ባይደን ለሩቶ ያደረጉት አቀባበል እና ፈተና የገጠመው የአሜሪካ-አፍሪካ ግንኙነት

ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ጆ ባይደን

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ እና ጆ ባይደን

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ በ15 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

ይህ ጉብኝትም ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለአፍሪካ ጉዳዮች ያላቸውን ቁርጠኛነት ማሳየት የሚችሉት አጋጣሚ ነው።

እንደ ሩሲያ እና ቻይና ያሉ የምዕራቡ ዓለም ተገዳዳሪ አገራት ከአፍሪካ አገራት ጋር ያላቸውን ግንኙነት ከግምት በማስገባት አሜሪካ ከብዙ የአህጉሪቱ አገራት ጋር ያላት ትስስር እየላላ ይመስላል።

በዋይት ሐውስ ለአሜሪካ ቅርብ አጋሮች ብቻ በሚሰጠው ታላቅ የአቀባበል ሥነ ሥርዓትን ሩቶ ይገኛሉ ብሎ በአንድ ወቅት ማሰብ ቀላል አልነበረም።

ለምን ቢባል፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት ከ2007ቱ የኬንያ ምርጫ ጋር በተያያዘ በተነሳው ነውጥ በሰብአዊነት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ምክንያት ከሷቸው ሰለነበረ ነው።

አሁን ግን ክሱ ተቀልብሶ ዊሊያም ሩቶ የአሜሪካ አጋር ሆነዋል።

ዊልያም ሩቶ በ15 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ዊልያም ሩቶ በ15 ዓመታት ውስጥ በአሜሪካ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት በማድረግ የመጀመሪያው አፍሪካዊ መሪ ናቸው።

በኬንያ የአሜሪካ አምባሳደር ሜግ ዋይትማን እንዳሉት፣ የአሜሪካ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ሩቶ እንዲጋበዙ ድጋፍ ሳይሰጥ የቀረው ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር በተያያዘ ምክንያት ሳይሆን ጊዜ የማመቻቸት ጉዳይ ነው።

ቀድሞ እንደ ኢቤይ ያሉ ድርጅቶችን የመሩት ሜግ፣ ኬንያ በቴክኖሎጂው ዘርፍ ያላትን ዕምቅ አቅም የሚደግፉ ናቸው።

“አፍሪካ ውስጥ ተጽዕኖ ለመፍጠር እራት መጋበዝ ያለብን ማንን ነው? ኬንያን ብንወስድ፣ የአሜሪካ የ60 ዓመት አጋር ናት። በምሥራቅ አፍሪካ የተረጋጋ ዴሞክራሲ የሰፈነባት ናት። ስለዚህ ሩቶ ትክክለኛ መሪ ናቸው” ብለዋል።

በዊሊያም ሩቶ አስተዳደር ኬንያ የቀጠናው ዲፕሎማሲ እና የንግድ ማዕከል ሆናለች። አሜሪካ አስቸጋሪ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አጋሯ የሆነችውም ኬንያ ናት።

ሩቶ ከምጣኔ ሀብት ጋር በተያያዘ በኬንያ ትችት በርትቶባቸዋል። ግን ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር በተገናኘ የአፍሪካ ድምጽ ሆነዋል።

ባይደን አምና ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት መካከል በስልክ ያናገሩት መሪ ሩቶ ናቸው።

ኬንያ ወደ ሄይቲ ወታደር ለመላክ ፈቃደና በመሆንም አሜሪካንን አስደስታለች።

የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባዔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ-አፍሪካ ጉባዔ

ባይደን አፍሪካን ለመጎብኘት ቃል ገብተው ስላልተሳካ ነው ሩቶ ወደ አሜሪካ ያቀኑት የሚሉም አሉ።

ባይደን ከሁለት ዓመት በፊት በአፍሪካ-አሜሪካ ጉባዔ ላይ ነው አፍሪካን ለመጎብኘት ቃል የገቡት።

ሆኖም በዩክሬን እና ጋዛ ቀውስ ተይዘዋል።

አፍሪካ እና አሜሪካ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ አዲስ አካሄድ ለመዘርጋት ቃል ተገብቷል።

ሩቶም የዚህ ቃል ማሳያ ናቸው።

አሜሪካ እንደ ኒጀር ባሉ አገራት ፈተና ውስጥ ናት።

ከ1,000 በላይ ወታደሮቿ በኒጀር ከእስላማዊ ታጣቂዎች ጋር ሲዋጉ ቆይተዋል።

አምና መፈንቅለ መንግሥት ሲካሄድ ግን ኒጀር ወደ ሩሲያ እና ኢራን ፊቷን አዙራለች።

የመፈንቅለ መንግሥቱ መሪ አሜሪካ “ክብር እየሰጠችን” አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

