በኢራቅ ጦርነት የአንድ ቤተሰብ አባላትን የገደሉ የአሜሪካ ወታደሮችን ማንነት የሚጠቁም ማስረጃ በቢቢሲ ምርመራ ተገኘ

ሳፋ የኑስ
የምስሉ መግለጫ, የ33 ዓመቷ ሳፋ የኑስ በሃዲታ ከተማ በተፈጸመው ግድያ ሁሉም ቤተሰቧ ሲገደል፤ እርሷ ተርፋለች

"ሁሉም ቤተሰቤ የተገደለው እዚህ ክፍል ውስጥ ነበር" ትላለች ሳፋ የኑስ።

ልጅነቷን ባሳለፈችባት የኢራቋ ሃዲታ ከተማ የሚገኘው መኖሪያ ቤት በር በጥይት ተበሳስቷል። ቤቱ ውስጥ በጀርባ በኩል የሚገኘው መኝታ ቤት በተለያዩ ቀለሞች የፈካ ብርድ ልብስ የተነጠፈበት አልጋን ይዟል። ወላጆቿ በጥይት የተደበደቡት እዚህ ክፍል ውስጥ ነው።

ከ20 ዓመታት በፊት በሕዳር 10/1998 ዓ.ም. የአሜሪካ ወታደሮች ወደ ቤታቸው ሲገቡ በር የከፈተላቸውን አባቷን በጥይት የገደሉት እዚያው ነበር። ሳፋ ከአምስት እህት እና ወንድሞቿ እንዲሁም ከእናት እና አክስቷ ጋር ወታደሮቹን ሽሽት እዚህ ክፍል ውስጥ ተደብቀው ነበር።

በዚያች እድለ ቢስ ቀን ከሳፋ ውጪ በሕይወት የተረፈ አልነበረም። ሁሉም ተገድለዋል።

ከ20 ዓመት በኋላ የቢቢሲ አይ የምርመራ ዘገባ ሁለት የአሜሪካ ወታደሮች በዚህ ድርጊት ውስጥ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚያመለክት ማስረጃ አግኝቷል። የፎረንሲክ ባለሙያዎች እንደሚናገሩት የሳፋን ቤተሰቦች የገደሉት ወታደሮች ለፍርድ አልቀረቡም።

የቢቢሲ ዘገባ ይፋ ያደረገው ማስረጃ በአብዛኛው ከግድያው በኋላ በተሰጡ ቃሎች እና እማኝነቶች ላይ የተመሠረተ ነው።

ይህ ማስረጃ በዕለቱ ስለተፈጸመው ወንጀል የተደረገው የአሜሪካ መንግሥት ምርመራ ግኝት ላይ ጥርጣሬን የሚጭር ነው። የአሜሪካ ወታደሮች ለተጠያቂነት በሚቀርቡበት መንገድ ላይ መሠረታዊ ጥያቄዎችን ያስነሳል።

የሳፋ ቤተሰቦች ላይ የተፈጸመው ግድያ የሃዲታ ጭፍጨፋ ተብሎ የሚታወቀው አስከፊ ክስተት አካል ነው። በዕለቱ የአሜሪካ ወታደሮች ስድስት ሕጻናት እና አራት ሴቶችን ጨምሮ 24 ንጹኃን ኢራቃውያንን ገድለዋል።

ወታደሮች ሦስት ቤቶች ውስጥ በመግባት ያገኙትን በሙሉ በሚባል ደረጃ ገድለዋል። አሽከርካሪ እና ወደ ኮሌጅ ለመሄድ መኪና ውስጥ የነበሩ አራት ተማሪዎችም ከተገደሉት መካከል ናቸው።

አሜሪካ በኢራቅ ከፈጸመችው ወረራ ጋር በተያያዘ ከተካሄዱ የጦር ወንጀል ምርመራዎች ረዥም ጊዜ የፈጀው ይህ ክስተት ቢሆንም አንድም ሰው በግድያ ጥፋተኛ አልተባለም።

በ1998 ዓ.ም. በሃዲታ ከተማ የሳፋ ቤተሰቦች የተገደሉበት ቤት
የምስሉ መግለጫ, በ1998 ዓ.ም. በሃዲታ ከተማ የሳፋ ቤተሰቦች የተገደሉበት ቤት

