ሶማሊያ ኢትዮጵያም አባል ትሆንበታለች የተባለውን የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ተቀላቀለች

ፕሬዝዳንት ሐሰነ ሼክ ሞሐመድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ሐሰነ ሼክ ሞሐመድ ሶማሊያ ወደ ማኅበሩ መግባቷ የተስፋ ብርሃን የፈነጠቀ ነው ብለዋል

ከሦስት አስርት ዓመታት በላይ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ የቆየችው ሶማሊያ ምጣኔ ሃብታዊ እድገቷን ለማጠናከር የትልቁ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል ሆነች።

ኢትዮጵያም አባል ትሆንበታለች የተባለው የምሥራቅ አፍሪካ አፍሪካ አገራት ማኅበር የሆነው ኢኤሲ በአገራት መካከል ነጻ እንቅስቃሴ እና የገበያ ትስስር እንዲፈጠር የሚያደርግ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰነ ሼክ ሞሐመድ አገራቸው የማኅበሩ አብል መሆኗን በማስመልከት አደተናገሩት፣ ውሳኔው ለአገራቸው ብልጽግና “የተስፋ ብርሃንን የሚፈነጥቅ ነው” ብለዋል።

ሶማሊያ ከ30 ዓመታት በላይ በጦርነት ውስጥ የቆየች ሲሆን፣ አሁንም አብዛኛው ክፍሏ በእስላማዊው ቡድን አል ሻባብ ቁጥጥር ስር ይገኛል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ የተወሰኑት ጎረቤቶቿም ከአል ቃኢዳ ጋር ግንኙነት ያለውን ይህንን ታጣቂ ቡድን ለመዋጋት ወታደሮቻቸውን ወደ ሶማሊያ ማሰማራታቸው ይታወቃል።

ሶማሊያ የምሥራቅ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብን በአባልነት እንድትቀላቀል ውሳኔ የተሰጠው የማኅበሩ አባል አገራት መሪዎች በታንዛኒያ አሩሻ ውስጥ እያካሄዱ ባለው ስብሰባ ላይ ነው።

ሶማሊያ የማኅበሩ አባል እንድትሆን የተፈቀደላት እንዲሁ በቀለላሉ አይደለም። አንዳንድ አባል አገራት ሶማሊያን ለመቀበል ጥያቄቀዎች እና እርግጠኛ ያለመሆን ስሜት የነበራቸው ሲሆን፣ ለወራት ባደረገችው የማግባባት ጥረት ተሳክቶላታል።

የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል አገራት ዜጎቻቸው በነጻነት ከአገር አገር እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅዱ በመሆናቸው፣ ሶማሊያ አባል ስትሆን አል ሻባብ በቀላሉ በግዛታቸው ውስጥ እንዲንቀሳቀስ ዕድል ይፈጠራል የሚል ስጋት አላቸው።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ወደ ማኅበሩ የሚገቡ አገራት በግዛታቸው ውስጥ ዴሞክራሲ እና መልካም አስተዳደር ማስፈን፣ የሕግ የበላይነትን፣ የሰብአዊ መብቶችን እና ፍትሕን የማስፈን መርኅን ማክበር ይጠበቅባቸዋል።

በዓለም ዙሪያ ያለውን የሙስና ሁኔታ የሚከታተለው ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል ባወጣው ደረጃ መሠረት ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ሶማሊያ በዓለም ላይ ሙስና የተስፋፋባቸው ከተባሉ አገራት መካከል ተመድባለች።

በዚህም ምክንያት አንዳንዶች ሶማሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብን ለማቀላቀል ዝግጁ አልነበረችም ሲሉ ይተቻሉ።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ለማኅበረሰቡ አባል አገራት ቃል እንደገቡት አገራቸው ያሉባትን ችግሮች ለመቅረፍ አባል አገራቱ ድጋፍ ያልተቆጠበ ጥረት ታደርጋለች ብለዋል።

የሶማሊያን የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ አባል መሆንን ተከትሎ የተደበላለቁ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ነው።

አንዳንዶች ሶማሊያ ቀደም ብላ የማኅበሩ አባል መሆን ነበረባት በማለት ድጋፋቸውን ሲገልጹ፣ ሌሎች ደግሞ ማኅበሩ ሶማሊያ የገጠማት ችግር ውስጥ አብሮ ሊገባ ይችላል በሚል ስጋት የተቻኮለ ውሳኔ ነው ሲሉ ሐሳባቸውን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንጸባርቀዋል።

ማኅበሩ ያለውን የገበያ ዕድል ለማስፋት ባለው ተስፋ መሠረት ከሶማሊያ ባሸገር ሌሎች የአፍሪካ ቀንድ አገራትን ጭምር ለማካተት ፍላጎት አለው።

ባለፈው ዓመት አጋማሽ ላይ የምሥራቅ አፍሪካ ማኅበረሰብ ዋና ፀሐፊ ፒተር ማቱኪ በሰጡት ፍንጭ ኢትዮጵያ እና ጂቡቲ ማኅበሩን እንደሚቀላቀሉ ተናግረዋል።

ሶማሊያ ስምነተኛ አባል አገር ሆና የተቀላቀለችው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ማኅበር ቡሩንዲን፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎን፣ ኬንያን፣ ደቡብ ሱዳንን፣ ታንዛኒያን፣ ሩዋንዳን እና ኡጋንዳን በአባልነት የያዘ ነው።