ትራምፕ ቲክቶክን የሚገዛ "የቱጃሮች ቡድን" አለኝ አሉ

የፎቶው ባለመብት, Future Publishing via Getty Images
ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በአሜሪካ ውስጥ የብሔራዊ ደህንነት አደጋን ይፈጥራል በሚል የታገደውን ቲክቶክ የሚገዛ "የቱጃሮች ቡድን" አለኝ አሉ።
ትራምፕ፤ ከፎክስ ኒውስ ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ የቪዲዮ ማጋሪያ መተግበሪያውን ለመግዛት ፈቃደኛ የሆኑ "በጣም ሀብታም ሰዎች" አሉ ብለዋል።
"ከሁለት ሳምንት በኋላ እነግራችኋለሁ" ሲል ጠቆም አድርገዋል።
መተግበሪያውን ለመሸጥ የቻይና መንግሥት ይሁንታ ያስፈልጋል።
ነገር ግን ትራምፕ፤ ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ "ያደርጉታል" ብለው እንደሚያስቡ ለፎክስ ኒውስ ተናግረዋል።
ትራምፕ በዚህ ወር ቲክ ቶክ እንዲሸጥ የሚያስገድደው ሕግ ተግባራዊ እንዳይሆን ለሦስተኛ ጊዜ አራዝመዋል።
ለሦስተኛ ጊዜ የተደረገው ማራዘሚያ የቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይትዳንስ በመስከረም 17 ለመሸጥ ስምምነት ላይ እንዲደርስ ይጠይቃል።
ቢቢሲ የቲክቶክን አስተያየት የጠየቀ ቢሆንም ወድያውኑ ምላሽ አላገኘም።
ባለፈው ሚያዝያ ወር ላይ ቲክቶክን ለአንድ አሜሪካዊ ገዢ ለመሸጥ የተደረሰው ስምምነት፤ አሜሪካ ቻይና ላይ የጣለችውን ታሪፍ ተከትሎ በተፈጠረ ውዝግብ ፈርሷል።
ትራምፕ አሁን ገዢዎች አሉኝ ያሉት ከሦስት ወር በፊት ለመግዛት ሲጠብቅ ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ስለመሆኑ ግልጽ የሆነ ነገር የለም።
የአሜሪካ ኮንግረስ ቲክቶክ እንዲሸጥ የሚያስገድድ ሕግ ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር ሲያጸድቅ የመተግበርያው እናት ኩባንያ የአሜሪካ ተጠቃሚዎችን መረጃ ለቻይና መንግሥት አሳልፎ ሊሰጥ ይችላል የሚል ስጋት እንዳለው የገለፀ ቢሆንም ቲክቶክ ግን ስጋቱን ውድቅ አድርጓል።
ትራምፕ በመጀመርያው የሥልጣን ዘመናቸው መተግበሪያውን ተችተውት ነበር።
ነገር ግን በ 2024 ባደረጉት ምርጫ ለማሸነፋቸው እንደ አንድ ምክንያት አድርገው ስለሚመለከቱት አሁን በአሜሪካ ውስጥ ጥቅም ላይ መዋሉን ይደግፋሉ።
ሕጉ በጥር 19 ተግባራዊ መሆን የነበረበት ቢሆንም ነገር ግን ትራምፕ በፊርማቸው በተደጋጋሚ አዘግይተውታል።
ይህም የኮንግረሱ ሕግ አውጪዎችን ተቃውሞ እና ትችት አስከትሏል።
ቲክቶክ ሕጉ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲል ተቃውሞውን አሰምቷል፣ ነገር ግን ለአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ያቀረበው ይግባኝ ውድቅ ተደርጎበታል።















