ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል ለመሆን ጥያቄ አላቀረብኩም አለች

የፎቶው ባለመብት, MoFA/fb
ኢትዮጵያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊ ድርጅት አባል ለመሆን ጥያቄ አለማቅረቧን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ቃል አቀባዩ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊ ድርጅት አባል የመሆን ፍላጎት የላትም፤ የአባልነት ጥያቄም አላቀረበችም ሲሉ ጨምረው ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የኬንያ መንግሥታዊ ሚዲያ ኬንያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን (ኬቢሲ) የቀጠናዊ ማኅበሩን ከፍተኛ ባለሥልጣንን በመጥቀስ ኢትዮጵያ ዘጠነኛ አባል አገር አድርጎ ሊቀበል መሆኑን ዘግቦ ነበር።
ኬቢሲ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የበረሃማ፣ ከፊል በረሃማ አካባቢዎች ክልላዊ ልማት የካቢኔ ፀሐፊ የሆኑት ፔኒና ማሎንዛን ዋቢ አድርጎ ድርጅቱ ኢትዮጵያን ዘጠነኛ አባል አድርጎ ሊቀበል መሆኑን ስለመናገራቸው ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ነብዩ ተድላ ግን “መረጃው መሠረተ ቢስ ነው። ግለሰቧ መረጃውን ምን ላይ መሠረት አድርገው እንደሰጡ አናውቅም። እኛ እንደ አገር ድርጅቱን ለመቀላቀል ምንም አይነት ጥያቄ አላቀረብንም። የተለዋወጥነው ሠነድም የለም” ብለዋል።
ነብዩ ተድላ ጨምረውም ኢትዮጵያ ቀጠናዊ ድርጅቱን ልትቀላቀል ነው የሚለው መረጃ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተባለ ነገር አለመኖሩን አስታውሰው፤ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ትኩረት የአፍሪካ አህጉር ነጻ የንግድ ቀጠና ተግባራዊነት ላይ ነው ብለዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ቀጣናዊ ድርጅት ብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያን በአባልነት የያዘ ሲሆን፣ ዋና መቀመጫውም በታንዛኒያ አሩሻ ነው።
የ300 ሚሊዮን ሕዝብ የመገበያያ መድረክ የሆነው ማኅበሩ ኢትዮጵያን በአባልነት የመቀበሉን ዜና ቀደም ሲልም ሲዘገብ ቆይቷል።
በቅርቡ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዋና ፀሐፊ ፒተር ማቱኪ ለኬንያው ዘ ኢስት አፍሪካን ጋዜጣ ሲናገሩ ኢትዮጵያ የድርጅቱ አባል በምትሆንበትም ወቅት የግብይት ሁኔታው ከአምስት መቶ ሚሊዮን ሕዝብ በላይ እንደሚያደርሰው ተናግረዋል።
የሰባቱ አገራት ጥቅል ብሔራዊ ምርት (ጂዲፒ) ባለፈው ዓመት 346.17 ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል የዓለም አቀፉን የገንዘብ ተቋም (አይኤምኤፍ) ትንበያ ወስዶ የዘገበው የታንዛኒያው ዘ ሲትዝን በበኩሉ የኢትዮጵያ ማኅበረሰቡን መቀላቀል ድርጅቱን ኃያል ያደርገዋል ብሎ ነበር።
ከጥቂት ወራት በፊት ሶማሊያ የዚህ ቀጣናዊ ድርጅት አባል መሆኗ ይታወሳል።
የአባል አገራቱን ቁጥር እየጨመረ ያለው ቀጣናዊው ድርጅት ባወጣው ፕሮቶኮል መሠረት አገራቱ የሚገበያዩበት አንድ ገንዘብ ላይ ለመድረስ ወሳኝ ፖሊሲዎችን እየገመገሙ ይገኛሉ ተብሏል።
በዓለም ላይ ጠንካራ ትስስር ካላቸው የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ አንዱ ሆኖ ማየት እንደሆነም ራዕያቸውን የገለጹት ዋና ፀሐፊው ድንበር አልባ የሆነች አህጉር አጀንዳንም ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ብለዋል።
በተጨማሪም የአገራቱ አየር መንገዶች በጋራ የሚሠሩበት መንገድ ተቀይሶ በአባላቱ መካከል የሚደረገውን የአየር ትራንስፖርትን ተመጣጣኝ በማድረግ ሕዝቡ ቀላል በሆነ መንገድ የንግድ ልውውጥ መደረግ አለበት ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, SM
ባለፉት ዓመታት ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ አርባ ሚሊዮን ዶላር መዋጮ ባለመክፈላቸው ችግር ገጥሞ እንደነበር የተጠቀሰ ሲሆን፣ ባለፈው ዓመት ግን አገራቱ ያለባቸውን ውዝፍ መዋጮ እየከፈሉ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለም ተገልጿል።
የንግድ ማኅበረሰቡ ከአባል አገራቱ መወጮ በተጨማሪ 60 በመቶ የሚሆነውን በጀቱን የሚያገኘው ከልማት አጋሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከሚገኝ የገንዘብ ድጋፍ መሆኑም ተገልጿል።
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ለ2023/2024 ዓመት 103 ሚሊዮን 842 ሺህ 880 ዶላር በጀት ይዞ እንደነበር ከድረ ገጹ የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ባለፈውም ዓመትም የማኅበረሰቡ አጠቃላይ ንግድ ከአውሮፓውያኑ 2022፣ 74.03 ቢሊዮን ዶላር በ13.4 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱ የተጠቀሰ ሲሆን፣ በአውሮፓውያኑ 2021ም አጠቃላይ ንግዱ 65.268 ቢሊዮን ዶላር እንደነበርም ተመልክቷል።
የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ የተመሠረተው በአውሮፓውያኑ 1999 ሲሆን፣ ቀዳሚ አባላቱም ሦስቱ አገራት ኬንያ፣ ኡጋንዳ እና ታንዛኒያ ነበሩ።
ድርጅቱ ራዕይ ብሎ የያዘው የበለፀገ፣ ተወዳዳሪ፣ ደኅንነቱ የተጠበቀ፣ የተረጋጋ እና ፖለቲካዊ አንድነት ያለው ምሥራቅ አፍሪካን መመሥረት መሆኑን በድረ ገጹ አስፍሯል።












