አሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳይ ለምን በጥብቅ ያሳስባታል?

የአሜሪካ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት ወታደሮቿን በመካከለኛው ምሥራቅ ከማሰማራቷ በተጨማሪ ወታደራዊ ሰፈሮችም አሏት

አሜሪካ ላለፉት በርካታ አስርት ዓመታት በኢራቅ ላይ ወረራ በመፈጸም፣ ኢስላሚክ ስቴትን (አይኤስ) በመዋጋት፣ ለእስራኤል እና ለሳዑዲ አረቢያ የጦር መሳሪያዎችን ማቅረብን ጨምሮ በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ በቀጥታ ጣልቃ ስትገባ ቆይታለች።

ለመሆኑ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላት ፍላጎት ምንድነው? በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በቀጠናው ጉዳዮች ውስጥ እንድትሳተፍ የሚያደርጋት ነገር ምንድን ነው?

አሜሪካ በአሁኑ ወቅት ከግብፅ እስከ አፍጋኒስታን ባሉ የቀጠናው አገራት የተሰማሩ ከ40 ሺህ ያላነሱ ወታደሮች አሏት።

እአአ 2007 በኢራቅ ብቻ ከ160ሺህ የማያንሱ ወታደሮችን ነበሯት።

አሜሪካ ልክ እንደ የአገር ውስጥ የግል ጉዳይዋ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ የምትገባው ከነዳጅ/ከኃይል አቅርቦት፣ ከንግድ ሥራዎች ጋር በተያያዙ ባሏት ብሔራዊ ጥቆሞቿን ምክንያት ብቻ እንዳልሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን ብሔራዊ ጥቅሟን ከማስከበር ባለፈ እስራኤል በቀጠናው መገኘቷ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ጉዳዮች በቀጥታ እንድትሳተፍ ከሚያደርጓት ምክንያቶች ዋነኛው ነው ይላሉ።

ነዳጅ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ነዳጅ/የኃይል አቅርቦት

መካከለኛው ምሥራቅ በዓለማችን ሰፊ የሆነ የነዳጅ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ መገኛ ስፍራ ነው።

እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኢራን፣ ኢራቅ፣ ኩዌት እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ አሜሪካ በቀጠናው ያላትን ፖሊሲ ቅርጽ የሚቀይሩ አገራት ሆነው ቆይተዋል።

ይሁን እንጂ ባለፉት 15 ዓመታት አሜሪካ የራሷን የነዳጅ እና የጋዝ ምርት በመጨመሯ ከውጭ አገራት በሚገባ ምርት ላይ ያላትን ጥገኝነት ቀንሷል።

ይሁን እንጂ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ የተያያዘ ጉዳይም አለ። በመካከለኛው ምሥራቅ የነዳጅ ምርት እና አቅርቦት ላይ አንዳች እክል ቢያጋጥም የዓለም የነዳጅ ዋጋ ላይ ለውጥ በማምጣት የኢኮኖሚ መናጋትን ያስከትላል።

ስለዚህም የዓለም ምጣኔ ሀብት መረጋጋት አሜሪካ በዓለም ዙሪያ ያላትን ሚና የሚያጠናክረው በመሆኑ የአረቡ ዓለም የሚያመርተው ነዳጅ ለገበያ መቅረቡን በቅርበት ትከታተላለች።

ከዚህ በተጨማሪም አሜሪካ በንግዱ ዓለም እንደ ባላንጣ የምትመለከታት የቻይና ዋነኛ የነዳጅ ምንጭ መካከለኛው ምሥራቅ ነው።

ለአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅን መቆጣጠር ማለት በእጅ አዙር የቻይናን የነዳጅ አቅርቦት መቆጣጠር ማለት ነው።

በሁቲዎች ጥቃት የሰጠመች መርከብ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሁቲ አማጺያን ባለፉት ወራት በቀይ ባሕር ላይ በሚተላለፉ መርከቦች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ስጋት ፈጥረዋል

የኢኮኖሚ ፍላጎት/የንግድ መተላለፊያ

አሜሪካ ምርት እና አገልግሎቷን ከምትሸጥባቸው ቀጠናዎች መካከል የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚጠቀሱ ናቸው። በተለይ ደግሞ አሜሪካ ሠራሽ ወታደራዊ ቁሶች በመካከለኛው ምሥራቅ በከፍተኛ መጠን ተፈላጊነት አላቸው።

