ቀይ መስቀል እርዳታ የጫኑ ሁለት ተሽከርካሪዎቹ መቀለ መድረሳቸውን አስታወቀ

የፎቶው ባለመብት, @ICRCEthiopia
ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ማኅበር የእርዳታ መድኃኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎቹ ትግራይ ክልል ዋና ከተማ መቀለ መድረሳቸውን አስታወቀ።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ በዘላቂነት ተኩስ ለማቆም እና በወታደራዊ ዝርዝር ሁኔታዎች ላይ ከተስማሙ በኋላ እርዳታ ወደ ትግራይ መድረሱን ሰብዓዊ እርዳታ ድርጅት ሲገልጽ ይህ የመጀመሪያው ነው።
ምንም እንኳ የትግራይ ኃይሎች ባይቀበሉትም ባለፉት ቀናት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሰብዓዊ እርዳታ ወደ ትግራይ አካባቢዎች እየደረሰ መሆኑን ገልጸው ነበር።
የዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማኅበር በትዊተር ገጹ ላይ ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 06/2015 ዓ.ም. እንዳሰፈረው መድኃኒቶች፣ የአስቸኳይ ጊዜ እና የመጀመሪያ እርዳታ ድጋፍ የጫኑ ሁለት ተሸከርካሪዎች መቀለ መግባታቸውን በትዊተር ገጹ አስታውቋል።
ትግራይ የደረሱት የእርዳታ መድኃኒቶች በአስቸኳይ የሕክምና ድጋፍ የሚሹ ሰዎችን ለማከም እንደሚውሉ ማኅበሩ ጨምሮ ገልጿል።
ባለፈው ሳምንት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰብዓዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ወዳሉባት ትግራይ ክልል እርዳታ እየገባ መሆኑን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታውቆ ነበር።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ትግራይ ኃይሎች ሁለት ዓመት የሆነውን ጦርነት ለማብቃት ግጭትን በዘላቂነት ለማቆም እና የሰብዓዊ ዕርዳታ ለማድረስ ከስምምነት መድረሳቸው ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግሥት
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሬድዋን ሁሴን ኅዳር 02/2015 ዓ.ም. “ከየትኛው ጊዜ በተሻለ ዕርዳታ እየቀረበ ነው” ብለው ነበር።
አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን መድኃኒት እና ምግብ የጫኑ ተሸካርካሪዎች ሽረ ከተማ መድረሳቸውን ገልጸዋል። “ምግብ የጫኑ 35 እና መድኃኒት የጫኑ 3 ተሸከርካሪዎች ሽረ ከተማ ድርሰዋል። በረራዎች ተፈቅደዋል” ሲሉ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ጨምረውም ከትግራይ ቆዳ ስፋት 70 በመቶ ያህሉ በፌደራል መንግሥቱ ቁጥጥር ሥር መሆኑ ገልጸው በመንግሥት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኙት የትግራይ አካባቢዎች የሰብዓዊ ዕርዳታ እና መድኃኒት እየቀረበ ነው ብለዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ ከሽረ ውጪ የደረሱባቸው የትኞቹ አካባቢዎች እንዲሆኑ ለአምባሳደር ሬደዋን ቢቢሲ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።
የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪው ይህን ካሉ ከአንድ ቀን በኋላ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት በአገር መከላከያ ቁጥጥር ሥር በሚገኙ የትግራይ አካባቢዎች ዕርዳታ ለማቅረብ ጥረት እየተደረገ ነው ሲል መግለጫ አውጥቶ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትግራይ አመራሮች
የፌደራል መንግሥቱ ዕርዳታ ወደ ትግራይ እየደረሰ ነው ይበል እንጂ ህወሓት እርዳታ ትግራይ እየደረሰ አይደለም ሲሉ ቆይተዋል።
የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ እስከ ቅዳሜ ኅዳር 03/2015 ዓ.ም. ድረስ ትግራይ የደረሰ ዕርዳታ የለም ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የህወሓት ማዕከላቂ ኮሚቴ አባሉ ክንደያ ገ/ሕይወት በተመሳሳይ ዕርዳታ ክልሉ አለመግባቱን በትዊተር ገጻቸው ላይ ገልጸው ነበር።
“ሕዝባችን ያለ ክልከላ የሰብዓዊ ዕርዳታ አሁኑን ያስፈልገዋል . . . ቃል ሲተገበር ማየት እንፈልጋለን” ብለዋል።
የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚነት ላይ የሁለቱ ወገኖች ከፍተኛ የጦር አዛዦች ች ሌላ ስምምነት ላይ ሲደርሱ ድርድሩን በዋናነት ሲያስተባብሩ የነበሩት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ እርዳታ “ትናንት” መሄድ ነበረበት ብለዋል።
የሰብዓዊ ዕርዳታው ያለ አንዳች ክልከላ በአስቸኳይ ተፈጻሚ እንደሚሆን ተናግረው ነበር።
የእርዳታ ድርጅቶች
በተባበሩት መንግሥት ድርጅት አማካይነት ለመጨረሻ ጊዜ የሰብዓዊ ዕርዳታ በአፋር በኩል ወደ ትግራይ የተላከው ነሐሴ 16/2014 ዓ.ም. ነበር።
ነሐሴ 17 ከመዲናዋ አዲስ አበባ ወደ መቀለ በአየር ሰብዓዊ ዕርዳታ ተልኮ ነበር። የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከሆነ በወቅቱ ከአምስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የረሃብ አደጋ ተጋርጠውባቸዋል ብሎ ነበር።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት ቃል አቀባይ ከሌሎች ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢዎች ጋር በመሆን ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ሠራተኞችን እና ዕርዳታዎችን ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ እየተመካከርን ነው ሲሉ ለቢቢሲ ገልጸዋል።
“ሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ አጋር ድርጅቶች ፍቃድ እንደተሰጠ ከ48 አስከ 72 ሰዓታት ውስጥ ዕርዳታ ለማድረስ ዝግጁ ናቸው” ብለዋል።
ይህም እስካሁን ድረስ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዕርዳታ ጫኝ መኪኖች ወደ ትግራይ እንዲሄዱ ፍቃድ እንዳላገኙ የሚያመላክት ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት እርዳታ ሽረ ከተማ ደርሷል ያሉትም ትክክል እንዳልሆነ በከተማዋ ከሚገኙ የእርዳታ ድርጅት ሠራተኞች ተናግረዋል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
እርዳታ ትግራይ ሲደርስ የነበረው መቼ ነው?
የሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በርስ ከተቀሰቀሰ በኋላ እርዳታ ትግራይ ማድረስ ችግር ሆኖ ቆይቷል።
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ዕርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች በ2013 እና 2014 ዓ.ም. ለተወሰኑ ወራት ዕርዳታ ማቅረብ ችለው ነበር። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ለወራት እርዳታ ወደ ክልሉ ማድረስ አስቸጋሪ ሆኖ ቆይቷል።
ለዚህ ደግሞ ምክንያቶቹ የሰብዓዊ ዕርዳታ በሚተላለፍባቸው መንገዶች ግጭት መኖሩ፣ በርካታ የመንገድ መዘጋቶች እና ፍተሻዎች እንዲሁም የመሠረተ ልማት ውድመቶች ናቸው።
የፌደራሉ መንግሥት እና የክልል ኃይሎች ተቆጣጥረው በያዟቸው አካባቢዎች እርዳታ ለማድረስ ፍቃድ ማግኘት መሠረታዊ ጉዳይ ሆኖ ቆይቷል።
የፌደራሉ መንግሥት በአየር የሚላኩ ዕርዳታዎችም ወደ ትግራይ በቀጥታ ከመሄዳቸው በፊት ለፍተሻ በአዲስ አበባ ማለፍ አለባቸው በማለት ጥብቅ ቁጥጥር ሲያደርግ ቆይቷል።