የአሜሪካ ወታደሮች መንገድ ዳር ቦንብ ከፈነዳ በኋላ ለተከፈተባቸው ተኩስ ምላሽ እንደሰጡ ይናገራሉ። በፍንዳታው አንድ ባልደረባቸው ሲገደል ሁለቱ መቁሰላቸውን ገልጸዋል።

በወቅቱ የ13 ዓመት ልጅ የነበረችው ሳፋ፤ "ምንም ነገር በመፈጸም አልተከሰስንም። ቤቱ ውስጥ እንኳ ምንም መሣሪያ አልነበረንም" ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።

ሳፋ በሕይወት የተረፈችው የሞተች መስላ እህቶቿ እና ወንድሟ አስከሬን ስር በመደበቋ ነው። "ከሙሉ ቤተሰቤ ውስጥ በሕይወት የተረፍኩት እኔ ብቻ ነኝ" ትላለች።

ከዚህ ክስተት ጋር በተያያዘ መጀመሪያ ላይ የተከሰሱት አራት ወታደሮች ነበሩ። ተከሳሾቹ ስለክስተቱ የሰጡት ቃል እርስ በእርሱ የሚጣረስ ነው። ከጊዜ በኋላ የአሜሪካ ወታደራዊ አቃቤ ሕግ በሦስቱ ላይ የመሠረተውን ክስ በማንሳት ከሌላ የሕግ ተጠያቂነት ነጻ የሚያደርጋቸውን ከለላ ሰጥቷቸዋል።

በ2004 ዓ.ም. ለፍርድ የቀረበው ብቸኛው የአሜሪካ ወታደር የቡድኑ መሪ የነበረው ስታፍ ሳርጀንት ፍራንክ ዉትሪች ነው።

ከዚህ በፊት ይፋ ካልሆነ ቪዲዮ ላይ የተወሰደው ይህ ምስል ኸምቤርቶ ሜንዶዛ (የተንበረከከው ወታደር) ምን እንደተፈጠረ ሲያስረዳ ያሳያል

የፎቶው ባለመብት, Michael Epstein

የምስሉ መግለጫ, ከዚህ በፊት ይፋ ካልሆነ ቪዲዮ ላይ የተወሰደው ይህ ምስል ኸምቤርቶ ሜንዶዛ (የተንበረከከው ወታደር) ምን እንደተፈጠረ ሲያስረዳ ያሳያል

ከፍርድ ሂደቱ በፊት የተቀረጸ እና እስካሁን ድረስ ይፋ ያልሆነ አንድ ቪዲዮ ከቡድን አባሉ መካከል በወታደራዊ ማዕረግ ዝቅተኛ ደረጃ ያለው ላንስ ኮርፖራል (ወታደራዊ ማዕረግ) ኸምበርቶ ሜንዶዛ፤ በእነ ሳፋ ቤት ምን እንደተፈጠረ በድርጊት ሲያስረዳ አሳይቷል።

ከድርጊቱ ጋር በተያያዘ ክስ ያልቀረበበት ሜንዶዛ፤ ለወታደሮቹ በር የከፈተውን የሳፋን አባት መግደሉን አምኗል።

"እጁን አይተኸዋል" ሲል ጠበቃ ይጠይቀዋል።

"አዎ፤ አለቃ" ሜንዶዛ ይመልሳል። አክሎም የሳፋ አባል መሣሪያ እንዳልያዘ ይገልጻል።

"ይህም ቢሆን ግን ገድለኸዋል" ጠበቃው በድጋሚ ጠየቀ።

"አዎ፤ አለቃ" የሜንዶዛ ምላሽ ነበር።

ሜንዶዛ በሰጠው ይፋዊ ቃል ላይ፤ ወደ ቤቱ ከገባ በኋላ ሳፋ እና ቤተሰቦቿ የነበሩበትን መኝታ ቤት በር መክፈቱን ያስረዳል። ይሁን እንጂ መኝታ ቤቱ ውስጥ የነበሩት ሴቶች እና ሕጻናት ብቻ መሆናቸውን በመመልከቱ ወደ ውስጥ እንዳልገባ፤ ይልቁንም በሩን ዘግቶ መሄዱን ተናግሯል።

