“የወደብ ጉዳይ ለኢትዮጵያ የህልውና ጉዳይ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, hopr
የባሕር በር ማግኘት ለኢትዮጵያ ተገቢ ውይይት የሚያስፈልገው የሕልውና ጉዳይ ነው ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።
በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲነሳ የነበረው የኢትዮጵያ የባሕር መተላለፊያ የማግኘት ጉዳይ አሁን ይፋ የሆነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ እና በቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ትልቋ ግን የባሕር በር የሌላት አገር የሆነችው ከ30 ዓመት በፊት ኤርትራ ነጻ መውጣቷን ተከትሎ ነው። ከዚያ በኋላ አገሪቱ ለገቢ እና ለወጪ ንግዷ የትንሿን ጎረቤት አገር ጂቡቲን ወደብ በመጠቀም ላይ ትገኛለች።
“ቀይ ባሕር እና አባይ ኢትዮጵያን የሚበይኑ፣ ከኢትዮጵያ የተቆራኙ ለኢትዮጵያ ዕድገት እና ጥፋት መሠረት ናቸው” በማለት የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ ርዕሰ ጉዳይ መሸሽ እንደማይስፈልግ ተናግረዋል።
ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር በቀጥታ በኤርትራ ላይ ያነጣጠረ ባይሆንም በርካቶች በሁለቱ አገራት መካከል ባለፉት ዓመታት የተሻሻለውን ግንኙነት ሊያበላሸው የችላል የሚል ስጋት እናዳለቸው እየገለጹ ነው።
ከቅርብ ወራት በፊት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ስለማስገኘት በይፋ ሲባል ባይሰማም፣ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ አገሪቱ የፈረሰውን የባሕር ኃይሏን መልሳ ማቋቋሟ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ላነሱት የባሕር በር ጥያቄ ኤርትራ፣ ጂቡቲ እና ሶማሌላንድ አማራጮች ሊሆኑ እንደሚችሉ በመዘርዘር፣ ይህ የኢትዮጵያ ፍልጎት ሊሳካባቸው የሚችሉባቸው ያሏቸውን ከግጭት ውጪ ያሉ አማራጮችን አስረድተዋል።
ይህንን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሃሳብ በተመለከተ ኤርትራን ጨምሮ የተጠቀሱት አገራት አስካሁን ያሉት ነገር የለም።
“እምብዛም የማይደፈረው” የባሕር በር ጥያቄ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ባዳረጉት እና ትላንት አርብ ጥቅምት 02/2016 ዓ.ም. በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በተላለፈ 45 ደቂቃን የፈጀ ገለጻቸው “እምብዛም የማይደፈር” ባሉት የቀይ ባሕር ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ በዙሪያዋ ለሚገኙ አገራት የውሃ ምንጭ እንደሆነች አስታውሰዋል። ወደ ኤርትራ እና ሱዳን ተከዜ፣ ወደ ግብፅ እና ሱዳን አባይ፣ ወደ ደቡብ ሱዳን ባሮ፣ ወደ ኬንያ ኦሞ፣ ወደ ሶማሊያ ደግሞ ገናሌ ዳዋ እና ዋቢ ሸበሌ ወንዞች ከኢትዮጵያ ተነስተው እንደሚጓዙ አንስተዋል።
በተጨማሪም ወደ ጂቡቲ የውሃ መስመር በኢትዮጵያ ወጪ መገንባቱን ተናግረው በዙሪያዋ ካሉ አገራት አንዳቸው እንኳን “ለኢትዮጵያ ንጽህ ውሃ የሚሰጥ የለም፤ ሁሉም ተቀባይ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
“የእናንተን እንካፈል የእኛን አትጠይቁ ማለት ግን ትክክል አይደለም” በማለት ኢትዮጵያ ወደ ቀይ ባሕር እና ሕንድ ውቅያኖስ ለመውጣት የሚያስችላትን በር መጠየቋን ተገቢነት አስረድተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ባሕር በር አስፈላጊነት
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በታሪክ “ለቀይ ባሕር በቀረብን ጊዜ ከዓለም ኃያላን አንዱ ነበርን” ካሉ በኋላ ዳግም ወደ ቀይ ባሕር እንዴት እንቅረብ የሚል ጥያቄ አንስተው ሲመልሱ “በግድያ እና በጦርነት መሆን የለበትም” ብለዋል።
ቀጥለውም “በግድያና በጦርነት እንዳይሆን ደግሞ ሃቅን መካድ ትክክል አይደለም” ሲሉ አክለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከታሪክ በተጨማሪ ከሕዝብ አሰፋፈር አኳያ የባሕርን አስፈላጊነትን ጠቅሰዋል።
