ህወሓት ‘እጅ በመስጠት ምሥጢር አውጥተዋል’ ያላቸውን ኬሪያ ኢብራሂምን እና ሙሉ ገብረእግዚአብሔርን አባረረ

ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረእግዚአብሔር
የምስሉ መግለጫ, ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረእግዚአብሔር

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ በጦርነቱ ወቅት ለፌደራል መንግሥቱ እጅ ሰጥተው ምሥጢር አሳልፈው ሰጥተዋል ያላቸውን ሁለት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን ከፓርቲው ማባረሩን አስታወቀ።

ህወሓት ከድርጅቱ ያባረራቸው ሁለቱ ሴት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ ከጦርነቱ በፊት በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ የነበሩት ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረእግዚአብሔር ናቸው።

ሁለቱ ግለሰቦች በፓርቲው ውስጥ ከነበራቸው ኃላፊነት በተጨማሪ የምክር ቤት አባላት የነበሩ ሲሆን፣ ወ/ሮ ኬርያ ኢብራሒም የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እና ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔር ደግሞ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ነበሩ።

በትግራይ ውስጥ ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ተባብሶ የፌደራል መንግሥቱ ወደ መቀለ በገባበት ጊዜ መያዛቸው ከተገለጹት የፓርቲው አባላት መካከል የሆኑት ሁለቱ ግለሰቦች፣ በእስር ላይ ከቆዩ በኋላ በፕሪቶሪያው ስምምነት ጦርነቱ መቆሙን ተከትሎ ነበር የተለቀቁት።

ህወሓት ውሳኔውን ባሳወቀበት መግለጫው ላይ እንዳለው፣ ለረጅም ጊዜ የዘገየውን “በጦርነቱ ወቅት በጠላት እጅ ወድቀው ስለነበሩት የማዕከላዊ ኮሚቴው አባላቱን” በተመለከተ ግምገማ አድርጎ ውሳኔ አሳልፏል።

የፓርቲው ማዕከላዊ ኮሚቴ ሐሙስ የካቲት 14/2016 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ኬሪያ ኢብራሂም እና ሙሉ ገብረእግዚአብሔር “ለጠላት እጃቸውን ሰጥተው ምሥጢር አሳልፈው ሰጥተዋል” ተብለው በድርጅቱ ደንብ መሠረት ከማዕከላዊ ኮሚቴ እና ከህወሓት አባልነት እንዲባረሩ ወስኗል።

በተጨማሪም ይህንን ውሳኔ ተከትሎ ሁለቱ ተሰናባቾች “በጽኑ ተጸጽተው በሚሰማሩበት ሥራ ላይ በቀጣይ ሕዝባቸውን ለመካስ ቃል ገብተዋል” ብሏል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ስር የነበሩትን ሌሎች የፓርቲውን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ጉዳይ ተመልክቶም በነበሩበት ኃላፊነት እንዲቀጥሉ ወስኗል።

በዚህም መሠረት አዲስ ዓለም ባሌማ (ዶ/ር)፣ አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር)፣ አጽበሃ አረጋዊ፣ ኪሮስ ሐጎስ፣ ረዳኢ በርሀ (ዶ/ር) በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነታቸው እንዲቀጥሉ በሙሉ ድምጽ ወስኗል።

ህወሓት ባካሄደው የማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባው ከኃላፊነት እና ከአባልነት ያሰናበታቸው እንዲሁም በማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት እንዲቀጥሉ የወሰነላቸው አባላቱ፣ በተለያዩ ሁኔታዎች በጦርነቱ ወቅት በፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ውለው የነበሩ ናቸው።

ከፓርቲው እንዲባረሩ የተወሰነባቸው ሁለቱ ሴት የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ እንዲሰናበቱ የተደረገው እጃቸውን በመስጠታቸው እና ምሥጢር አሳልፈው በመስጠታቸው መሆኑ ተገልጿል።

ሌሎቹ በነበሩበት ቦታ እንዲቀጥሉ የተወሰነላቸው የድርጅቱ አባላት፣ በክልል እና በፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም በፓርቲው ውስጥ በተለያዩ የኃላፊነት ቦታ ላይ የነበሩ ናቸው።

ለሁለት ዓመታት በተካሄደው ደም አፋሳሽ ጦርነት ወቅት በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ስር የነበሩት የህወሓት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የተለያዩ ክሶች ተመስርተውባቸው እንደነበረ ይታወሳል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል ጦርነቱን ለማስቆም በአፍሪካ ኅብረት እንዲሁም በሌሎችም አደራዳሪነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የተደረሰውን ስምምነት ተከትሎ ነበር አሁን የፓርቲው ማዕካለዊ ኮሚቴ ውሳኔ ያሳለፈባቸው አባላቱ ከእስር የተለቀቁት።