የቡድኑ መሪ በነበረው ዉትሪች የፍርድ ሂደት ላይ የተቀረጸ እና አዲስ የተገኘ የድምጽ ቅጂ ላይ ግን ሜንዶዛ ተቃራኒ ነገር ሲናገር ይደመጣል። በዚህ ድምጽ ቅጂ ላይ ወደ መኝታ ቤቱ 2.4 ሜትር ገደማ መግባቱን ገልጿል።

የፎረንሲክ ባለሙያ የሆነው ማይክል ማሎኒ እንደሚናገረው ማስረጃዎቹ ትልቅ ጠቀሜታ ያላቸው ናቸው። ከክስተቱ አንድ ዓመት በኋላ የናቫል ወንጀል ምርመራ አገልግሎት ግድያዎቹን እንዲመረመር ወደ ሃዲታ ልኮት ነበር። የሳፋ ቤተሰብ አባላት የተገደሉበትን ክፍልም መርምሯል።

ሳፋ ቤተሰቦቿ በተገደሉበት መኝታ ቤት ውስጥ የሞተች መስላ የተኛችበትን ቦታ ስታሳይ
የምስሉ መግለጫ, ሳፋ ቤተሰቦቿ በተገደሉበት መኝታ ቤት ውስጥ የሞተች መስላ የተኛችበትን ቦታ ስታሳይ

በግድያው ወቅት ወታደሮች ክፍሉ ውስጥ ያነሷቸውን ፎቶዎችን ተጠቅሞ ባደረገው ምርመራ፤ ሁለት ሠራዊቱ አባላት ወደ ክፍሉ ገብተው ሴቶች እና ሕጻናትን ገድለዋል የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል።

ማሎኒ፤ ሜንዶዛ ወደ ክፍሉ መግባቱን የተናገረበትን የድምጽ ቅጂ ቢቢሲ ባሰማው ወቅት "እያዳመጥነው ያለነው፤ ይሄ ለእኔ አስገራሚ ነገር ነው። ከዚህ ቀደም ጭራሽኑ አልሰማሁትም ነበር" ብሏል።

የድምጽ ቅጂው ላይ የሚሰማው ንግግር፤ እርሱ ምርመራ ካደረገ በኋላ የመጀመሪያው ገዳይ የአልጋው እግር አጠገብ ቆሞ ነበር በማለት የሰጠው ድምዳሜ የሚያሳይ መሆኑንም አክሏል።

"እኔ ብትጠይቀኝ፤ 'ይሄ ድርጊቱን ስለመፈጸሙ እየተናዘዘ የሚያሳይ ነው?' እልሃለሁ። ሜንዶዛ የጥይቱ ቃታ ከመሳብ ውጪ ስለ ሁሉም ነገር ተናዝዟል"

ሳፋ ከግድያው አንድ ዓመት በኋላ ለወታደራዊ አቃቤ ሕጎች የሰጠችው ምስክርነት በፍርድ ሂደቱ ወቅት አልቀረበም።

ሳፋ በዚህ የእማኝነት ቃሏ ላይ ወታደሩ የመኝታ ቤቱን በር የከፈተው ወታደር ፈንጂ እንደወረወረ፤ ነገር ግን እንዳልፈነዳ ትናገራለች። ከዚያም ይኸው ወታደር ወደ ክፍሉ ገብቶ ቤተሰቦቿ ላይ ተኩስ መክፈቱን ታስረዳለች።

ቢቢሲ ያገኛቸው ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት በሩን መክፈቱን የገለጸው ብቸኛው ሰው ሜንዶዛ ነው።

ሳፋ በ14 ዓመቷ ምስክርነት ለመስጠት ቃለ መሃላ ስትፈጸም

የፎቶው ባለመብት, US Marine Corps

የምስሉ መግለጫ, ሳፋ በ14 ዓመቷ ምስክርነት ለመስጠት ቃለ መሃላ ስትፈጸም
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የቡድኑ አባል ነበረው ሌላኛው ወታደር ላንስ ኮርፖራል ስቴፈን ታተም በበኩሉ ተኩሱ ውስጥ መሳተፉን አልካደም። ይሁን እንጂ ወደ መኝታ ቤቱ የገባው የቡድኑ መሪ የሆነውን ዉትሪችን ተከትሎ መሆኑን ተናግሯል።

