የስማርት ስልኮች ተፈላጊነት ሊቀንስ ይችላል?

ቀደምት ስልኮች

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/BBC/Getty Images

ስማርት ስልኮች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ ቢመጡም፣ አነስተኛ ጥቅም የሚሰጡ ቀደምት ስልኮችን የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

የስማርት ስልኮችን ገጽታ የለወጠው አይፎን ገበያ ላይ ከዋለ 17 ዓመት ሆኖታል። ያሁኑ ትውልድ ያለ ስማርት ስልክ ሕይወት ምን ሊመስል እንደሚችል አያውቅም።

ዓለምን መዳፍ ላይ መያዝ ምን ማለት እንደሆነ ትውልዱ ተረድቷል።

ሆኖም ግን እነዚህ ስልኮች ትኩረትን የሚሰርቁ፣ እንቅልፍ የሚነሱ፣ ለአእምሮ ጤና እክል የሚዳርጉ ናቸው በሚል እየተተቹ ነው።

ሰዎች ስክሪን ላይ የሚያጠፉትን ጊዜ የሚገድቡ መተግበሪያዎች በመጫን እና በሌሎችም መንገዶች ተጽዕኖውን ለመገደብ ይሞክራሉ።

አንዳንዶች ደግሞ ከስማርት ስልክ በፊት የነበሩ ቀደምት ስልኮችን መያዝ ይመርጣሉ።

እነዚህ ስልኮች ጥሪ መቀበል እና ማድረግ እንዲሁም የጽሑፍ መልዕክት መላክ እና መቀበል ዋነኛ አገልግሎታቸው ነው።

እነዚህን ስልኮች ለልጆቻቸው ደኅንነት ሲሉ ገዝተው የሚሰጡ አልያም ስማርት ስልክ ለመግዛት አቅም ስለሌላቸው የጥንት ስልኮችን የሚመርጡም አልታጡም።

ብዙዎች እንደ ትዊተር እና ኢንስታግራም ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎችን ለመጠቀም ሲሉ ወደ ስማርት ስልክ ቢሸጋገሩም፣ ለጤናቸው አደጋ በሚሆን ደረጃ ላይ ሲደርሱ ከስማርት ስልክ ውጪ ወዳሉ አማራጮች ፊታቸውን ለማዞር ይሞክራሉ።

ይህን ዘገባ ያጠናቀረው የቢቢሲ ዘጋቢ ከሆዜ ብሪዮንስ ጋር የተገናኘው ከኮቪድ ወረርሽን በኋላ ነበር።

ሆዜ ከስማርት ስልክ ውጪ ያሉ ቀደምት ስልኮች (ዳምፎንስ) አፈላልጎ ያገኛል።

የቢቢሲ ዘጋቢ ከስማርት ስልክ ውጪ አማራጮች እየፈለገ ነበር።

“ካት ኤስ 22 የተባለውን ታጣፊ ስልክ ነበር የፈለግኩት። ስማርት ስልክ እና ዳም ስልክ መካከል ያለ ነው” ይላል ዘጋቢው።

ስልኩ እንደ ጉግል ማፕስ ያሉ መተግበሪያዎች አሉት። 69 ዶላር ነው የሚሸጠው።

እንደዚህ ዓይነት ስልኮች አፈላልጎ ማግኘት ቀላል አይደለም። ገበያውም ላይ በብዛት አይገኙም።

ስማርት ስልኮች ገበያውን በተቆጣጠሩበት በዚህ ወቅት፣ ዳም ስልኮችን ማምረት የሚፈልጉ የቴክኖሎጂ ተቋማት ማግኘት ቀላል አይደለም።

ቀደምት ስልኮች

የፎቶው ባለመብት, Serenity Strull/BBC/Getty Images

የምጣኔ ሀብት ጥያቄ

በእርግጥ ቀደምት ስልኮች ገበያው ላይ ፈላጊ አላቸው።

አሜሪካንን እንደ ማሳያ ብንወስድ ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት እነዚህ ስልኮች ከገበያው 2 በመቶ ብቻ ነበር የያዙት።

በዚህ ዓመት መጨረሻ ግን ሽያጫቸው 28 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ ይጠበቃል።

በዚህ ላይ ጥናት ያደረገው ተቋም ‘ካውንተርፖይንት ሪሰርች’ እንደሚለው፣ እነዚህ ስልኮች ለመጠቀም ቀላል እና ርካሽ መሆናቸው ተፈላጊ እንዲሆኑ አስችሏል።

እነዚህ ስልኮች ተፈላጊነታቸው አሁን ካለውም ሊጨምር እንደሚችል ግምት ተቀምጧል።

በቴክሳስ የቢዝነስ ዩኒቨርስቲ የማርኬቲንግ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ጂም ሮበርትስ እንደሚሉት በዋናነት እነዚህ ስልኮች የሚሸጡት በአሜሪካ ነው።

“ተጠቃሚዎች በእነዚህ ስልኮች ከጠበቁት በላይ ወይም በታች ደስተኛ እንደማይሆኑ ይገነዘባሉ። ስልካቸው ላይ ረዥም ጊዜ ማጥፋታቸውን እንደ ችግር ሲያዩ የሚወስዱት አማራጭ ነው” ሲሉ ያስረዳሉ።

‘ስታትስቲካ ማርኬት ኢንሳይትስ’ በዚህ ዓመት በመላው ዓለም የዳም ስልኮች ፍላጎት እስከ 10.6 ቢሊዮን ዶላር እንደሚጨምር ይተነብያል።

