የስልክዎ ባትሪ ቶሎ ቶሎ የሚያልቀው ለምንድን ነው?

እያለቀ ያለ ባትሪ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Apple

ከሦስት ሰዎች ጋር የጽሑፍ መልዕክት ተለዋውጠው፣ ሁለት ኢሜል መልሰው፣ አራት ድረ ገጾችን ቃኝተው ስልክዎ ባትሪው ያልቃል።

እናም ስልክዎን ‘ቻርጅ’ ማድረግ ከዕለት ከዕለት ግዴታዎችዎ አንዱ ይሆናል።

ቀደምት ስልኮች እንዲህ ቶሎ ቶሎ ባትሪ አይጨርሱም ነበር።

ለምን? ቢባል፣ ድሮ የምንይዛቸው ስልኮች 2ጂ ነበሩ። የሚጠቀሙት ጂኤስኤም ኔትወርክ ነበር።

እነዚህን ስልኮች እንደ አሁኑ ዘመን ለእያንዳንዱ ነገር አንጠቀምባቸውም ነበር።

ገፋ ቢል መደዋወያና የጽሑፍ መልዕክት መለዋወጫ ነበሩ።

እናም አንዴ ባትሪያቸው ከተሞላ ለሳምንትም ሊቆይ ይችላል።

አሁን ግን ስልካችንን የማናዘው ሥራ የለም።

ይደውላል፣ መንገድ ይጠቁማል፣ ምግብ ያዛል፣ ቪድዮ ያሳያል፣ ፎቶ ያነሳል፣ ከገመድ አልባ ኢንተርኔት ጋር ተሳስሮ በይነ መረብን ያስሳል ወዘተ. . .

ይሄ ሁሉ ሥራ ታዲያ ከፍተኛ የባትሪ አቅም ይጠይቃል።

የዚህ ዘመን ስልክ እና ኮምፒውተር መረጃን በፍጥነት ያብላላሉ።

ለዚህም ኤሌክትሮኖች በስውር የኤሌክትሪክ ገመዶች መዘዋወር ይጠበቅባቸዋል።

ይሄ ዝውውር ከፍተኛ ሙቀት ይፈጥራል።

ስለዚህ ስልኮች እና ኮምፒውተሮች ንፋስ መዘወሪያ ይገጠምላቸዋል።

ይሄ ሁሉ እንቅስቃሴ የባትሪ አቅም ይፈልጋል።

ስልክ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባትሪዎ ለምን ቶሎ ቶሎ ያልቃል?

ሲልከን ቫሊ ውስጥ የሚገኘው ዴቼ ቴሌኮም የጥናት ማዕከል ተመራማሪዋ ዶ/ር አንጄላ ኒኮራ ስለ ተንቀሳቃሽ ስልክ ባትሪ በመመራመር ትታወቃለች።

አንድ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከ15,000 እስከ 20,000 ጆልስ [የኃይል መለኪያ] የሚደርስ ኃይል ይፈልጋል።

ዶ/ር አንጄላ ተንቀሳቃሽ ስልክ ከዚህ ኃይል መካከል ምን ያህሉን ለምን ሥራ እንደሚያውል ነው የተመራመረችው።

ስልክን ከኢንተርኔት ጋር ማገናኘት ብቻውን 12 ጆልስ ኃይል ይጠይቃል።

ይሄ ስልኩ ከኢንተርኔት መረጃ ለመጫን የሚወስደውን ኃይል አያካትትም።

በዶ/ር አንጄላ ጥናት መሠረት፣ ድረ ገጾች ሲሠሩ ተጠቃሚዎች ድረ ገጾቹን ለመጎብኘት የሚወስድባቸው የባትሪ ኃይል ከፍ ብሎ ነው።

ለምሳሌ የቢቢሲን ድረ ገጽ በስልክዎ ለመክፈት 3 ጆልስ ኃይል ያስፈልግዎታል።

ከድረ ገጾች መካከል አፕልን ለመክፈት 34 ጆልስ ይጠይቃል። ዊኪፒዲያም ተቀራራቢ ኃይል ይፈልጋል።

ስለዚህ ግድ የለሽ ድረ ገጾች ስልካችን ባትሪ እንዳይበላ አድርገው ድረ ገጻቸውን እየገነቡ እንዳልሆነ ዶ/ር አንጄላ ታስረዳለች።

ድረ ገጾች የተወሰነ ማሻሻያ አድርገው ይህንን ችግር መቅረፍ ይችላሉ።

የኔትወርክ ችግር

በማሳቹሴትስ የቴክኖሎጂ ኢኒስቲቲዩት (ኤምአይቲ) የኮምፒውተር ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ሀሪ ባላክሻናን እንደሚለው፣ ችግሩ ያለው ድረ ገጾች ላይ ብቻ አይደለም።

