች አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ” ይላል።

በርካታ ኦሪጂናል ያልሆኑ ቻርጀሮችን በመሰብሰብ ባደረግነው ፍተሻ “98 በመቶ የሚሆኑት በተጠቃሚዎች ላይ አደገኛ ጉዳትን ሊያስከትሉ የሚችሉ ናቸው” ሲል የደረሰበትን በድረገጹ ላይ አስፍሯል።

ስለዚህም “ሊከተል የሚችለውን አደጋ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለስልካችን ቻርጀር ስንገዛ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን” ብሏል ተቋሙ።

በተበላሹና ትክክለኛ ባልሆኑ ቻርጀሮች ምክንያት በኤሌክትሪክ የመያዝ አደጋ ሊከሰት ይችላል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በተበላሹና ትክክለኛ ባልሆኑ ቻርጀሮች ምክንያት በኤሌክትሪክ የመያዝ አደጋ ሊከሰት ይችላል

2. እሳት እና ፍንዳታ

ትክክለኛ ያልሆኑ ቻርጀሮችን መጠቀም የእሳት አደጋን ሊያስከትሉ ይችላሉ።

ሐሰተኛ እና ችግር ያለባቸው የቻርጀር ገመዶች “ስልካችን ከሚገባው በላይ እንዲግል እንዲሁም እንዲፈነዳ ሊያደርጉ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ስልካችን ከጥቅም ውጪ ሊሆን እና ከባድ ጉዳትን የማስከተል ዕድልን ይፈጠራል" ሲል የኤሌክትሪክ ደኅንነት ተቋሙ አስጠንቅቋል።

“ፌክ ቻርጀሮች የሚሰሩባቸው ግብዓቶች በአብዛኛው በኤሌክትሪክ መያዝን፣ የስልካችንን የውስጥ ክፍል መቃጠል እና ሰውንም ለእሳት አደጋ ሊያጋልጡ ይችላሉ።”

በቤት ውስጥ የሚከሰቱ የእሳት አደጋውችን በተመለከተ ማፕሬ ፋውንዴሽን ባወጣው ሪፖርት መሠረት፣ ከእነዚህ አደጋዎች መካከል 25 በመቶው በኤሌክትሪክ ገመዶች ምክንያት ሲሆኑ፣ በርካቶቹም ችግር ባለባቸው የሞባይል ቻርጀሮች ሰበብ የሚቀሰቀሱ ናቸው ብሏል።

ሐሰተኛ ቻርጀር የስልካችንን ባትሪ ይጎዳል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሐሰተኛ ቻርጀር የስልካችንን ባትሪ ይጎዳል

3. ባትሪን ከጥቅም ውጪ ማድረግ

ኦሪጂናል ያልሆኑ ወይም የተጠጋገኑ የሞባይል ቻርጀሮች ስልካችንን ላያቃጥሉት ይችላሉ። ነገር ግን በእንዲህ ዓይነት ቻርጀሮች ስንጠቀም የስልካችን የባትሪ አቅም ቀስ በቀስ እየተዳከመ አገልግሎት ከማይሰጥነት ደረጃ ላይ ሊደርስ ይችላል።

ለዚህም ምክንያቱ ችግር ያለባቸው ቻርጀሮች የስልካችን ባትሪ የሚፈለገውን ያህል የኃይል መጠን ከሚሰጡበት ደረጃ ላይ ስለማይሆኑ ባትሪያችንን ቀስ በቀስ ይገድሉታል።

በየትኛው የቻርጀራችን ክፍል ላይ ሊበጠስ የደረሰ ወይም የተበጠሰ ክፍል ካለ በፕላስተር ወይም በሌላ ነገር መሸፈን የሚፈጠርን ችግር አያስቀረውም።

ስለዚህ ቻርጀራችን ከተበጠሰ በምንም ዓይነት መልኩ ጠግነን ወይም አስተካክለን አለመጠቀም ይመከራል።

የተሻለው መፍትሔ ከስልካችን ባትሪ የኃይል ፍላጎት ጋር የሚጣጣም ኦሪጂናል ቻርጀር መተካት ለእራሳችንም ለስልካችንም ደኅንነት ወሳኝ ነው።

ሐሰተኛ ቻርጀሮችን እንዴት እንለይ?

ቻርጀር ስንገዛ በእውነተኛው እና በሐሰተኛው መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ የጠለቀ ዕውቀትን የሚጠይቅ አይደለም የሚሉት ባለሙያች፣ ‘ፌክ’ የሆኑትን በቀላሉ መለየት የሚቻልባቸውን መንገዶች አሳውቀዋል።

በቻርጀሩ ላይ የሰፈረውን ጽሁፍ፡ የምርት ምልክት እና ጥራቱን ልብ ብለው ይመልከቱ አንዳች ጉድለት ያገኙበታል።

የሶኬቱን ጫፍ ይመልከቱ፡ ትክክለኛ ካልሆነ በአብዛኛው አንጸባራቂ እና ትክክል ያልሆነ ነገር ሊያገኙ ይችላሉ።

የቻርጀሮቹ ክብደት፡ የሚሰሩበት ቁሶች ርካሽ እና ክብደታቸው የተለየ ነው። ሐሰተኞቹ ውስጣቸው ባዶ ስለሚሆን ቀላል ይሆናሉ።

ቅርጽ እና መጠን፡ ቻርጀሩ ሐሰተኛ ከሆነ መሰኪያዎቹ በአብዛኛው ትልቅ ይሆናል።

የተጠጋገነ ቻርጀር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የቻርጀር አያያዝ

የስልካችን ቻርጀር ገመድ እንዳይበላሽ ወይም እንዳይበጠስ በአያያዝ እና በአቀማመጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልገናል። በዚህም ተጨማሪ ውጪ እንዳናወጣ እና የእራሳንንም ሆነ የስልካችንን ደኅንነት እንጠብቃለን።

ስለዚህ ቻርጀራችንን ገመዱን ለመሰባበር እና ለመበጣጠስ በሚያጋልጥ ሁኔታ አንጠቅልለው፣ ጥብቅ ብሎ እንዳይታጠፍ እናድርግ እንዲሁም ለፀሐይ ወይም ለሙቀት በማይጋለጥበት ቦታ ላይ ብቻ አናስቀምጠው።

ስልካችንን ቻርጅ ስናደርግም የባትሪው አቅም ሊሟጠጥ ሲቃረብ ቢሆን ይመከራል። በተጨማሪም የስልካችንን ኃይል አጥፍተን ቻርጅ ብናደርግ ባትሪው ለረጅም ጊዜ ልንገለገልበት እንችላለን።

በተጨማሪም በተለይ ሌሊት ላይ ባትሪው ሞልቶ ያድራል በሚል ስልካችንን ቻርጅ ላይ ሰክተን መተው የለብንም። ስልካችን ባትሪው ሙሉ እስኪሆን ድረስ ብቻ የሚያስፈልገውን የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያገኝ ቻርጅ ካደረገን በኋላ መነቀል አለበት።