እንደ ስቶኮልም ኢንተርናሽናል ፒስ ሪሰርች ኢንስቲትዩት ከሆነ ከእአአ 2019 እስከ 2023 ከፍተኛ መጠን ያለውን አሜሪካ ሠራሽ ወታደራዊ ቁሶችን ከተረከቡት የዓለም አካባቢዎች ቀዳሚው ይኽው መካከለኛው ምሥራቅ ነው።

ኢንስቲትዩቱ እንዳመለከተው ከአሜሪካ አጠቃላይ ወታደራዊ ሽያጭ 38 በመቶ የሚሆነው የተላከው ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታር፣ ኩዌት እና እስራኤል ነው።

ከዚህ በተጨማሪ መካከለኛው ምሥራቅ ቁልፍ የሆነ የንግድ መተላለፊያ ቀጠና ነው። የጋዛውን ጦርነት ተከትሎ ሁቲዎች በቀይ ባሕር ላይ የሚያልፉ የንግድ መርከቦች ላይ ጥቃት ከፍተው በንግድ እንቅስቃሴው ላይ እክል ፈጥረው ነበር።

ካርታ

በየዓመቱ 17 ሺህ በላይ መርከቦች ምግብ፣ ነዳጅ፣ መድኃኒት እና ሌሎች መሠረታዊ ቁሶችን ጭነው በቀይ ባሕር በኩል ያልፋሉ። ይህም የዓለምን አጠቃላይ ንግድ 12 በመቶ ያህል የሚሸፍን ነው።

ይህን የንግድ መስመር ያወከውን የሁቲ አማጺያን ጥቃትን ለማሰቆም አሜሪካ እርምጃ እየወሰደች ትገኛለች።

ከዚህ ውጪ ለአውሮፓ፣ ለእሲያ እና ለአፍሪካ ቅርበት ባለው መካከለኛው ምሥራቅ፤ አሜሪካ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮችን በማቋቋም እና እንደ አስፈላጊነቱ በቀጠናው ያላትን ጦር ሰፈር አጠናክራ ማቆየትን ትሻለች።

በአሁኑ ወቅት በባህሬን፣ በኳታር እና በኩዌት የጦር ሰፈሮች ያላት አሜሪካ፤ በቀጠናው ፖለቲካዊ መረጋጋት እንዲሰፍን በቅርብ ለመከታተል የጦር ሰፈሮች ትልቅ ሚና እንደሚጫወቱ የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት የመካከለኛው ምሥራቅ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሜሪሳ ከሁርማ ይናገራሉ።

የጋዛ ጦርነት የመካከለኛው ምሥራቅ ሁኔታዎች በፍጥነት ሊቀያየሩበት የሚችል ቀጠና መሆኑን አሳይቶናል የሚሉት ሜሪሳ፤ የፍልስጤም እና እስራኤል ጦርነት እንዲሁም በቀጠናው የኢራን ወታደራዊ ኃይል መስፋፋት ለአሜሪካ የደኅንነት ስጋት ሆኖ ይቀጥላል ይላሉ።

የአሜሪካ ወታደሮች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፀረ ሸብር ዘመቻ

የመካከለኛው ምሥራቅ ኢንስቲትዩት ባልደረባ የሆኑት ካሊድ ኤልጊንዲይ አሜሪካ በቀጠናው ጦሯን ካሰፈረችበት መካከል አንዱ የፀረ-ሸብር ዘመቻዎችን ለማካሄድ ነው ይላሉ።

ካሊድ ምንም እንኳ ኃያሏ አገር አሸባሪዎችን ለማጥፋት ጦሯን ብታዘምትም፤ የአሜሪካ ወታደሮች በመካከለኛው ምሥራቅ መስፈር “ጽንፈኛ ቡድኖች እንዲፈጠሩ” ሌላ ምክንያት ሆኗል ይላሉ።

ባለሙያው ለዚህ እንደማሳያ አል-ቃኢዳ ከ20 ዓመታት በፊት በአሜሪካ ምድር ላይ የፈጸመው የመስከረም 11ዱን ጥቃት የፈጸመው የአሜሪካ ወታደሮች በሳዑዲ አረቢያ በመስፈራቸው ምክንያት መሆኑን መጥቀሱ ያወሳል።

