ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ፡ የሳምንቱ ጨዋታዎች ግምት

ሞ ሳላህ እና ሀላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እሑድ ማንቸስተር ሲቲ ወደ አንፊል አቅንቶ ሊቨርፑልን ይገጥማል።

ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገደው ሲቲ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ መሪ ሲያቀና በቻምፒዮንስ ሊጉ 3 ለምንም ከመምራት ተነስቶ አቻ መውጣቱ “እያንገበገበው” እንደሚሆን የቢቢሲው የእግር ኳስ ተንታኝ ክሪስ ሱተን አስታውቋል።

“ታላቅ የነበረው ቡድን አሁን ላይ መካከለኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ቡድን መስሏል” ሲል አክሏል።

ሱተን ይህንን ጨምሮ የቀሪዎቹን የሊጉን 13ኛ ሳምንት ጨዋታዎች እንደሚከተለው ገምቷል።

አርብ

ብራይተን ከ ሳዘውዝሃምፕተን

ሳውዝሃምፕተን ከሊቨርፑል ጋር ጥሩ ሊፎካከር ቢችልም የማታ ማታ ከ12 ጨዋታዎች 10ኛ ሽንፈቱን ቀምሷል።

አሰልጣኝ ረስል ማርቲን ዋጋ ሊያስከፍላቸው ቢችልም አጨዋወታቸውን የሚቀይሩ አይመስልም።

ይህ ጨዋታ ለሳውዝሃምፕተን 11ኛ ሽንፈት ሆኖ ይመዘገባል።

ብራይትን ባለፈው ሳምንት በ10 ተጫዋች በርንመዝን ማሸነፍ የቻሉ ሲሆን በዚህ ጨዋታም ድሉ የእነሱ ይሆናል።

ግምት፡ 2 – 0

ቅዳሜ

ብሬንትፎርድ ከ ሌስተር

እስካሁን ድረስ ሩድ ቫን ኒስተልሮይ የሌስተር አስልጣኝ መሆኑ በይፋ አልተረጋገጠም።

አሰልጣኙ ከዚህ ጨዋታ በፊት ወደ ቡድኑ ባይቀላቀል የተሻለ ይሆናል።

ለዚህ ምክንያት የሚሆነው ደግሞ ብሬንትፎርድ ዘንድሮ በጥሩ አቋም ላይ መገኘቱ ነው።

ግምት፡ 2 – 1

ክሪስታል ፓላስ ከ ኒውካስል

በሊጉ አንድ ጨዋታ ብቻ ማሸነፍ የቻለው እና ባለፈው ሳምንት ከአስቶን ቪላ ጋር አቻ የተለያየው ፓላስ ከወዲሁ ነጥቦችን መሰብሰብ ይኖርበታል።

ይህ ጨዋታ ግን ሦስት ነጥብ የሚያገኙበት አይሆንም። ኒውካስል ባፈው ሳምንት ከደረሰበት ሽንፈት ሊያገግም ይችላል።

ይህንን ጨዋታ ኒውካስል የሚሸንፍ አይመስልም። ይልቁንም በአቻ ውጤት ይጠናቀቃል።

ግምት፡ 1 – 1

ኖቲንግሃም ፎረስት ከ ኢፕስዊች

ኢፕስዊች ባለፈው ሳምንት ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር አቻ ቢለያይም በዚህ ሳምንት ግን ይሸነፋል።

ኢፕስዊች ጥሩ ተጫዋቾችን ከመያዙም በላይ ጥሩ ይጫወታል። አንድሬ ኦናና ባይሆን ዩናይትድን ማሸነፍ ይገባቸው ነበር።

ከሁለት ሽንፈት በኋላ ፎረስት በዚህ ጨዋታ ወደ ድል የሚመለስበት ይሆናል። ክሪስ ዉድ ወደ ቋሚ አሰላለፍ መመለስ ከቻለ ሦስት ነጥቡን ያሳካሉ።

ግምት፡ 2 – 1

ዎልቭስ ከ በርንመዝ

በዎልቭስ የውድድር ዘመኑን በአስቸጋሪ ሁኔታ ቢጀምርም ውጤታማ መሆን ጀምሯል።

ባለፈው ሳምንት ፉልሃምን ማሸነፋቸው ደግመ ማሳያ ነው።

በርንመዝ በብራይተን እና በብሬንትፎርድ ሲሸነፍም ቡድኑ ዕድሎችን መፍጠር ችሏል።

በዚህ ጨዋታ ጎሎች ተቆጥረው ቡድኖቹ አቻ ይለያያሉ።

ግምት፡ 2 – 2

ዌስት ሀም ከአርሰናል

ዌስት ሃም ከ አርሰናል

መጥፎ አጀማመር የነበረው ዌስት ሃም ሰኞ ዕለት ኒውካስልን በማሸነፍ አስፈላጊ ሦስት ነጥቦችን አሳክቷል።

ማርቲን ኦዴጋርድን ከጉዳት መልስ አግኝቶ ተነቃቃውን አርሰናልን ለመግጠም ግን ጥሩ ጊዜ አይደለም።

መድፈኞቹ ያለ አምበላቸው ጥሩ ባይሆኑም እሱ ሲመለስ ግን ልዩነት ፈጣሪ መሆኑን እያስመሰከረ ነው።

ግምት፡ 0 – 1

እሑድ

ቼልሲ ከ አስቶን ቪላ

አስቶን ቪላ ያለፉትን ጥቂት ሳምንታት ውጤታማ መሆን ባይችልም በሻምፒዮንስ ሊጉ ጁቬንቱስን የሚያሸንፍበት ጎል ባለቀ ሰዓት ተሰርዞበታል።

