በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ መካከል አዲስ ውቅያኖስ እየተፈጠረ ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Juan Martinez
የአቤ/አብሄ ሐይቅ ደረቱን ለሰማይ ሰጥቶ፤ በኢትዮጵያ እና በጂቡቲ ድንበር መካከል ይገኛል።
ክችች ያለ መሬት እንጂ ለም ነገር በሥፍራው አይታይም፤ ልክ አልባው በረሃ ዐይን ማየት ከሚችለው ርቀት በላይ ተዘርግቷል።
የአቤ ሐይቅ [የአካባቢው ሰዎች አብሄ ይሉታል] ከዓለማችን ድንቅ ተፈጥሮዎች አንዱ ነው።
19 ኪሎ ሜትር ስፋት ይዞ፤ 17 ኪሎ ሜትር ረዝሞ የተዘረጋው ይህ ሐይቅ እጅግ ጨዋማ ስለሆነ ውሃው መርዛማ ነው።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የላይምስቶን ክምሮች ዙሪያውን ተደርድረው ልምድ የሌለው አናጢ የገነባው አጥር ይመስላሉ።
ሰማያዊ እና አረንጓዴ ቀለም የሚተፋውን ሐይቅ የከበቡት አንዳንድ እንፋሎት የሚተፉ ክምሮች 50 ሜትር ርዝመት አላቸው።
እኒህ ቋሚዎች ፀባያቸውን ላላወቀ ድንገት ጭስ ሲተፉ ልብ ይተረትራሉ። የሰልፈር ጭስ።
በዚህ በምሥራቃዊው የአህጉረ አፍሪካ ክፍል ውስጥ በሚገኘው እጅግ ከባድ ሥፍራ ተፈጥሮ ሰውን ገፍታ በራሷ ፍቅር የወደቀች ይመስላል።
የአፋር ዲፕረሽን
አቤ ሐይቅ በሶማሊ፣ በአረቢያን እና በኑቢያን ‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ መጣመሪያ ላይ የሚገኝ ነው። በሌላ ቋንቋ ይህ ሥፍራ የአፋር ዲፕረሽን (ዝቅተኛ ቦታ) ይባላል።
ሥፋራው የጥንታዊቷ ሉሲ መገኛ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ሳይንቲስቶች ‘የሥልጣኔ መገኛ እዚህ ነው’ ሲሉ ይከራከራሉ።
ሐይቁ እንዲህ ከሌሎች መሰሎቹ ተለይቶ የተቀመጠበት ምክንያት ‘ቴክቶኒክ ፕሌትስ’ የሚባሉት ንብርብር አለቶች ቀስ በቀስ እየተሰነጠቁ በመምጣታቸው ነው።
ይህ ደግሞ ከአቤ ሐይቅ በታች የተቀመጠው የምድር የታችኛው አካል (ክረስት) እየቀጠነ እንዲሄድ አስገድዶታል።
በ1950ዎቹ ሐይቁ ለእርሻ ተፈልጎ ውሃው እየተጎተተ ሲቀዳ መጠኑ በሁለት ሦስተኛ ቀንሷል።

የፎቶው ባለመብት, Juan Martinez
‘አዲሱ ውቅያኖስ’
‘ጂኦፊዚሲስቶች’ 10 ሚሊዮን ዓመት ከተሰጠው የአፋር ዲፕረሽን እና ይህ የአልካላይን ሐይቅ አዲስ ውቅያኖስ ይፈጥራል የሚል ግምት አላቸው።
ሳይንቲስቶቹ እንደሚሉት እኒህ ሦስት መሬቶች እየተሰነጠቁ በመሃላቸው ያለው ሥፍራ እሰፋ በመጣ ቁጥር ቀይ ባሕር የጅቡቲን ጠረፍ ይዞ ወደ አፋር ዲፕረሽን ይጓዛል።
በአሜሪካ ናሳ የሚገኙ ሳይንቲስቶች ናቸው ይህን የሚሉት።
ቀይ ባሕር፣ የምሥራቅ አፍሪካ ስምጥ ሸለቆ እና የኤደን ባሕረ ሰላጤ ሁላቸውም ተጠቃለው አትላንቲክን የሚያክል ውቅያኖስ ይሠራሉ።
እንደ ሳይንቲስቶቹ ግምት የአፍሪካ ቀንድ በውሃ የተከበበ ደሴት ሊሆን ይችላል።

የፎቶው ባለመብት, Juan Martinez
የአፋር ሕዝብ
ምንም እንኳ የአፋር ዲፕረሽን በአፍሪካ ከሚገኙ ሊለመዱ የሚከብዱ ሥፍራዎች አንዱ ቢሆንም ሰው ሊኖርባቸው አይችልም ማለት ግን አይደለም።
ከጂቡቲ መዲና በምዕራብ በኩል ወደኋላ ሳይመለከቱ 150 ኪሎ ሜትር ከተጓዙ አቤ ሐይቅን ያገኙታል።
በሥፍራው የሚገኙ እርብቶ አደሮች እንኳን ለከብቶቻቸው፣ ለራሳቸው የሚሆን ጠብታ ውሃ ለማግኘት ብዙ መንከራተት ይጠበቅባቸዋል።
በማስጎብኘት ሥራ የሚተዳደረው ሞሐመድ ኦማር አሊ “በእንደዚህ ዓይነት ሥፍራ መኖር ለአፋር ሕዝብ እንግዳ አይደለም” ይላል።
በሥፍራው የሚኖረው የአፋር ሕዝብ ከፊል አርብቶ ነው። ከሥፍራ ሥፍራ እየተዘዋወረ የሚኖር ነው።
ቤተሰቦቻቸውን ይዘው፤ የጨው አለት ፈልፍለው ሸጠው፤ ውሃ እና ምግብ ገዝተው እራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን መግበው የሚኖሩ ናቸው።
አብዛኞቹ የአፋር ከፊል አርብቶ አደሮች ተንቀሳቃሽ ቤት ይዘው ስለሚዘዋወሩ ቋሚ የውሃም ሆነ የኤሌክትሪክ አቅርቦት የላቸውም።