የኢንተርኔት ኔትወርክ የሚያቀርቡ ድርጅቶች የሚከተሉት አሠራርም ለባትሪ ቶሎ ቶሎ ማለቅ ተጠያቂ ነው።

መረጃ ማስተላለፍ ስንፈልግ፣ ኢንተርኔት አቅራቢው ተለቅ ያለ ኃይል ይለቃል።

አንዴ ኃይሉ ከተለቀቀ በኋላ አነስተኛ ኃይል የሚጠይቅ ሥራ ብንሠራም መጀመሪያ በተለቀቀው መጠን የሚቆይበት ዕድል አለ።

ፕሮፌሰር ሀሪ እንደሚለው፣ ይህ ከፍተኛ ኃይል ባትሪያችንን ቶሎ ይጨርሰዋል።

የባትሪ አቅም ከስልክ ስልክ እንዲሁም ከኔትወርክ ኔትወርክ ይለያያል።

ዘለግ ላለ ጊዜ ባትሪ እንዲቆይ የሚያስችል ተመራጭ የሚሆነውም ለዚህ ነው።

3ጂ ሲተገበር፣ ኔትወርኩ የሚጠይቀው ዓይነት ባትሪ መዘጋጀት ነበረበት።

የሞባይል ባትሪ መጠን አመልካች

የፎቶው ባለመብት, Thinkstock

ኃይል መቆጠብ

ተንቀሳቃሽ ስልክ ትንሽ ኃይል ከሚፈግ መተግበሪያ ከፍተኛ ኃይል እስከሚወስደው ድረስ ያስተናግዳሉ።

በተለይ ደግሞ የተንቀሳቃሽ ስልኮችን ስክሪን ዐይነ-ግቡ ለማድረግ ከፍተኛ ኃይል ያስፈልጋል።

ኃይል ቆጣቢ ከሚባሉ መተግበሪያዎች አንዱ የኪንድል የበይነ መረብ መጽሐፍ ማንበቢያ ነው።

አሁን ባለንበት ዘመን የተሻለ የሚባለው የቴክኖሎጂ ምርት ባትሪ ቆጣቢው እንደሆነ ባለሙያዎች ይስማማሉ።

በተደጋጋሚ ‘ቻርጅ’ የሚደረግ ባትሪ እአአ በ1990ዎቹ ሲፈጠር አስደንቋል።

አሁን ደግሞ ዘመኑ ታዳሽ ኃይል የተሻለ አማራጭ የሆነበት ነው።

በእርግጥ በፀሐይ የስልክ ባትሪን ለመሙላት የተደረገው ሙከራ እምብዛም አልተሳካም።

ሌላው ሙከራ ስልክን በራድዮ ሞገድ ባትሪ ለመሙላት መሞከር ነው።

በዩኒቨርስቲ ኦፍ ዋሽንግተን ሲያትል ተመራማሪ የነበረው ጆሽዋ ስሚዝ ነው ይህንን የሞከረው።

ጥናቱን እንደ ጉግል እና ኢንቴል ያሉ ትልልቅ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎች ደግፈውታል።

ስልክ ከራድዮ ሞገድ ኃይል እንዲያገኝ የሚያደርገውን መንገድ ለማሳለጥ የአሜሪካ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከኃይል ማማቸው ኃይል እንዲወሰድ እያደረጉ ነው።

እስከ 30 ኪሎ ሜትር ከሚጓዝ የራድዮ ሞገድ ነው ኃይል ለመውሰድ የተሞከረው።

ይህ ኃይል ስልክ ለመደዋወል ባይበቃም፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት ለመለዋወጥ ያስችላል።

ወይም ደግሞ ስልክዎ ባትሪው ሊያልቅ የቀረውን ሰዓት በማራዘም ይረዳዎታል።