ደቡብ አፍሪካን ለሦስት አስርት ዓመታት የመራው ኤኤንሲ አብላጫ ድምፅ ሊያጣ እንደሚችል ተገለጸ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የደቡብ አፍሪካ ገዢ ፓርቲ አፍሪካን ናሽናል ኮንግረስ (ኤኤንሲ) ከ30 ዓመታት በኋላ በፓርላማው የነበረውን አብላጫ ድምፅ ሊያጣ መሆኑ ተገለጸ።
ሐሙስ ዕለት የደቡብ አፍሪካ ምርጫ ገሚስ ውጤት ይፋ የሆነ ሲሆን ገዢው ፓርቲ አብላጫ ድምፁን እያጣ እንደሆነ ውጤቶቹ አመላክተዋል።
ከምራጭ ቀጣናዎች 50 በመቶው ድምፅ የተቆጠረ ሲሆን ኤኤንሲ በ42 በመቶ ሲመራ ዲሞክራቲክ አላያንስ (ዲኤ) በ23 በመቶ ይከተላል።
የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝደንት ጃኮብ ዙማ ፓርቲ የሆነው ኤምኬ 11 በመቶ ሲያገኝ፤ ኢኮኖሚክ ፍሪደም ፋይተርስ አሊያም ኢኤፍኤፍ እስካሁን ባለው ቆጠራ 10 በመቶ ድምፅ አግኝተዋል።
የምርጫው አጠቃላይ ውጤት ቅዳሜና እሑድ ሊገለጥ እንደሚችል ተነግሯል።
በርካታ መራጮች ኤኤንሲ በሙስና ተዘፍቋል፣ ወንጀል እንዲሰፋፋ አድርጓል እንዲሁም በሀገሪቱ ላለው ሥራ-አጥነት ተጠያቂ ነው ሲሉ ይወቅሱታል።
ላለፉት 30 ዓመታት ደቡብ አፍሪካን በበላይነት ያስተዳደረው ኤኤንሲ በአውሮፓውያኑ 2019 በተደረገው ምርጫ ያገኘው ድምፅ 57 በመቶ ነበር። ነገር ግን በዘንድሮው ምርጫ ከ42 በመቶ ብዙም ያልዘለለ ድምፅ እንደሚያገኝ ተገምቷል።
ይህ ማለት ኤኤንሲ ከአንድ ፓርቲ አሊያም ተጨማሪ ፓርቲ ጋር ተጣምሮ ቅንጅት በመመሥረት የፓርላማውን አብላጫ ወንበር መያዝ አለበት ማለት ነው።
ዲኤ የተሰኘው ፓርቲ ነፃ ገበያ አራማጅ ሲሆን ኢኤፍኤፍ እና ኤምኬ ደግሞ በመንግሥት ጣልቃ ገብነት እና በብሔራዊነት ያምናሉ። ኤኤንሲ ከማን ጋር ሊጣመር ይችላል የሚለው ጥያቄ ምላሽ የደቡብ አፍሪካን መፃኢ ዕጣ የሚወስን ነው።
ፕሬዝደንት ሲሪል ራማፎሳ ሥልጣን ላይ ይቆያሉ የሚለው ጉዳይ አጠራጣሪ ሲሆን ፓርቲው ከ45 በመቶ በታች ድምፅ ካመጣ ከሊቀ-መንበርነታቸው ይነሱ የሚሉ ጫናዎች እየመጡ ነው።
የመጀመሪያ ዙር ውጤቶች እንደሚያሳዩት ኤኤንሲ ከኤምኬ ፓርቲ ከባድ ትግል የገጠመው ሲሆን በተለይ በኩዋዙሉ ናታል የዙማ ፓርቲ በ43 በመቶ ሲመራ ኤኤንሲ 21 በመቶ ድምፅ አምጥቷል።
ዙማ ባለፈው ታኅሣሥ ኤኤንሲን ትተው የራሳቸውን ኤምኬ የተባለ ፓርቲ ሊያቋቁሙ እንደሆነ ሲናገሩ ብዙዎች ግራ ተጋብተው ነበር።
ኩዋዙሉ ናታል የዙማ ክልል ሲሆን በርካታ መራጭ አለባቸው ከሚባሉ አካባቢዎች ሁለተኛው ነው። ይህ ግዛት የትኛው ፓርቲ አብላጫ ድምፅ ያገኛል የሚለውን የሚወስን ነው።
ምንም እንኳ የቀድሞው ፕሬዝደንት ዙማ ፍርድ ቤት በመዳፈር ተፈርዶባቸው ለፓርላማ እንዳይወዳደሩ ቢታገዱም ኤምኬ ፓርቲ የሚለው ወረቀት ላይ የፓርቲው ሊቀ-መንበር ተብለው ስማቸው ሰፍሯል።
አጠቃላይ ውጤቱ ሲገለጥ ኤምኬ በኩዋዙሉ ናታል አብላጭ ድምፅ የሚያመጣ ከሆነ ኤኤንሲን በግዛቱ የነበረው ተፅዕኖ አበቃ ማለት ነው ይላሉ ተንታኞች።
ኤኤንሲ የምጣኔ ሀብት መናኸሪያ በምትባለው ጉዋቴንግ ግዛትም አብላጫ ድምፅ ሊያጣ እንደሚችል ተሰግቷል። በጉዋቴንግ ኤኤንሲ በ36 በመቶ እየመራ ሲሆን ዲኤ ፓርቲ በ29 ይከተላል።
ረቡዕ ዕለት በነበረው ምርጫ ደቡብ አፍሪካ ፀሐይ እስክትጠልቅ ድረስ በረዥሙ ተሰልፈው ድምፃቸውን ሲሰጡ ታይተዋል።
እንደምርጫ ኮሚሽኑ ከሆነ የመጨረሻው የድምፅ መስጫ ጣቢያ የተዘጋው ረቡዕ ለሊት 9 ሰዓት ነው። በርካታ ሰዎች ወጥተው መምረጣቸው ጥቁሮች ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ መስጠት ተፈቅዶላቸው በነበረ ጊዜ የተካሄደውን የ1994 ምርጫ አስታውሷል።
ኤኤንሲ በፓርቲ በወጣቶች ዘንድ ያለውን ተቀባይነት እያጣ መምጣቱን ብዙዎች ይናገራሉ። በርካቶች ለውጥ እንደሚሹ አስተያየት ሲሰጡ ይሰማል።
ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 70 ፓርቲዎች በምርጫው የተሳተፉ ሲሆን አዳዲስ የፓርላማ አባላት እና የ9 ግዛቶች ሕግ አውጭዎች ይመረጣሉ።
ምንም እንኳ አዳዲሶቹ ፓርቲዎች የኤኤንሲን የበላይነት ቢገዳደሩም ገዢው ፓርቲ ምርጫውን በማሸነፍ ቅንጅት የመመሥረት ሥልጣን ሊያገኝ እንሚችል ተገምቷል።