ወታደሩ መጀመሪያ በሰጠው ቃል ላይ በደንብ ለመመልከት አስቸጋሪ ስለነበር ክፍሉ ውስጥ ሴቶች እና ሕጻናት መኖራቸውን እንዳላወቀ ገልጿል። ታተም ከዚያ በኋላ የሰጣቸው እና ቢቢሲ ያገኛቸው ሌሎች ምስክርነቶች ላይ ግን የተለየ ነገር መናገሩን አሳይተዋል።

"ሕጻናቱ ክፍሉ ውስጥ መንበርከካቸውን ተመለከትኩ። ትክክለኛ ቁጥሩን አላስታውስም፥ ነገር ግን ብዙ ነበሩ። ሁለት ጊዜ ደረት ላይ እና ሁለት ጊዜ ጭንቅላት ላይ እንድተኩስ ነው የሰለጠንኩት፤ የተከተልኩት የተሰጠኝን ስልጠና ነው" ሲል በሚያዝያ 1999 ዓ.ም. በተካሄደ ምርመራ ወቅት ተናግሯል።

ከአንድ ወር በኋላ በሰጠው ሌላ ቃል ላይ "ከመተኮሱ በፊት ክፍሉ ውስጥ የነበሩት ሴቶች እና ሕጻናት መሆናቸውን በትክክል ለይቶ" እንደነበር ገልጿል።

ከሳምንት በኋላ ደግሞ "የተኮስኩበትን ልጅ የተመለከትኩት እዚህ ጋር ነበር። ሕጻን መሆኑን ባውቅም ተኩሼበታለሁ" በማለት አጭር ጸጉር ያለው ልጅ ነጭ ቲሸርት ለብሶ አልጋ ላይ ቆሞ እንደነበር አስታውሷል።

የታተም ጠበቃ፤ ኋላ ላይ የተመዘገቡት ምስክርነቶች የተሰጡት በጫና ውስጥ እንደሆነ በመግለጽ ተከላክለዋል። በመጋቢት 1999 ታተም ላይ የተመሰረቱ ክሶች የተነሱ ሲሆን በዉትሪች የፍርድ ሂደት ወቅትም ምስክርነቶቹ ውድቅ ተደርገዋል።

የፎረንሲክ ባለሙያው ማይክል ማሎኒ በበኩሉ እነዚህ የእማኝነት ቃሎች በሳፋ ቤተሰብ ላይ ግድያ የፈጸሙት ሜንዶዛ እና ታተም መሆናቸውም እንደሚያሳዩ ይናገራል። ሜንዶዛ በቅድሚያ ወደ ክፍሉ ገብቷል፤ ታተምም ተከትሎት "አልጋው ጫፍ ዙሪያ ተኩሷል" ብሎ ያምናል።

ቢቢሲ ውንጀላዎቹን ለሜንዶዛ እና ታተም አቅርቧል። ሜንዶዛ ምላሽ አልሰጠም። አስቀድሞ የሳፋን አባት መግደሉን፤ ይህንን ያደረገው ግን የተሰጠውን ትዕዛዝ ተከትሎ መሆኑን አምኖ ነበር። ሜንዶዛ ወንጀል ተጠያቂነት አልቀረበበትም።

ታተም ደግሞ በጠበቃው በኩል በሰጠው ምላሽ በሃዲታ ከተማ የተፈጠሩ ነገሮች በሙሉ ወደ ኋላ መተው እንደሚፈልግ ገልጿል። ታተም በሳፋ ቤት ተኩስ ከከፈቱ ወታደሮች አንድ መሆኑን የገለጸበትን የምስክርነት ቃል አልሻረም።

የቡድን መሪ የነበረው ፍራንክ ዉትሪች ከተፈጸሙት ግድያዎች ጋር በተያያዘ ለፍርድ የቀረበ ብቸኛው ሰው ነው

የፎቶው ባለመብት, Michael Epstein

የምስሉ መግለጫ, የቡድን መሪ የነበረው ፍራንክ ዉትሪች ከተፈጸሙት ግድያዎች ጋር በተያያዘ ለፍርድ የቀረበ ብቸኛው ሰው ነው። ኋላም ድርጊቱን መፈጸሙን በማመኑ የክስ ሂደቱ ተቋርጧል

የፎረንሲክ ባለሙያው ማሎኒ፤ በፍርድ ሂደቱ ላይ "ዉትሬች ዋነኛው ተኳሽ ሆኖ እንዲቀርብ እንደተፈለገ" ይናገራል። ማሎኒ ግድያውን በተመለከተ ባደረገው ምርመራ ስለደረሰበት ድምዳሜ ምስክርነት ለመስጠት ከመቻሉ በፊት የፍርድ ሂደቱ መጠናቀቁን ያስታውሳል።

