የአማራ እና የትግራይ ክልሎች በሚወዛገቡባቸው የራያ ወረዳዎች እየተከሰተ ያለው ምንድን ነው?

ኮረም ከተማ

የፎቶው ባለመብት, korem Commun.

የምስሉ መግለጫ, ኮረም ከተማ

በራያ ወረዳዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የተፈጠረው ውጥረት ቀጥሎ በዛታ ወረዳ ተኩስ እየተሰማ መሆኑን የአካባቢው ባለሥልጣናት ለቢቢሲ ገለጹ።

ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ዕለት የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ተሽከርካሪ ከኮረም ከተማ አንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በታጣቂዎች ጥቃት እንደተፈጸመበት ማኅበሩ ለቢቢሲ አስታውቋል።

በትግራይ እና አማራ ክልል መካከል ውዝግብ ከሚነሳባቸው የራያ አካባቢዎች መካከል አንዱ በሆነው ዛታ ወረዳ የተኩስ ድምጽ ድጋሚ መሰማት የጀመረው ከትላንት ረቡዕ የካቲት 13/2016 ዓ.ም. ከረፋድ አራት ሰዓት ተኩል ጀምሮ መሆኑን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን መኮንን ገልጸዋል።

አቶ ካሳሁን ተኩስ የከፈቱት ታጣቂዎች ከትግራይ ክልል “ማይጨው ከተማ” የተነሱ ናቸው ያሉ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከልም “የድሮ የህወሓት ፕሮፓጋንዳ ሰዎች” እንደሚገኙበት ተናግረዋል።

የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ ኪዳኑ ከክልሉ ተነስቶ ጥቃት የፈጸመ ታጣቂ ቡድን “የለም” ሲሉ ክሱን አስተባብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ፤ “ሚሊሻ፣ ነዋሪ፣ ሕዝብ ወደ ቀያችን እንመለስ የሚል ጥያቄ ነው ያለው። ከዚያ ባለፈ በትዕግስት እየተጠባበቀ ያለ ኃይል ነው” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የዛታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ካሳሁን፤ ወደ ወረዳው የገቡ ታጣቂዎች ተኩስ የተከፈቱት በሦስት አቅጣጫ እንደሆነ ገልጸው፣ “አንዱ በጥራሬ በኩል ሆኖ ወደ ሰቆጣ መሻገሪያ፣ ሁለተኛው ዛታ ወረዳ ፊት ለፊት ካምፕ አለ ትምህርት ቤት ላይ፣ ሦስተኛው ማይላሃም ከዛታ ቀበሌ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀትነው” ሲሉ አስረድተዋል።

ዋና አስተዳዳሪው እንደሚሉት በትላንትናው ዕለት የተከፈተው ተኩስ ለአንድ ሰዓት ከ20 ደቂቃ ገደማ ከተሰማ በኋላ ቆሟል። ተኩሱ ሊቆም የቻለው የፌደራል ፖሊስ መሃል በመግባቱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ካሳሁን፤ “ተኩሱ ከፍተው ወደዚህ ሲገቡ፤ ፌደራል ፖሊስ መሃል ላይ ገባ። እነሱ ላይ ሦሰት ጊዜ ጥቃት ለማድረስ ቢሞክሩም አልተቻለም” ሲሉ ሁኔታውን ገልጸዋል።

በዛሬው ዕለት ደግሞ አልፎ አልፎ የ“የስናይፐር” ተኩስ ድምጽ እየተሰማ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል። ትላንትም ሆነ ዛሬ ለተከፈተው ተኩስ የአካባቢው ሚሊሻ የአጸፋ መልስ ከመስጠት መቆጠቡን አቶ ካሳሁን ተናግረዋል።

ይሁንና ቢቢሲ ይህንን መረጃ ከሌላ ገለልተኛ ምንጭ ማረጋገጥ አልቻለም።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነትን ተከትሎ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር በሆኑት የራያ ወረዳዎች ላይ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት እና ቦታዎች የተኩስ ልውውጥ መደረጉን እና ጥቃት መፈጸሙን ቢቢሲ ያገኛቸው መረጃዎች ያሳያሉ።

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደሚያስረዱት በወረዳዎቹ የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የካቲት 6/2016 ዓ.ም. ጀምሮ ነው።

