በሙስና ቅሌት ስማቸው እየተነሳ ያለው የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ከስልጣን እንደማይለቁ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎዛ ከእርሻቸው በተዘረፈው ገንዘብ ጋር ተያይዞ በሙስና ቅሌት ስማቸው ቢነሳም ከስልጣናቸው እንደማይለቁ ቃለ አቀባያቸው ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ከሁለት ዓመት በፊት በእርሻ መሬታቸው ላይ የተፈጸመውን የ4 ሚሊዮን ዶላር ዘረፋ ለመሸፋፈን ሰዎችን በማገት እና ጉቦ በመስጠት ጉዳዩን በዝምታ እንዲታለፍ ጥረዋል ተብለው ይከሰሳሉ።
ይህ ተዘረፈ የተባለው ገንዘብ ከሙስና ወይም ህጋዊ ያልሆነን ገንዘብ ህጋዊ ከማስመሰል ወንጀል ጋር የተያያዘ ነው ተብሏል።
ገለልተኛ ከሆነ አካል ሾልኮ የወጣ አንድ ሪፖርት ራማፎዛ ስልጣናቸውን በመጠቀም ያልተገባ ድርጊት እንደፈጸሙ እና የጸረ ሙስና ህጉን ጥሰው ሊሆን እንደሚችል አመላክቷል።
ፕሬዚዳንት ሲሪል ራማፎሳ በበኩላቸው ይህንን እንደሚታገሉና ከስልጣን አልለቅም ማለታቸውን ቃለ አቀባያቸው ተናግረዋል።
ይልቁንም የገዢው ፓርቲ የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ መሪ ሆነው ለሁለተኛ ጊዜ አገሪቷን መምራት እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።
“ፕሬዚዳንት ራማፎዛ በተሳሳተ ሪፖርት ከስልጣናቸው አይለቁም ከፖለቲካም አይገለሉም” በማለት ቪንሰንት ማግዌንያ አስረግጠው ተናግረዋል።
አክለውም “ከራማፎዛ ፕሬዚዳንትነት ባለፈ ዲሞክራሲያዊ ለሆነው ህገመንግሥታችን የወደፊቱ ጥቅም እና ዘላቂነት ስንል እንዲህ ዓይነቱን የተሳሳተ ሪፖርት ልንገዳደረው ይገባል” ብለዋል።
የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ስለላ መስሪያ ቤት ሃላፊ አርተር ፋራሰር ፕሬዝዳንት ራማፎዛ እንደ አውሮፓውያኑ በ2022 በሰሜን ምስራቅ የደቡብ አፍሪካ ክፍል የሚገኘው ፓላ ፓላ የተሰኘው እርሻቸው ላይ የተፈጸመውን የ4 ሚሊዮን ዘረፋ በተመለከተ ለፖሊስ አቤቱታ ማቅረባቸውን ተከትሎ የፋርማ ጌት ቅሌት ለመጀመሪያ ጊዜ ህዝብ ጆሮ የገባው ባለፈው ሰኔ ወር ነበር።
ራማፎዛ ስርቆት መኖሩን ያመኑ ቢሆንም የተሰረቀው ገንዘብ ከተባለው በታች ነው፣ ለመሸፋፈንም አልሞከርኩም ብለዋል።
ከጎሽ ሽያጭ በጥሬ ገንዘብ ከተከፈለው 580 ሺህ ዶላር ውስጥ የተወሰነው የእርሻ ቦታው ስር ካለ ሶፋ ስር ተሰርቋል ብለዋል። ነገር ግን በቀድሞው ዋና ዳኛ የሚመራው ጉባዔ የጎሽ ሽያጭ ስለመፈጸሙ ከፍተኛ ጥርጣሬ እንዳለው አሳውቋል።
ኮሚቴው ሪፖርቱን ለሀገሪቱ ፓርላማ ያቀረበ ሲሆን በቀጣይነትም ጉዳዩን መርምሮ ራማፎዛ ላይ ክስ የመመሰረቱ ሂደት ይጀመር ወይም አይጀመር የሚለው ላይ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
ፕሬዚዳንቱ ከተቃዋሚዎች እንዲሁም በፓርቲያቸው ውስጥ ባሉ ተቀናቃኞቻቸው ስልጣን እንዲለቁ ጫና በርትቶባቸዋል።
ከሙስና ቅሌት ጋር በተያያዘ ከስልጣን የለቀቁት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማን ብልሹ አሰራር አስተካክላለሁ ብለው ቃል በመግባት ወደ ስልጣን ለመጡት ፕሬዚዳንት ራማፎሳ ይህ ቅሌት የፖለቲካ ህይወታቸውን የሚጎዳ ነው ተብሏል።












