በቀጣይ ቀናት በርካታ የእርዳታ በረራዎች ወደ ትግራይ ለማድረግ እንደታቀደ ተመድ አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, ICRC
በጦርነት ለተጎዳው የትግራይ ክልል ዕርዳታ ለማድረስ በመጪዎቹ ቀናት በርካታ የሰብዓዊ እርዳታ በረራዎችን ለማድረግ እንዳቀደ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
በክልሉ አስቸኳይ ድጋፍ ለመስጠት እና ይህንንም እርዳታ ለማድረስ የሚያስፈልጉ ሠራተኞችን ለማሰማራት በረራዎቹ እንደሚደረጉም የድርጅቱ ቃል አቀባይ ፋርሃን ሃቅ ረቡዕ ኅዳር 07/2015 ዓ.ም. ተናግረዋል።
ትናንት ረቡዕ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ አየር አገልግሎት የመጀመሪያውን የሰብዓዊ እርዳታ የሙከራ በረራ አድርጎ ሽረ ከተማ ማረፉ ተገልጿል።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ኮሚቴ በሽረ ያረፈው ይህ የሙከራ በረራ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ከሁለት ዓመት በኋላ የመጀመሪያው እንደሆነ የኢትዮጵያ ቢሮ አስታውቋል።
ወደ ትግራይ የሚደረጉ የአየር በረራዎች እንደገና መጀመራቸው አስቸኳይ ሰብአዊ እርዳታን በፍጥነት ወደ ክልሉ ለማድረስና በሺዎች የሚቆጠሩ አፋጣኝ ሰብአዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸውን ሰዎች ስቃይ ለመቅረፍ ይረዳል ብሏል።
“ሁሉም የሰብዓዊ እርዳታ ማኅበረሰብ እነዚህ የመንገደኞች እና የጭነት በረራዎች በተቻለ ፍጥነት ወደ መቀለ እና ሽረ የመጀመሩን አስፈላጊነት ሊረዱ ይገባል” በማለት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መልዕክቱን አስተላልፏል።
በእነዚህ በረራዎች የሰብዓዊ እርዳታ ሰጪ ሠራተኞች ወደ ክልሉ እንዲገቡና እንዲወጡ ለማመቻቸት፣ እንዲሁም የሕይወት አድን የህክምና እና የምግብ አቅርቦቶችን እንዲያደርሱ ያስችላቸዋል በማለት የዓለም ምግብ ፕሮግራም አጽንኦት መስጠቱን ፋርሃን አስረድተዋል።
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የእርዳታ መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. መድረሳቸውን አስታውቋል።
ትግራይ የደረሱት የእርዳታ መድኃኒቶች በአስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ለማከም እንደሚውሉ ማኅበሩ ጨምሮ መግለጹ ይታወሳል።
ሆኖም በትግራይ ክልል ሕይወትን ለመታደግ በአስቸኳይ የሚያስፈልጉ የኢንሱሊን እና የዳያሊስስ መድኃኒቶች እንዳልተካተቱበት የአይደር ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ክብሮም ገብረሥላሴ ከቢቢሲ ፎከስ ኦን አፍሪካ ጋር ኅዳር 07/2015 ዓ.ም. ባደረጉት ቆይታ አስረድተዋል።
የህክምና ባለሙያው በትግራይ በኢንሱሊን እጥረት ምክንያት በየሳምንቱ በርካታ የስኳር ህሙማን እየሞቱም እንደሆነ ለቢቢሲ መናገራቸው ይታወሳል።
ከኢንሱሊን እና ከዲያሊስስ መድኃኒቶች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት የዓይደር ሆስፒታል በአስቸኳይ የሚፈልገው ለቀዶ ጥገና የሚያገለግል የሰመመን መስጫ፣ አንቲባዮቲክስ እና ሌሎች መሠረታዊ መድኃኒቶች በገቡት የቀይ መስቀል ጭነቶች ውስጥ የሉበትም ብለዋል።
ይህንንም አስመልክቶ አዲስ አበባ የሚገኘውን የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀልን መጠየቃቸውን የተናገሩት ባለሙያው፣ እነዚህን መድኃኒቶች ለመላክ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ እየጠበቁ እንደሆነ ነግረውኛል ሲሉም ለፎከስ ኦን አፍሪካ አስረድተዋል።
“ሁኔታው በጣም የከፋ እና የሚያሳዝንም ነው” ሲሉም አስረድተዋል።
በተጨማሪም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከወራት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የእርዳታ ጭነቱ በጎንደር በኩል ምዕራብ ትግራይ ማይጸብሪ መድረሱን አስታውቋል።