አሜሪካ አል-ቃኢዳን ብቻ ሳይሆን ከሌሎች የአካባቢው አገራት እና ኃይሎች ጋር በመተባበር ኢስላሚክ ስቴትን በኢራቅ እና ሶሪያ ተዋግታለች።

የአሜሪካ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እስራኤል

ባለፉት 60 ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ከየትኛውም ነገር በላይ የእስራኤልን ጉዳይ አሜሪካ ቅድሚያ የምትሰጠው አጃንዳ ሆኖ ቆይቷል።

አሜሪካ እስራኤል በመካከለኛው ምሥራቅ አለችኝ የምትላት አጋር ከመሆኗም በላይ በዋሽንግተን ዲሲ ያሉ ባለሥልጣናት ለቴል አቪቭ ድጋፍ እንዲያደርጉ ትልቅ ጫና ይደርስባቸዋል።

አሜሪካ አጋር የምትላት እስራኤል በቀጠናው ባሉ በርካታ የአረብ አገራት እንደ ጠላት የምትታይ ናት። ይህን ለመቀየርም ዋሽንግተን የማሸማገል ሥራዎችን ስትሠራ ቆይታለች።

እስራኤል በአሜሪካ ጥረት ከግብፅ፣ ከተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ እና ከባህሬ ጋር ያላትን ግንኙነት እንድታሻሽል ዕድል ተፈጥሮላታል። ሐማስ የፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ቢደናቀፍም ከሌሎች አረብ አገራት ጋርም መልካም ግንኙነት እንድትመሠርት ስትረዳት ቆይታለች።

አሜሪካ እስራኤልን በዲፕሎማሲው መስክ ከመደገፍ ባሻገር በቀጥታ ከጠላቶቿ ከሚሰነዘርባት ጥቃቶችም ለመጠበቅ ያላትን ቁርጠኝነት ጨምር አሳይታለች።

በቅርቡ ሐማስ ድንገተኛውን ጥቃት እስራኤል ላይ ሲፈጽም አሜሪካ የጦር መርከቦቿን ወደ እስራኤል መላኳ ይታወሳል። ኢራን የሚሳኤል እና የድሮን ጥቃቶችን ስትፈጽምባትም አሜሪካ አጋሮቿን አስተባብራ ተከላክላታለች።

የአሜሪካ ወታደር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በቀጣይስ?

አንዳንድ ተንታኞች አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን የጦር ስምሪት ብትቀንስ ሩሲያ እና ቻይና በቦታዋ እንዲተኩ ዕድል ይሰጣል ይላሉ።

ይሁን እንጂ ተንታኞች አሜሪካ እግሯን ከመካከለኛው ምሥራቅ ታወጣለች ብለው አይጠብቁም።

የአሜሪካ ዜጎች በመካከለኛው ምሥራቅ የአገራቸው ተሳትፎ እንዲቀንስ ካላቸው ፍላጎት የተነሳ ምናልባት አሜሪካ ወታደሮቿን በቀጠናው ከማስፈር ይልቅ ዘመን አፈራሽ ወታደራዊ ቁሶችን በመጠቀም በአካባቢው ያላትን ተጽእኖ ማስቀጠልን እንደ አማራጭ ልትወስድ ትችላለች ይላሉ።

በሌላ በኩል አሜሪካ ሙሉ በሙሉ ከመካከለኛው ምሥራቅ ወጥታ ትኩረቷን ወደ ሌላ ስፍራ ማድረግ አለባት የሚሉ አልጠፉም።

መቀመጫውን ዋሽንግተን ዲሲ ያደረገው የስቲመን ሴንተር ባልደረባ የሆኑት ኬሊ ግሪኮ አሜሪካ ከመካከለኛው ምሥራቅ ጠቅልላ ወጥታ ትኩረቷን ኢንዶ-ፓስፊክ ላይ ማድረግ አለባት ይላሉ።

ኬሊ አሜሪካ ባለፉት አስርት ዓመታት በመካከለኛው ምሥራቅ ያደረገችው ጣልቃ ገብነት በቀጠናው አሜሪካ ጠል ስሜቶች እንዲያድጉ አድርገዋል ነው በማለት የአሜሪካንን የመካከለኛው ምሥራቅ ቆይታ አስፈላጊነትን ይሞግታሉ።