ውትሬች፤ በወቅቱ በእነ ሳፋ ቤት ምን እንደተፈጠረ እንደማያስታውስ የተናገረ ሲሆን ከኃላፊነት በመዘናጋት ድርጊት ለቀረበበት ክስ ጥፋተኝነቱን አምኗል። ዉትሬች ላይ ቀረበው ክስ በቀጥታ ግድያዎቹ ውስጥ ከመሳተፍ ጋር የተያያዘ አይደለም።

በዉትሬች ክስ ወታደራዊ ጠበቃ የነበረው የቀድሞ ወታደር ሃይታም ፋራጅ፤ በተከሳሹ ላይ የተጣለበው ቅጣት "የፍጥነት ወሰን ጥሰው ለሚያሽከረክሩ ሰዎች" የሚሰጥ አይነት ቀላል መቀጮ መሆኑ በማንሳት ተችቷል።

የዉትሬች ዋና ጠበቃ ኒል ፐኬት በበኩሉ በደንበኛው ላይ የተደረገው ምርመራ እና የቀረበው ክስ በሙሉ "እርባና ቢስ" እንደሆነ ገልጿል። "ክሱ ለሌሎች ምስክሮች ያለመከሰስ መብት ሰጥቷል፤ የቀረበባቸውን ክስም ውድቅ አድርጓል" ብሏል።

ወታደራዊ ጠበቃው ሃይታም ፋራጅ የክስ ሂደቱ ክፍተቶች የነበሩበት እንደሆነ ይስማማል። "መንግሥት ሰዎች እንዲመጡ እና እንዲዋሹ ከፍሏቸዋል። ክፍያውም ያለመከሰስ መብት ነበር። እንዲህ አድርገው ነው የሕግ ሂደቱን የተጠቀሙበት" ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።

የፍርድ ሂደቱ "ለተጎጂዎች ድምጽ ለመሆን የተካሄደ እንዳልነበረ" በማንሳትም ወቅሷል።

አሁንም ድረስ ሃዲታ ውስጥ የምትኖረው ሳፋ፤ አንዲት ሴት እና ሁለት ወን ድልጆች አሏት
የምስሉ መግለጫ, አሁንም ድረስ ሃዲታ ውስጥ የምትኖረው ሳፋ፤ አንዲት ሴት እና ሁለት ወን ድልጆች አሏት

አሜሪካ ጦር በበኩሉ የክስ ሂደቱ ወታደራዊ ፍትሕ ሕግ መሠረት የተከናወነ እንዲሁም ፍትሐዊ እና ለሕዝብ ክፍት እንደነበር በመግለጽ ለቢቢሲ ምላሽ ሰጥቷል። ግዙፍ አዲስ፣ ያልተመረመረ እና በፍርድ ሂደት ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል ማስረጃ እስካላገኘ ድረስ በድጋሚ ምርመራ እንደማከፍት አስታውቋል።

33 ዓመት የሆናት ሳፋ ከሦስት ልጆቿ ጋር እዚያው በሃዲታ ትኖራለች። በቤተሰቧ ግድያ እንዴት አንድም ወታደር እንዳልተቀጣ ለመረዳት እንደምትቸገር ታነሳለች።

የሜንዶዛን ቪዲዮ ስትመለከት "ክስተቱ ከተፈጠረበት ጊዜ ጀምሮ ሊታሰር ይገባው ነበር፤ የቀን ብርሃንን ለማየት እንዳይችል ሊደረግ ይገባ ነበር" ስትል በምሬት ተናግራለች።

"[የሚሰማኝ] ባለፈው ዓመት እንደተፈጠረ ሆኖ ነው። አሁንም ስለእሱ አስባለሁ" ስትል ቤተሰቦቿ ስለተገደሉበት ቀን ትናገራለች።

"ይህንን ያደረጉት ተጠያቂ እንዲሆኑ እና በሕግ እንዲቀጡ እፈልጋለሁ። ለፍርድ ሳይቀርቡ 20 ዓመት ገደማ ሆኖታል። ይህ ትልቅ ወንጀል ነው" ስትል አሁንም ተጠያቂነት እንዲሰፍን ትማጸናለች።