ግብ ጠባቂው ኤሚ ማርቲኔዝ ድንቅ በረኛ ቢሆንም በዚህ ጨዋታ ግን ጎሉን ሳያስደፍር ለመውጣት ይቸገራል።

ይህንን ጨዋታ ቼልሲ በበላይነት ያጠናቅቃል። ኮል ፓልመር እንደተጠበቀው ባልሆነበት ዓመት ኒኮላስ ጃክሰን ጎሎችን እያመረተ ነው።

ግምት፡ 2 – 1

ማንቸስተር ከኤቨርተን

ማንቸስተር ዩናይትድ ከ ኤቨርተን

አዲሱ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪም መምጣቱን ተከትሎ በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ተስፋ ቢኖርም ይህ ተስፋ ወደ ውጤት የሚቀየረው ከሁለት እና ሦስት የዝውውር መስኮቶች በኋላ ነው።

ከኢፕስዊች ጋር የጀመሩበት መንገድ ጥሩ ቢሆንም ትራክተሮቹ የኋላ ኋላ የተሻሉ ከሆኑ ችግር መኖሩን ያሳያል።

ቡድኑ በመጀመሪያው አሰላለፍ ክርስቲያን ኤሪክሰንን እና ካሰሚሮን ይዞ በ 3 – 4 – 3 አሰላለፍ መጫወት እንደሚያስቸግረው ታይቷል።

የሾን ዳይሽ ቡድን ባለፈው ሳምንት በ10 ተጫዋቾች የተጫወተውን ብሬንትፎርድን ማሸነፍ አልቻለም።

ይህ የዩናይትድ ቡድን ወደ የሚፈለገው ደረጃ ለመድረስ ጊዜ ስለሚፈልግ ይህ ጨዋታ ለኤቨርተን ጥሩ አጋጣሚ ነው።

ግምት፡ 1 – 1

ቶተንሃም ከ ፉልሃም

ቶተንሃም ባለፈው ሳምንት ያለ ቁልፍ ተከላካዮቹ ጎል ሳይቆጠርበት ማንቸስተር ሲቲን 4 ለምንም ማሸነፍ ችሏል።

በረኛው ጉግይልሞ ቪካርዮ በመጎዳቱ ፍሬዘር ፎስተር የሚተካው ቢሆንም ቪካሪዮን ያህል በእግሩ መጫወት አይችልም።

ዘንድሮ ከዩናይትድ ጋር ካደረጉት ጨዋታ ውጭ ፉልሃሞች በሁሉም ጨዋታዎች ጎል አስቆጥረዋል።

ፉልሃም በዚህ ቸዋታም ጎል ቢያስቆጥርም የቶተንሃም አጥቂዎች እንደሲቲው ጨዋታ መንቀሳቀስ ከቻሉ ድሉ ባለሜዳዎቹ ይሆናል።

ግምት፡ 3 – 1

ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ

ሊቨርፑል ከ ማንቸስተር ሲቲ

ሊቨርፑል በቻምፒየንስ ሊጉ ሪያል ማድሪድን በማሸነፍ ትልቅ ድል ቢያስመዘግብም ኮኖር ብራድሊ ተጎድቶ ለመውጣት ሲገደድ ኢብራሂማ ኮናቴም መጥፎ አወዳደቅ ገጥሞታል።

ሁለቱ ተጫዋቾች መሰለፍ በዚህ ጨዋታ ግምት ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አለው።

በሌላ በኩል ኧርሊንግ ሃላንድ ባለፈው ሳምንት ጎል ካለማስቆጠሩም በላይ እሱ ጎል ካላገባ ቡድኑ ውጤታማ አይሆንም።

ከሦስት ለምንም 3 ለ 3 የተለያዩበት የፌይኖርዱ የሻምፒዮንስ ሊግ ዓይነት ጨዋታዎች መከሰታቸው አይቀርም።

ፔፕ ጋርዲዮላ ጭንቀት ገብቶታል። ተጫዋቾቹም በራስ መተማመናቸው ወርዷል።

ቡድኑ በየትኛውም አጋጣሚ ጨዋታ ቀይረው ምን ያህል ትልቅ ቡድን እንዳላቸው ማስመስከር የሚችሉ ተጫዋቾችም አሉት።

ኮናቴ እና ብራድሊ ባይሰለፉም ግን ይህ አንፊልድ ላይ የሚሳካ አይመስልም።

ሊቨርፑል አማካዩ ጠንካራ ከመሆኑም በላይ ከማድሪድ ጋር የተጫወተበት ፍጥነት ከሲቲ አሁናዊ አቋም በላይ ይመስላል።

ሊቨርፑል ድንቅ ውድድር ዓመት እና ሰምንት እያሳለፈ ሲሆን ሲቲን አሸንፎ ከአምናው ሻምፒዮን በ11 ነጥቦች ከራቀ ደግሞ የበለጠ ውጤታማ ይሆናል።

ሲቲን ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን እንደ ቶተንሃም ሁሉ ሊዘርሩት ይችላሉ።

ግምት፡ 4 – 1