ጋና የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን በተመለከተ ጠንካራ ሕግ አጸደቀች

የፎቶው ባለመብት, AFP
የጋና ፓርላማ ከተመሳሳይ ፆታ ግንኙነቶች እና በዚህ ዙሪያ ከሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ጋር በተያያዘ በሚከሰሱ ሰዎች ላይ ጠንከር ባለ እስር የሚቀጣ ሕግ አጸደቀ።
አዲሱ ሕግ በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ መሆናቸውን የሚገልጹ እንዲሁም ሆነው የተገኙ ሰዎችን እስከ ሦስት ዓመት በሚደርስ እስር፣ ቡድኖችን የሚያቋቁሙ እና በገንዘብ የሚደግፉ እስከ አምስት ዓመት እስር እንዲቀጡ ያደርጋል።
የአገሪቱ ሕግ አውጪዎች የእስር ቅጣቱ ወደ ማኅበረሰብ አገልግሎት እና የምክር ድጋፍ እንዲቀየር የተደረገውን ጥረት ተቃውመው ውድቅ አድርገውታል።
በአገሪቱ ሁለት ዋነኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተደገፈው እና ፓርላማው ያጸደቀው ይህ ሕግ ተግባራዊ የሚሆነው የጋናው ፕሬዝዳንት ናና አኩፎ-አዶ በፊርማቸው ሲያጸድቁት ነው።
ፕሬዝዳንቱ ቀደም ሲል አብዛኛው የአገሪቱ ዜጎች የሚፈልጉት ከሆነ ሕጉን እንደሚያጸድቁት ተናግረው ነበር።
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት በጋና ውስጥ ቀደም ብሎም ሕገወጥ ሆኖ በሦስት ዓመት እስር የሚያስቀጣ ነው።
ሕጉ “በሰዎች መሠረታዊ መብት እና ነጻነት ላይ ከባድ አደጋን የሚደቅን ነው” ሲል ባለፈው ወር አምነስቲ ኢንተርናሽናል ተቃውሞውን አሰምቶ ነበር።
የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት መብት ተቆርቋሪዎች አሁን የወጣው ሕግ ሰዎችን እና በዚህ ዙሪያ የሚሠሩ ማኅበራትን ለማሳደድ ስለሚውል አንዳንዶች ለመደበቅ ይገደዳሉ ብለዋል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የኤድስ መከላከያ ተቋም ኃላፊ ዊኒ ባያኒያማ “ይህ ሕግ ተግባራዊ ከሆነ በአገሪቱ ጥላቻ እና ፍርሃትን ያባብሳል፣ በጋናውያን ላይ ጥቃትን ያስከትላል እንዲሁም የነጻነት መብቶችን ይጋፋል” ሲሉ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።
ጨምረውም ሕጉ “ሰዎች ነፍስ አድን የሆኑ አገልግሎቶችን እንዳያገኙ በማደናቀፍ የጋናን የልማት ስኬት አደጋ ላይ ይጥላል” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።
አዲሱ የጋና ሕግ በተለይ ህጻናት ላይ አተኩሮ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነትን ለማስተዋወቅ በሚደረግ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የተሳተፈ ማንኛውም ሰው አስከ አስር ዓመት የሚደርስ እስር የሚቀጣ ነው።
ባለሥልጣናት “አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ” ለማስቻል ሕብረተሰቡ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ማኅበራት አባላትን እንዲጠቁሙ ሕጉ ያበረታታል።
ይህ ሕግ እንዲረቅ ምክንያት የሆነው ከሦስት ዓመት በፊት በጋና ዋና ከተማ አክራ የመጀመሪያው የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት የማኅበረሰብ ማዕከል መከፈቱን ተከትሎ እንደሆነ የፓርላማ አባላቱ ተናግረዋል።
ይህንንም ተከትሎ ብዙኃኑ ክርስቲያን በሆነባት ጋና የሃይማኖት እና ባህላዊ መሪዎች በፈጠሩት ግፊት ሕዝባዊ ተቃውሞ በመቀስቀሱ ፖሊስ ማዕከሉ እንዲዘጋ አድርጓል።
በወቅቱ የጋና የክርስትና እምነት ማኅበራት ባወጡት የጋራ መግለጫ የተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት “ለአገሪቱ ባህል እና የቤተሰብ ዕሴት እንግዳ በመሆኑ የጋና ዜጎች ሊቀበሉት አይችሉም” ሲሉ ተቀውመዋል።
አሁን በፓርላማው እንዲጸድቅ የተደረገው ሕግ ቀደም ሲል በቀረበው ረቂቅ ላይ ማሻሻያ ተደርጎ ቅጣቱ እንዲቀንስ እና ሌሎች እርምጃዎችም ለዘብ እንዲሉ መደረጋቸው ተነግሯል።
በአዲሱ ሕግ የእስር ጊዜው እንዲቀንስ ከመደረጉ በተጨማሪ አወዛጋቢው በተመሳሳይ ፆታ ግንኙነት ውስጥ ያሉ ሰዎችን ለመለወጥ የሚሰጥ ህክምናን በተመለከተ የነበረው አንቀጽ እንዲቀር ተደርጓል።
የተለያዩ አገራት እና ዓለም አቀፍ ተቋማት የጋና ፓርላማ ያጸደቀውን ሕግ በመቃወም አስተያየት እየሰጡ ነው።












