የኬንያው ፕሬዝዳንት ወደ አሜሪካ የተጓዙበት ጄት ወጪ የተሸፈነው በወዳጆቻቸው እንደሆኑ ገለጹ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ወደ አሜሪካ በግል ጄት የተጓዙት “የአገሪቷ ወዳጆች” ወጪውን ሸፍነው መሆኑን ተናገሩ።
ለአሜሪካ ጉዟቸው የተከፈለው ገንዘብ ከፍተኛ ነው በሚል በኬንያውያን እየተተቹ ያሉት ፕሬዝዳንቱ፣ በኪራይ ለተጓዙበት የግል ጄት የወጣው 73,000 ዶላር (10 ሚሊዮን የኬንያ ሽልንግ) እንደሆነ ገልጸዋል።
ዊሊያም ሩቶ በአገሪቱ አየር መንገድ በመጓዝ ገንዘብ ለማዳን እየሞከሩ ሳለ “የአገሪቱ ወዳጆች” ወጪውን ለመሸፈን ጥያቄ እንዳቀረቡ ተናግረዋል።
ቦይንግ 737-700 አውሮፕላን 1.5 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያወጣ በመጥቀስ ለቀረበባቸው ትችት “እንደዚያ ዓይነት ገንዘብ በምንም ሁኔታ ላወጣ አልችልም” ብለዋል።
ሐሙስ ዕለት ናይሮቢ ውስጥ በተካሄደ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ላይ መነጋገሪያ በሆነው የአውሮፕላን ጉዟቸው ወጪ ላይ ምላሽ በሰጡበት ጊዜ ከመንግሥት ካዝና እንዲህ ያለውን ወጪ የሚያወጡ “እብድ” እንዳልሆኑ ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ንግግራቸውን ተከትሎ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ “ወዳጆች” በሚል የጠቀሷቸው እነማን ናቸው? የሚል ሌላ ጥያቄ አስነስቷል።
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ ለሦስት ቀናት ወደ አሜሪካ ለይፋዊ ጉብኝት የሄዱት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ፣ በ15 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።
ፕሬዝዳንቱ በአሜሪካ ደማቅ መንግሥታዊ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን፣ ቆይታቸው በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠሩ ኢንቨስትመንቶችን ለኬንያ አስገኝተዋል።
ፕሬዝዳንት ሩቶ ወደ ኬንያ ከተመለሱ በኋላ ወደ አሜሪካ የተጓዙበት የግል የኪራይ ጄት ወጪ በአገሪቱ አየር መንገድ አውሮፕላን ከመጓዝ አንጻር ዋጋው እንደሚያንስ መናገራቸው ሲያስተቻቸው ቆይቷል።
ለጉዟቸው ምን ያህል ገንዘብ እንዳወጡ ወይም በኬንያ አየር መንገድ ቢጓዙ ኖሮ ምን ያህል ሊያወጡ እንደሚችሉ በይፋ ሳይናገሩ ቆይተዋል።
ኋላ ላይ ግን ርካሽ የሚባለው አውሮፕላን 530,000 ዶላር እንደሚያስከፍል በመጥቀስ ለእሳቸው እና ለ30 አብረዋቸው ለተጓዙ ልዑካን ከኬንያ አየር መንገድ ትኬቶች እንዲገዙ ማዘዛቸውን ገልጸዋል።
በንግድ አውሮፕላን ሊጓዙ እንደሆነ የሰሙ ወዳጆቻቸው ይህን ሲሰሙ የኪራይ አውሮፕላን ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያስወጣ መጠየቃቸውን ሩቶ ተናግረዋል።
“እንደ አገር ጥሩ ስም ገንብተናል። ወዳጆችም አፍርተናል። ከ153 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለማውጣት ዝግጁ እንዳልሆንኩ ገለጽኩላቸው። እነሱም 73,000 ዶላር ስጠንና አውሮፕላን እንስጥህ አሉኝ” ብለዋል።
የግብር ከፋዮችን ገንዘብ እንደማያባክኑና ሌሎችም ጠንቃቃ እንዲሆኑ ሲናገሩ ጥንቃቄው ከራሳቸው እንደሚጀምርም አክለዋል።
“ክርክሩ ያብቃ። ተረጋጉ” ቢሉም ክርክሩ ግን አሁንም አላቆመም።
እነዚህ “ጓደኞች” እነማን ናቸው? የሚለው ጥያቄ እያወዛገበ ነው።
“ለፕሬዝዳንቱ ስጦታ የሚሰጡት ‘ወዳጆች’ እነማን ናቸው? ይነገረን” ሲሉ አንድ ኬንያዊ ኤክስ ላይ ጠይቀዋል።
ሙዋንጊ ማይና የተባሉ ግለሰብ ደግሞ “ከውጭ የተሰጠ ሥጦታ ከሆነ ጂኦፖለቲካዊ አንድምታ አለው። ነጻ ምሳ የለም” በማለት ከወዳጆቻቸው የተዋለላቸው ውለታ ምላሽ ይኖረዋል ብለዋል።
በኬንያ መሠረታዊ መገልገያዎች ላይ የተጣለው ግብር ከፍተኛ ሆኖ ለባለሥልጣናት ቅንጡ ኑሮ እየዋለ ነው የሚል ትችት ሲሰነዘር ቆይቷል።
እአአ በ2022 ሩቶ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ከፍተኛ ግብር ነዋሪዎች ላይ መጣሉም ቁጣ አስነስቷል።