በዕለቱ ተኩስ የተከፈተው በራያ ባላ ወረዳ በኩል መሆኑን ለቢቢሲ የተናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀፍቱ ስዩም፤ “ከ400 ያላነሰ ኃይል ነው የመጣው። አብዛኛው ዘመናዊ መሳሪያ የያዘ ነው። ዲሽቃ፣ ብሬን፣ ስናይፐር የያዘ ነው” ሲሉ “ከትግራይ ክልል መጥተዋል” ያሏቸውን ታጣቂዎች ገልጸዋል።

ዋና አስተዳዳሪው፤ “የማንነት ጥያቄ ያለበት አካባቢ ነው። በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሕጋዊ በሆነ መንገድ [ጥያቄው] እስከሚመለስ ድረስ ‘ሊወጡልን ይገባል’ ብለን እየጠየቅን፤ ሚሊሻው በአካባቢው ስለነበር ቦታ ይዞ ነበር። አሁንም ገፍተው ሲመጡ [ሚሊሻው] ማሳለፍ አልፈለገም [የተኩስ] ልውውጥ አድርጓል” ሲሉ በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ አስረድተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ይህ የተኩስ ልውውጥ ለአንድ ሰዓት ገደማ ከቆየ በኋላ በማግስቱ ሐሙስ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው ገብቶ ሁኔታውን ማረጋጋቱን እና ረቡዕ ዕለት ሌሊት ላይ በወፍላ ወረዳም ጥቃት መፈጸሙን የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፍሰሐ ሞላ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አቶ ፍሰሃ፤ “ባለፈው ሳምንት ወፍላ ወረዳ ፋላ ቀበሌ ላይ የካቲት ስድስት ሌሊት ለሰባት አጥቢያ ቀበሌ መሃል ላይ በመግባት የቀበሌውን ምክትል አስተዳዳሪ [አግተው] ወስደዋል” ሲሉ “በማይጨው ዙሪያ” ካሉ ቀበሌዎች መጥተዋል ያሏቸውን ታጣቂዎች ከስሰዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አክለውም፤ “እዚያ አካባቢም የፌደራል ፖሊስ ስላለ ተኩስ እንዲጀመር ፍላጎት የለንም። ወደ መጡበት እንዲመለሱ ነው ፍላጎታችን። ከአቅም በላይ ከሆነ ግን እኛ እርምጃ እንወስዳለን” ብለዋል።

የረቡዕ ዕለቱ የተኩስ ልውውጥ ከተካሄደ አራት ቀናት በኋላ ቅዳሜ የካቲት 9/2016 ዓ.ም. ከኮረም ከተማ በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ “አድ ነባ” በሚባል ቦታ ላይ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር እና በአንድ የሕዝብ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥቃቶች መፈጸማቸውን የአካባቢው ምንጮች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

አንድ የኮረም ከተማ የመንግሥት ኃላፊ፤ “ቅዳሜ ዕለት ገበያ ቆይተው የሚመጡ [ሰዎችን በያዘ] የሕዝብ ባስ ላይ ታጣቂዎች ጥይት ተኩሰው አንድ ሰው ቆስሎብናል። ተሳፋሪዎቹንም በጣም አንገላተዋቸዋል። ከወደ ሰቆጣ የሚመጣ አንድ የቀይ መስቀል መኪናም [በጥይት] መትተዋል” ሲሉ በዕለቱ የደረሱ ጉዳቶችን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የሰብአዊ ዲፕሎማሲ እና የኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ኃላፊ አቶ መስፍን ደረጄ፤ በማኅበሩ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት መፈጸሙን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

እንደ አቶ መስፍን ገለጻ ጥቃት የደረሰበት የቀይ መስቀል ማኅበር ተሽከርካሪ ድርቅ በተከሰተባቸው የዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች የሚሰጥ ድጋፍን በተመለከተ ጥናት ለማድረግ የተንቀሳቀሱ አንድ የእርዳታ ሠራተኛን እና አሽከርካሪውን የያዘ ነበር።

ኃላፊው፤ “[አድ ነባ] አካባቢ ሲደርሱ የታጠቁ ኃይሎች ተሽከርካሪው ላይ ጥቃት ከፈቱ፤ ቦንብም አፈነዱ። በሰው ላይ ግን የደረሰ ጉዳት የለም” በማለት ጥቃቱ የጥይት ተኩስ ብቻ እንዳልነበር አስረድተዋል። ከቀኑ አስር ሰዓት ተኩል ገደማ በተፈጸመው በዚህ ጥቃት፤ የተሽከርካሪው መስታወቶች “መበተናቸውን” ተናግረዋል።

