የቢቢሲ የምርመራ ዘገባን ተከትሎ ታዳኙ ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪ በቁጥጥር ስር ዋለ

ባርዛን ማጂድ

የቢቢሲ ምርመራ ዘገባን ተከትሎ በአውሮፓ በጣም ተፈላጊ የሆነው ህገወጥ የሰዎች አዘዋዋሪው ኢራቅ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።

ባርዛን ማጂድ እሑድ ጠዋት በኢራቋ ኩርዲስታን ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉን አንድ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣን ተናግረዋል።

ግለሰቡ ከአጋሮቹ ጋር በመሆን ለበርካታ ዓመታት በእንግሊዝ ቻናል በኩል በጀልባ እና በጭነት መኪኖች ስደተኞችን በህገወጥ በማዘዋወር ይታወቅ ነበር።

ቢቢሲ ‘ስኮርፒዮን’ (ጊንጡ) በመባልም የሚታወቀውን ማጂድን በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞችን በህገወጥ መንገድ እንዳጓጓዘ በሚታመንባት ሱለይማንያ ከተማ ድረስ ተከታትሎ አግኝቶታል።

“ምናልባት አንድ ሺህ ምናልባትም 10 ሺህ ሊሆኑ ይችላል። ስላልቆጠርኩ በትክክል አላውቀውም” ብሏል ስላዘዋወራቸው ሰዎች ቁጥር ሲናገር።

ማጂድን በቁጥጥር ስር ለመዋል የቢቢሲ ምርመራን መጠቀማቸውን የኩርዲስታን ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ባለሥልጣኑ "ዛሬ ጠዋት 1 ሰዓት ላይ በቁጥጥር ስር የዋለው ከቤቱ ደጃፍ ነው። ከቤቱ በወጣበት ቅጽበት ያለምንም ችግር ነው የያዙት" ብለዋል ።

"በመጀመሪያ በእሱ ላይ የሚቀርቡትን ክሶች እዚህ እየተመለከትን ነው። ቀጥለን ከአውሮፓ ፖሊሶች እና አቃብያነ ህግ ጋር እሱን ለመክሰስ በሚቀርበው ጉዳይ ላይ እንወያያለን።”

የዩናይትድ ኪንግደም ብሔራዊ የወንጀል ኤጀንሲ (ኤንሲኤ) ግለሰቡ በቁጥጥር ስር መዋሉን አረጋግጧል።

"ቢቢሲ ጉዳዩን ይፋ በማውጣቱ እናመሰግናለን። ሰዎችን ወደ እንግሊዝ በማዘዋወር ላይ የተሰማሩ የወንጀል መረቦችን ለመበጣጠስ እና ለመስበር የምንችለውን ሁሉ ለማድረግ ቆርጠናል” ሲል መግለጫው አክሏል።

እአአ ከ2016 እስ 2021 መካከል ባለው ጊዜ የስኮርፒዮን ቡድን በአውሮፓ እና በእንግሊዝ መካከል ያለውን አብዛኛውን የሰዎች ህገ ወጥ ዝውውር እንደተቆጣጠረ ይታመናል።

ሁለት ዓመት በፈጀ ዓለም አቀፍ የፖሊስ ዘመቻ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በፈረንሳይ እና በቤልጂየም ፍርድ ቤቶች 26 የቡድኑ አባላት ላይ የቅጣት ውሳኔ ተላልፍቧቸዋል።

ስኮርፒዮን ግን ለመደበቅ ችሎ ነበር።

እሱ በሌለበት በቤልጂየም ፍርድ ቤት 121 ሰዎችን በማዘዋወር ወንጀል ተከሷል። በኋላም የ10 ዓመት እስራት እና 968 ሺህ ዩሮ ቅጣት ተበይኖበት ነበር።

ባርዛን ማጂድ ሜካኒክ ሆኖ እንግሊዝ ውስጥ ይሠራ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Facebook

ቢቢሲ እስኪያገኘው ድረስ ስኮርፒዮን የት እንዳለ አይታወቀም ነበር።

በሚያዝያ ወር በስልክ በነበረ ቆይታ ማጂድ በባሕር ሲጓዙ ለሰመጡ ስደተኞች ብዙም ርህራሄ ያለው አይመስልም ነበር።

"መጨረሻህን አምላክ ያውቃል። ይህ ግን አንዳንድ ጊዜ የአንተም ጥፋት ሊሆን ይችላል። አምላክ በጀልባ ሆናችሁ አቋርጡ አይልም" ብሏል።

በመጨረሻም ከቢቢሲ ጋር ሱለይማንያ በሚገኝ የገበያ አዳራሽ ለመገናኘት ፈቃደኛ ሆነ።

ከቢቢሲ ጋር በነበረው ቆይታ በዚህ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር የወንጀል መረብ ውስጥ ትልቅ ሚና የለኝም ሲልም ቃሉን ሰጥቷል። ሌሎች የቡድኑ አባላት እሱን ተጠያቂ ለማድረግ ሞክረው እንደነበርም ተናግሯል።

"የተወሰኑ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሲውሉ 'እኛ ለእሱ እየሠራን ነበር የሚል ምላሽ ሰጥተዋል ይህንንም ያሉት ቅጣቱ እንዲቀንስላቸው ፈልገው ነው።” ብሏል

በመቀጠልም ማጂድ ከስደተኞች ጋር የሚሠራውን እና ከቢቢሲ ጋር በምርመራው ላይ የተሳተፈውን የቀድሞ የጦር አባል ሮብ ላውሪንን በሱለይማንያ ያደረገውን የገንዘብ ልውውጥ እንዲያይ ጋበዘው።

“ማንም አላስገደዳቸው። ፈልገው ነው። እባካችሁ ይህን አድርጉልን እያሉ አዘዋዋሪዎችን እየለመኑ ነበር። ... አዘዋዋሪዎች ለአምላክ ሲሉ ሌላ አገር ይሰዷቸዋል። ከዚያ የማይሆኑ ነገሮች ማለት ይጀምራሉ” ብሏል።

በቤልጂየም የሚገኘው የአቃቤ ህግ ቢሮ አባል የሆኑት አን ሉኮቪያክ ግለሰቡ በቁጥጥር ስር የመዋሉን ዜና በደስታ ተቀብለዋል።

“እሱ በአካል ተገኝቶ መልስ እየሰጠ በመጨረሻ በዚህ ጉዳይ ላይ ፍትህ ሲገኝ የማየት ዕድል አለን።" ብለዋል።