የቴክኖሎጂ ተቋማት እነዚህን ስልኮች በማምረት ይህ ነው የሚባል የምጣኔ ሀብት ውጤት ላያገኙባቸው ይችላሉ።

አብዛኞቹ ተቋማት ገቢ የሚያገኙት ከመተግበሪያዎች ወይም ሀርድዌሮች ነው።

ለስማርት ስልኮች የሚጠይቁትን ከፍተኛ ገንዘብ ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅርብ ጊዜ ውስጥ ዳም ስልኮችን ወደማምረት ሊገቡ እንደማይችሉ መረዳት ይቻላል።

ሆዜ ብሪዮንስ ስማርት ስልክ መጠቀም ያቆመው በ2019 ነበር።

“ትልልቅ የቴክኖሎጂ ተቋማት በስማርት ስልክ ላይ የምናጠፋውን ጊዜ የሚያስቀር ምርት አይፈልጉም” ይላል።

ሌላ የስልክ አማራጭ አለ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

‘ፎረስተር ሪሰርች’ የተባለው የጥናት ተቋም ምክትል ፕሬዝዳንት የሆነው ቶማስ ሁሶን እንደሚለው፣ የቴክኖሎጂ ተቋማት በቀጣይ ዓመታት እነዚህን ስልኮች ያመርታሉ ብሎ መጠበቅ ይከብዳል።

ጥያቄው የትርፋማነት ብቻ ሳይሆን ስልኮቹ ዘመናቸው ባለፈ ቁጥር እንደልብ አገልግሎት ለመስጠት አስቸጋሪ መሆናቸውም ጭምር ነው።

የ2ጂ እና 3ጂ አገልግሎት በሚቋረጥበት ወቅት እነዚህ ስልኮች መሥራት አይችሉም ማለት ነው።

የፈላጊዎቻቸው ቁጥርም በጊዜ ሂደት ሊቀንስ ይችል ይሆናል።

ባለሙያው እንደሚያስረዳው የተወሰኑ ጀማሪ ተቋማት በገበያው ያለውን ክፍተት በመሙላት ትርፋማ ለመሆን እየሞከሩ ይገኛሉ።

ለምሳሌ ኒው ዮርክ የሚሠራው ‘ላይት’ ስልክ የኢንተርኔት አገልግሎትን የሚገድብ ነው።

ማኅበራዊ ሚዲያንም ለመቀነስ ይሞክራል።

የላይት አጋር መሥራች ጆ ሆለር እንደሚለው፣ ይህ ስልክ ‘ዳምፎን’ በሚል የሚመረት አይደለም።

“ከቴክኖሎጂ ጋርም አይጻረርም” ይላል።

በ299 ዶላር የሚሸጠውን ይህንን ስልክ በመላው ዓለም ተጠቃሚ እንዲኖረው ማድረግ ነው ግባቸው።

ዋጋው ከስማርት ስልኮች የሚተናነስ አይደለም።

ዘመኑ ያመጣውን ቴክኖሎጂ ችላ ሳይሉ የስማርት ስልክ አገልግሎትን ለመቀነስ በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ የተሻለ ተፈላጊነት አላቸው።

ስልክ መደወል፣ አጭር የጽሑፍ መልዕክት መላክ፣ ካርታ መጠቀም፣ ሙዚቃ መስማት፣ ማስታወሻ መያዝ እና ሌሎችም አገልግሎቶችን ስልኩ ይሰጣል።

‘ፐንክት’ የተባለ ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጥ ስልክ ስዊድን ውስጥ መመረት ጀምሯል።

በ750 ዶላር የሚሸጠው ይህ ስልክ ከስማርት ስልክ ጋር የሚመሳል ሆኖ “ቅንጡ ዳም ስልክ” በሚል ሊገለጽ የሚችል ነው።

የዲጂታል ዓለምን ለመቀነስ በሚፈልጉ ሰዎች ዘንድ እነዚህ ስልኮች ተፈላጊ ናቸው።

ይህን ዘገባ ያዘጋጀው የቢቢሲ ዘጋቢ ብሬናን ዶርቲ የገዛው ስልክ ካት ኤስ 22 ሲሆን፣ የሚያመርተው ቡሊት የተባለው ተቋም ነው።

ስልኩ የሚሰጠው የጥሪ፣ የአጭር ጽሑፍ መልዕክት እና ሌሎችም ቀለል ያሉ አገልግሎቶች መሆኑን በመጥቀስ “አካባቢዬ ላይ የተሻለ ትኩረት እንድሰጥ አስችሎኛል። ማንበብ እና ሙዚቃ ማዳመጥ ላይ ማተኮር ችያለሁ” ሲል ይገልጸዋል።

ሆኖም ግን ስማርት ስልኩ የሚሰጠው ጥቅሞች ሳይናፍቁት አልቀሩም።

ወደ ጋላክሲ ኤ32 ስልኩ ሲመለስ ‘ሚኒማሊስት ፎን’ የተባለ መተግበሪያ ጫነ።

እንደ ዋትስአፕና ሜሴንጀር ያሉ አስፈላጊ መተግበሪያዎችን ብቻ መጠቀም የሚያስችል አሠራር ነው።

ሌሎች “እምብዛም አስፈላጊ ያልሆኑ” መተግበሪያዎችን ስልክ ላይ ከመጠቀም ይቆጥባል።

እነዚህን መተግበሪያዎች ማገድ እንደቻለ የሚናገረው ዘጋቢው “እኔም አልናፍቃቸውም” ሲል ስሜቱን ይገልጻል።