የፎቶው ባለመብት, Juan Martinez
የአየር ንብረት ለውጥ
አቤ ሐይቅ ዓመቱን ሙሉ ከባድ ሙቀት እና ለስለስ ያለ ሙቀት የሚፈራርቅበት ሥፍራ ነው።
በቀዝቃዛው ጊዜ የአየሩ ሁኔታ 30 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ይደርሳል፤ በሙቀቱ ጊዜ ደግሞ እስከ 45 ያሻቅባል።
በርካታ ታዳጊ የአፋር ማኅበረሰብ አባላት ይህን ተለዋዋጭ እና ከባድ የአየር ሁኔታን ተቋቁመው ነው ኑሮን የሚገፉት።
በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የአየር ንብረት ለውጥ አካባቢው እጅግ አስቸጋሪ እንዲሆን ከማድረጉም በላይ ድርቅም አስከትሏል።
ነገር ግን ኦማር አሊ እንደሚለው የአፋር ሕዝብ ሥፍራውን ጥሎ መሄድ ፈፅሞ አይፈልግም።
ሥፍራው ቀልብ የሚገዛ ውበት የሚላበሰው ጎህ ሲቀድ ነው።
የሰልፈር ክምሮቹ የሚተፉት የሰልፈር ጭስ ከብርቱካናማዋ ፀሐይ ጋር ተደባልቆ ሮዝ ቀለም ሲፈጥር መመልከት ሐሴት ያጎናፅፋል።
ልክ እንዲህ ያለ የተፈጥሮ ውበት ከፓሲፊክ ውቅያኖስ ሥር እንጂ ሌላ ቦታ የለም ይላሉ ሳይንቲስቶች።
ሲመሽ ደግሞ የአቤ ሐይቅ ልክ ሆሊውድ እንደሚያቀናብረው የሳይንስ ልብ ወለድ ዓይነት ትዕይንት ይፈጥራል።
ከዋክብት ልክ የአልጋ ልብስ ላይ እንደተሳለ አበባ ሰማዩን ተደግፈው ጊዜው ቀጥ ያለ ያስመስሉታል።
በአካባቢው ዳስ ጥሎ በምሽት ሰማዩን እያዩ ማደር በከተማ ግርግር ለተጨነቀች ነብስ እፎይታ ነው።

የፎቶው ባለመብት, Juan Martinez
ወደ አቤ ሐይቅ
ይህ መቼ እንደሆነ በማይታወቀው በመጪው ዘመን በአካባቢው ባለው ሥነ ምርድራዊ እንቅስቃሴ ሳቢያ ለሁለት ተከፍሎ ትልቅ የውሃ አካል ይፈጠርበታል የሚባለው ቦታ አነጋጋሪ እየሆነ ነው።
ለዚህም አካባቢው የሰው ልጅ አመጣጥን እና ሥነ ምድርን ከሚያጠኑ የየዘርፎቹ አንቱ የተባሉ ባለሙያዎች ባሻገር ሌሎችንም እያስተናገደ ነው።
አካባቢው በሉሲ አማካይነት ቀደምት የሰው ልጅ መገኛ በመሆኑ የበርካቶችን ትኩረት ስቧል፣ የዓለም እጅግ ዝቅታማው ቦታም እዚያው አቅራቢያ ነው፣ የኤርታሌ የእሳተ ገሞራ ሐይቅም እንዲሁ አንዱ መስህብ ነው።
በተጨማሪ ደግሞ ወደፊት በሥነ ምርድራዊ እንቅስቃሴ ይፈጠራል ተብሎ የሚታመነው የውሃ አካልም ያንኑ አካባቢ ከፍሎ ነው የሚያልፈወቅ።
እነዚህ ታሪካዊ እና ተፈጥሯዊ ክስተቶች ታዲያ በርካቶች ከኢትዮጵያውም ሆነ ከጂቡቲ በኩል በመሆን አካባቢውን እየተመለከቱ ዓመታት ተቆጥረዋል።
ምንም እንኳ በርካታ ጎብኚዎች ከጂቡቲ ተነስተው የአቤ ሐይቅን አይተው ለመመለስ አንድ ቀን ቢወስድባቸውም፣ ይህ ግን ለአካባቢው ክብር መንሳት ነው።
የአቤ ሐይቅን መጎብኘት ከፈለጉ ቢያንስ ለአንድ ምሽት ዳስ ጥለው ማደር አለብዎ።
እርግጥ ነው በሥፍራው ማደሪያ አዘጋጅተው የሚያስጎብኙ ድርጅቶች ጥቂት ናቸው።
ከእነዚህ መካከል አንዱ ከሚል ሐሰን ነው። ከሚል በሥፍራው ለበርካታ ዓመታት ኖሯል።
አካባቢውን ከእግር እስከ ራሱ የሚያውቀው ከሚል በአፋር ቱሪዝም ተስፋፍቶ የገቢ ምንጭ እንዲሆን ይመኛል። መመኘት ብቻ ሳይሆን እሱም የበኩሉን ያደርጋል።