“ታጣቂዎቹ ሰዎቹ የቀይ መስቀል ሠራተኞች መሆናቸውን ሲያውቁ ለቅቀዋቸዋል” ያሉት አቶ መስፍን፤ ከጥቃቱ በኋላ ሠራተኞቹ በዕለቱ በሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪ ላይ በተፈጸመ ጥቃት እግሩ ላይ በጥይት የተመታ የ16 ዓመት ልጅን ጭነው ኮረም ከተማ ወደ የሚገኝ ሆስፒታል ማድረሳቸውን ገልጸዋል።

በተፈጸመባቸው ጥቃት የተነሳም ሠራተኞቹ እያከናወኑ የነበረውን ጥናት አቋርጠው በአሁኑ ሰዓት ወደ አዲስ አበባ እየተመለሱ መሆኑንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር የጥቃት አድራሾቹን ማንነት ለይቶ እንደሆን ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ መስፍን፤ “እኛ እንደዚህ ዓይነት ነገር የምናጣራበት መንገድ የለም። ግን የታጠቁ ኃይሎች ናቸው” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በራያ ወረዳዎች ጥቃት ያደረሱት እና ተኩስ የከፈቱት “ከትግራይ ክልል የመጡ” ታጣቂዎች ናቸው የሚለውን ክስ የሚያስተባብሉት የትግራይ ክልል ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ ኃላፊ ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ፤ ጥያቄውም ተገቢ ነው ብለው እንደማያምኑ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

“ከትግራይ የመጣ [ታጣቂ] በክልላችን [ተኩስ] እያደረገ ነው የሚለው፤ መጀመሪያ [ሕዝቡ] መሬቱን ነው እየጠየቀ ያለው። የእርሻ ወቅት እየመጣ ነው ያለው፤ በልግ ነው። ስለዚህ ማነው እንደዚህ ብሎ ጠያቂው?” ሲሉ ቦታዎቹ ከትግራይ ክልል የይገባኛል ጥያቄ እንደሚነሳባቸው አመልክተዋል።

እነዚህን ቦታዎች በተመለከተ የትግራይ ክልል ሕዝብ ጥያቄ አለመመለሱን የሚናገሩት ኃላፊው፤ “[ሕዝቡ] አሁንም እየጠየቀ ነው” ብለዋል።

ሌተናል ጄኔራል ፍሰሐ፤ የራያ አካባቢዎች ባለሥልጣናት ከትግራይ ክልል ታጣቂዎች መጥተዋል ማለታቸውን “ሌላ የፖለቲካ ትርፍ ስለፈለጉ ነው” ሲሉ አጣጥለውታል። አክለውም፤ “በግጭት እና በኃይል ቢሆን ኖሮ ወደ ስምምነትም አንገባም [ነበር]። የሚከለክል ኃይል ስላለ አይደለም ዝም የተባለው ሰላምን አክብሮ ነው” ሲሉ የክልሉን አቋም ገልጸዋል።

የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተከትሎ በአማራ ክልል አስተዳደር ስር የሚገኙት ራያን ጨምሮ አወዛጋቢ ቦታዎች ከጦርነቱ ማብቃት አንድ ዓመት ከአራት ወራት በኋላም መፍትሔ አልተገኘላቸውም። የፌደራል መንግሥት የሁለቱ ክልሎች ይገባኛል ጥያቄ መልስ ለመስጠት ያሰበው በሕዝበ ውሳኔ መሆኑን ማስታወቁ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ሳምንት በፊት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ማብራሪያ በሰጡበት ወቅት “በምሁራን፣ በሃይማኖት አባቶች፣ በሽማግሌዎች፣ በወጣቶች ወይይት እያደረግን በሕዝበ ውሳኔ፣ ሕዝቡ ወደ ፈለገበት እንዲመለስ እናድርግ ይህንን ካደረግን ዘላቂ ሰላም ልናመጣለን እንችላለን” ብለው ነበር።

ይሁንና የሁለቱን ክልሎች ግዛት ይገባኛል ጥያቄ በሕዝበ ውሳኔ ለመመለስ የተጀመረው ጥረት በግጭቶች ምክንያት መደናቀፉንም ጠቅሰዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ይህንን ማብራሪያ ከመስጠታቸው አንድ ቀን አስቀድሞ መግለጫ ያወጣው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ግን አወዛጋቢዎቹን ቦታዎች በተመለከተ በሕዝብ ውሳኔ መፍትሄ ለመስጠት ከስምምነት አለመድረሱን ገልጾ ነበር።