ወሳኝ የምግብ እርዳታዎች በመጪዎቹ ቀናት በአማራ ክልል ቁጥጥር ስር ባለችው ማይጸብሪ ከተማ ለሚገኙ ነዋሪዎች እንደሚደርስም ተገልጿል። የገባው እርዳታ 300 ቶን ምግብ የያዙ 15 የጭነት መኪናዎችን ያካተተ ነው።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ የተደረሰው የሰላም ስምምት በኋላ የገባ የመጀመሪያው እርዳታ መሆኑንም ገልጾ፣ የእርዳታ ጭነቶች በሁሉም ኮሪደሮች እንዳሉትና በሰፊውም እርዳታ ለማድረስ በየዕለቱም እርዳታ የሚገባበት መንገድ እንደሚቀጥልና ተስፋ ማድረጉንም ቃለ አቀባዩ ገልጸዋል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ከሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ጋር በመሆን ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ሠራተኞችን እና ዕርዳታዎችን ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ እየተመካከርን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
“ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ አጋር ድርጅቶች ፍቃድ እንደተሰጠ ከ48 አስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ዕርዳታ ለማድረስ ዝግጁ ናቸው” ብለዋል።
ይህም እስካሁን ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕርዳታ ጫኝ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዲሄዱ ፍቃድ እንዳላገኙ የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እርዳታ ሽረ ከተማ ደርሷል ያሉትም ትክክል እንዳልሆነ በከተማዋ የሚገኙ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ባለፈው ሳምንት ተናግረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ኅዳር 02/2015 ዓ.ም. “ከየትኛው ጊዜ በተሻለ ዕርዳታ እየቀረበ ነው” ብለው ነበር።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መድኃኒት እና ምግብ የጫኑ ተሸካርካሪዎች ሽረ ከተማ መድረሳቸውን ገልጸዋል። “ምግብ የጫኑ 35 እና መድኃኒት የጫኑ 3 ተሸከርካሪዎች ሽረ ከተማ ድርሰዋል። በረራዎች ተፈቅደዋል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ጨምረውም ከትግራይ ቆዳ ስፋት 70 በመቶ ያህሉ በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ገልጸው በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት የትግራይ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እና መድኃኒት እየቀረበ ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሽረ ውጪ የደረሱባቸው የትኞቹ አካባቢዎች እንዲሆኑ ለአምባሳደር ሬደዋን ቢቢሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
የፌደራል መንግሥቱ ዕርዳታ ወደ ትግራይ እየደረሰ ነው ይበል እንጂ የህወሓት አመራሮች እርዳታ ትግራይ እየደረሰ አይደለም ሲሉ ቆይተዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ እስከ ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ድረስ ትግራይ የደረሰ ዕርዳታ የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህወሓት ማዕከላቂ ኮሚቴ አባሉ ክንደያ ገ/ሕይወት በተመሳሳይ ዕርዳታ ክልሉ አለመግባቱን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸው ነበር።
“ሕዝባችን ያለ ክልከላ የሰብዓዊ ዕርዳታ አሁኑን ያስፈልገዋል . . . ቃል ሲተገበር ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚነት ላይ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ች ሌላ ስምምነት ላይ ሲደርሱ ድርድሩን በዋናነት ሲያስተባብሩ የነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እርዳታ “ትናንት” መሄድ ነበረበት ብለዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታው ያለ አንዳች ክልከላ በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረው ነበር።