በዚህም በኤርትራና ጅቡቲ ያሉ የአፋር ብሄሔ እንዲሁም በሶማሊያ፣ በኬንያ እና በጅቡቲ የሚገኙ የሶማሌ ብሔር አባላት የውቅያኖስ ውሃን እንደሚገኙ አንስተው “ኢትዮጵያ ያለው ሶማሊ ምን በድሎ ነው? - ለምንድን ነው ለብቻ የተከለከለው?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ኢትዮጵያ ወደብን ለማግኘት አማራጮችን መመልከቷን ገልጸው፣ ከሌሎች ወገኖች ስለተገኘው ምላሽ በቂ ማብራሪያ ባይስጡም “አይ ስጋት አለብን” የሚል ምላሽ እንደተገኘ ተናግረዋል።
በምላሹ ኢትዮጵያ ከሕዳሴ ግድብ፣ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እንዲሁም ከኢትዮቴሌኮም ድርሻ ለመስጠት ፍላጎት ማሳየቷን ገልጸዋል።
ሕዳሴ ግድብን “ሼር እናድርግ ያልነው ዝም ብለን አይደለም። ያዋጣል፣ ሂሳቡን አስበን ነው” ብለዋል።
“ልጆቻችን እንዳይባሉ አሁን ያለን መሪዎች መነጋገር አለብን። በኢንቨስትመንት፣ በሼር፣ በሊዝ ምርጫው ሊታይ ይችላል። አንነጋገርበትም የሚባል ነገር ግን ስህተት ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወደብ አልባ መሆኗ የአፍሪካ ኃያል አገር ለመሆን ያላትን አቅም እንደገደበው አንስተው፣ አገሪቱ ያላትን የባሕር በር አማራጮች ዘርዝረዋል።
የኢትዮጵያ የባሕር በር አማራጮች
ዐቢይ ኢትዮጵያ ለወደብ ክፍያ የምታወጣው ገንዘብ እጅግ ከፍተኛ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ገንዘብ በየሦስት ዓመቱ የሕዳሴ ግድብን ሊገነባ እንደሚችል ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ኢትዮጵያ ካሏት የወደብ አማራጮች መካከል በቀዳሚነት ያስቀመጡት ዘይላን ነው፤ ዘይላ ወደብ በሶማሌ ላንድ ግዛት በምዕራባዊ አውደል ግዛት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የኤደን ባሕረ ሰላጤን መሠረት ያደረገ ነው።
ይህ ወደብ ለጅቡቲ ድንበር እጅግ የቀረበ ሲሆን፣ ይህቺ የወደብ ከተማ በሐረሪ ክልል በኩል ከኢትዮጵያ ደንበር በጥቂት መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ትገኛለች።
ሁለተኛ አማራጭ ተደርጎ የተጠቀሰው የጂቡቲ ወደብ ነው። የጂቡቲ ወደብ አሁን ላይ 90 በመቶ የሚሆነውን የኢትዮጵያ የወጪ እና ገቢ ንግድ በር ሲሆን፣ ወደቡ በዓለም ላይ ከሚገኙ እጅግ ወሳኝ እና ሥራ ከሚበዛባቸው ወደቦች አንዱ ነው።
ሌላው ደግሞ በኤርትራ ውስጥ የሚገኘው አዱሊስ ወደብ ነው። አዱሊስ ቀይ ባሕርን መሠረት ያደረግ ጥንታዊ የወደብ ከተማ ሲሆን፣ ከምጽዋ በ40 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ይገኛል። ይህ ወደብ ከኢትዮጵያ ድንበር በቅርብ ርቀት ላይ ያለ ነው።
በመቀጠል ምጽዋ እና አሰብን አንስተዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ እነዚህ ሁለት ወደቦች በቀይ ባሕር ሰሜን እና ደቡብ ክፍል ውስጥ የሚገኙ በኤርትራ ግዛት ውስጥ ያሉ ወደቦች ሲሆኑ ለኢትዮጵያ ድንበር እጅግ ቀርበው ያሉ ናቸው።
“እኛ የግድ በምጽዋ ካልሆነ፣ የግድ በአሰብ ካልሆነ የሚል አቋም የለንም። እኛ የምንፈልገው መተንፈሻ በር ብቻ ነው። መተንፈሻ በር በየትኛውም መንገድ ከመጣ በግዢም ይሁን፣ በሊዝም ይሁን፣ በሆነ መንገድ በስምምነት ከመጣ የምንፈልገው እሱን ነው” ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
ቀጥለው “ከአሁኑ መክረን ዘክረን አማራጭ መንገድ የማናይ ከሆነ. . . አደገኛ ነው” በማለት፣ ነገር ግን ኢትዮጵያ ያላት የባሕር በር “ይገባኛል” ጥያቄ ሰላማዊ ሊሆን ይገባዋል ሲሉም ተደምጠዋል።
በፌዴሽን ወይም ኮንፌዴሬሽን ከሌሎች አገራት መዋሃድ እና የመሬት ልውውጥ የባሕር በር ባለቤት ለመሆን አማራጭ ከሚሆኑ መንገዶች መካከል እንደሆኑም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።
እየጨመረ የሚሄደው የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት ያሳሰባቸው የሚመስሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ ጉዳይ በገለጻቸው ውስጥ በተዳጋጋሚ ጠቅሰውታል።















