ሦስት ልጆችን የተገላገለችው ኬንያዊት ለልጆቿ በአርሰናል ተጫዋቾች ስምን ሰጠች

የፎቶው ባለመብት, arsenal.com
ሦስት ልጆችን በአንድ ጊዜ በሰላም የተገላገለችው ኬንያዊት እናት ልጆቿኝ በአርሰናል ተጫዋቾች ስም መሰየሟ አነጋጋሪ ሆኗል።
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊጉ ክለብ አርሰናል ደጋፊ የሆነችው ኢፓካን ኢካሌ ሦስቱን ልጆቿን ጋብርኤል ማርቲኔሊ፣ ጋብርኤል ጄሱስ እና ጋብርኤል ማጋሌዥ ብላቸዋለች።
በቱርካና ግዛት ነዋሪ የሆነችው እናት ሦስት ልጇችን ከተገላገለች በኋላ በመልካም ጤንነት ላይ እንደምትገኝ የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ዘ ስታር የተሰኘው ጋዜጣ ባወጣው ዘገባ የአርሰናል ደጋፊ የሆኑ ኬንያውያን አራሷ ሕክምና ወደ ምታገኝበት ሆስፒታል እየሄዱ እየጎበኟት ነው ብሏል።
ጋዜጣው አክሎም ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች አራስ ጥየቃ ከመሄድ ባለፈው ገንዘብ አዋጥተው አስፈላጊ መገለግያዎችን በመግዛት እንዳበረከቱላት አስነብቧል።
ከመድፈኞቹ ደጋፊዎች የህጻናት የዱቄት ወተት፣ ልብስ፣ የገላ ሳሙና፣ ዳይፐር እና የተለያዩ አልባሳት በሥጦታ የቀረበላት እናት ደስታዋን ገልጣለች።
እናትየው ሦስት ልጆች የማሳደግ አቅም እንደሌላት የተረዱት የአርሰናል ደጋፊዎች በየጊዜው እየተመላለሱ ድጋፍ ለመስጠት ቃል ገብተዋል።
የ30 ዓመቷ እናት ሁለት ሴቶች እና አንድ ወንድ ከተገላገለች በኋላ ጋብርኤል የሚለውን ስም መርጣ፤ ማርቲኔሊ፣ ጄሱስ እና ማጋሌዥን ለልጆቿ አከፋፍላለች።
በብራዚላውያኑ የአርሰናል ተጫዋቾች ስም ልጆቿን የሰየመችው እናት ከሰል እየሸጠች ሕይወቷን የምትገፋ ሴት ናት።
ይህን የሰሙት ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች ለእናቲቱ የአራስ መጠየቂያ ድጋፍ ከማድረግ ባለፈ ዘላቂ እርዳታ ለማድረግ እየታሩ ነው።
በኬንያ የአርሰናል ደጋፊዎች የማኅበራዊ ሚድያ ገፅ ዜናውን በተለያዩ አውታሮቹ አጋርቶታል።
ኬንያውያን የአርሰናል እና የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊዎች የዜና ርዕስ ሲሆኑ ይህ የመጀመሪያው ጊዜ አይደለም።
ደጋፊዎቹ ተሰባስበው የታመመ በመጠየቅ እና የደም ልገሳ በማድረግ ይታወቃሉ።
ከሳምንታት በፊት በመቶዎች የሚቆጠሩ ኬንያውያን የአርሰናል ደጋፊዎች በመዲናይቱ ናይሮቢ ተሰባስበው ለቡድናቸው ፀሎት ማድረጋቸው ይታወሳል።
በፕሪሚዬር ሊጉ ባለፈው ጥር አርሰናል ክሪስታል ፓላስን 5 ለምንም ከረታ በኋላ ነው ደጋፊዎች ቤተ-እምነት ተሰባስበው፤ በአርሰናል ማሊያ ደምቀው በፀሎት፣ በመዝሙር እና በጭፈራ ደስታቸውን የገለጡት።
ደጋፊዎቹ ፀሎታቸውን ወደ ፈጣሪያቸው ሲያደርሱ አርሰናል የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ዋንጫ እንዲያነሳ ተማጽነዋል።
ከወራት በፊት ደግሞ አንድ ኬንያዊ የማንቸስተር ዩናይትድ ደጋፊ “ቡድኔ ያሸንፋል” ብሎ ተወራርዶ በመረታቱ 15 እንቁላሎችን ውጦ ሆስፒታል መግባቱ መነጋሪያ ሆኖ ነበር።
አርሰናል በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ የደረጃ ሠንጠረዥ ላይ በ58 ነጥብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።