አሜሪካ ወታደሮቿን ከኒጀር ለማስወጣት የወሰነችውም ለዚህ ነው።

አሜሪካ ወታደሮቿን ከኒጀር ለማስወጣት ወስናለች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, አሜሪካ ወታደሮቿን ከኒጀር ለማስወጣት ወስናለች

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ከፍተኛ ልዑክ ሞሊ ፊ እንደሚሉት በኒጀር የአሜሪካን ጥቅም ማስጠበቅ ከባድ የሆነበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።

“ኒጀር ወደ ሩሲያ እና ኢራን እየቀረበች መምጣቷ ያሰጋናል። ሊያግባባን የሚችል ነጥብ ላይ ባንደርስም ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታችን ይቀጥላል” ብለዋል።

ኒጀር የቀድሞ ቅኝ ገዢዋ ፈረንሳይ ወታደሮችንም አባራለች።

በኒጀር የተከሰው መፈንቅለ መንግሥት ወደ ሌሎች የሳህል አገራትም ተስፋፍቷል። ሩሲያ በምላሹ የተፈጥሮ ነዳጅ ለማግኘት ከእነዚህ አገራት ጋር ግንኙነቷን እያጠናከረች ነው።

ቻይናም አሜሪካንን በአፍሪካ ተኮር ንግድ ትገዳደራለች።

‘ጋልአፕ’ በወጣው መረጃ፣ አሜሪካ አፍሪካ ላይ ያላትን ተጽዕኖ የመፍጠር አቅም በቻይና እየተነጠቀች ነው።

የክራይሲስ ግሩፕ የአፍሪካ ፕሮግራም ዳይሬክተር ሙሪታ ሙቲጋ “በታሪክ ምዕራባውያን አፍሪካን መፈታት እንዳለባት ችግር አይተዋል። ቻይና፣ ቱርክ እና የአረብ አገራት ግን እንደ ዕድል ነው የሚያይዋት” ይላሉ።

አፍሪካ ከአሜሪካ ውጪ ላሉ አገራት የተሻለ ክፍት እየሆነች የመጣችውም በዚህ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

ባይደን አፍሪካን እንደ አጋር ለመያዝ ጥረት አድርገዋል።

የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት በኬንያ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, የአሜሪካ ቀዳማዊት እመቤት በኬንያ

የሕዝብ ቁጥር በከፍተኛ መጠን እየጨመረባት ያለ እና በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገች አህጉር መሆኗን ከግምት በማስገባት፣ “የወደፊቱ አህጉር” በሚል ከፍተኛ ባለሥልጣናት አፍሪካ ተኮር ጉዞ ሲያደርጉ ነበር።

እንደ ቡድን 20፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም እና የዓለም ባንክ ውስጥ አፍሪካ ያላትን ውክልና ከፍ ለማድረግ ከአሜሪካ ጋር ያላት ግንኙነት ጠቅሟታል።

በተቃራኒው አሜሪካ በጋዛ እና ዩክሬን ጦርነት ላይ ባላት አቋም የአፍሪካን ድጋፍ እምብዛም እያገኘች አይደለም።

በአንጎላ፣ በኮንጎ እና በዛምቢያ የሚያልፈው ‘ሎቢቶ ኮሪደር’ ከአሜሪካ የአፍሪካ ፕሮጀክቶች አንዱ ነው።

ናይጄሪያዊው ፖለቲካል ኢኮኖሚስት ኪንግስሊ ሞግሉ “በሎቢቶ ኮሪደር አሜሪካ አፍሪካውያን የሚረዱትን ቋንቋ ለመናገር እየሞከረች ነው” ይላሉ።

አፍሪካውያንን የሚጠቅም ፕሮጀክት መዘርጋት “እንደ ዴሞክራሲ ስላሉ ጉዳዮች ለማውራት መነሻ ይሆናል” ሲሉ ያስረዳሉ።

በቻታም ሐውስ የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ አሌክስ ቪንስ እንደሚሉት አፍሪካውያን ከምዕራባውያን እየተራራቁ ሳይሆን የተለያዩ አማራጮችን እየወሰዱ ነው።

“አብዛኞቹ የአፍሪካ አገራት ከአሜሪካም፣ ከሩሲያም፣ ከአረብ ኤምሬትስም፣ ከቱርክም የተወሰነ ነገር መውሰድ ይሸሉ” ይላሉ።

ኒጀርን ጨምሮ ሌሎችም የአፍሪካ አገራት አማራጭ እንዳላቸው ማሳያው ሩቶ ናቸው።

ቪንስ እንደሚሉት በአፍሪካ “የዳማ ጨዋታ” እየተከናወነ ነው።

“አፍሪካን ለመቀራመት አዲስ ፉክክር አለ። የዳማ ጨዋታ ነው። አፍሪካ ግን ዝም ብላ አታይም። የመረጠችውን ሰው መውሰዷ ሊያስደንቃቸው ይችላል” ብለዋል።