ማክሮን ከፈረንሳይ ለመገንጠል በምትሻው ኒው ካሌዶኒያ የተሰማሩ ፖሊሶች እንደማይወጡ አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት ኢማኑዔል ማክሮን የሀገራቸው ፖሊስ ኒው ካሌዶኒያ በተሰኘችው ግዛት "አስፈላጊውን ጊዜ ያክል" እንደሚቆይ ገለጡ።
ፕሬዝደንቱ በተቃውሞ እየታመሰች ወዳለችው ደሴት አቅንተዋል።
ማክሮን እንዳሉት ቁጥራቸው 3000 ገደማ የሚሆኑ የፈረንሳይ ፖሊስ አባላት አስፈላጊ ከሆነ በፓሪስ ኦሊምፒክ ጊዜም ቢሆን በደሴቷ ይቆያሉ።
ባለፈው ሳምንት የወጣ የምርጫ ሕግን ተከትሎ በተነሳ ተቃውሞ ሁለት የፖሊስ መኮንኖችን ጨምሮ ስድስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል።
ካናክ የተሰኙት የሀገሪቱ ጥንታዊ ሕዝቦች የፈረንሳይ ዜጋ የሆኑ ነዋሪዎች በምርጫው እንዲሳተፉ መፈቀዱ ትክልል አይደለም ሲሉ ድምፃቸውን በማሰማት ላይ ይገኛሉ።
ኒው ካሌዶኒያ ነፃነቷን ልታውጅ ይገባል በሚሉት ካናክ እና ፓሪስ በተቀመጠው ማዕከላዊው መንግሥት መካከል ለረዥም ጊዜ የቆየ አለመግባባት አለ።
ካናክ ከደሴቷ ጠቅላላ የሕዝብ ቁጥር 40 በመቶው ይሆናሉ።
በአውስትራሊያ እና ፊጂ መካከል የሚገኙት ደሴቶች ከ19ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ የፈረንሳይ ግዛት ሆነው ቆይተዋል። ዘንድሮ የታየው ተቃውሞ ከ1980ዎቹ በኋላ የከፍ መሆኑ ተዘግቧል።
ሐሙስ ዕለት ወደ ኒው ካሌዶኒያ መዲና ኑሜያ የበረሩት ማክሮን ሀገሪቱ "በተቻለ ፍጥነት" ወደ ሰላምን መረጋጋት እንድትመለስ ጥሪ አቅርበዋል።
"ቅድሚያ የምንሰጠው ነገር እሱ ነው" ብለዋል የፈረንሳዩ ፕሬዝደንት።
ከግዛቷ ፖለቲከኞች እና ነጋዴዎች ጋር የተገናኙት ማክሮን በተቃውሞው ሕይወታቸውን ላጡ ሰዎች ቤተሰቦች መፅናናትን ተመኝተዋል።
ከፕሬዝደንቱ ጋር በነበረው ስብሰባ ላይ የተገንጣይ ኃይሎች መሪዎችም የተገኙ ሲሆን ነፃነት ስለማወጅ ጉዳይ ከፈረንሳይ ጋር አዲስ ውይይት ለማድረግ አልመዋል።
ማክሮን የኒው ካሌዶኒያ መፃኢ ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል የሚለው ርዕስ እጅግ አሳሳቢ መሆኑን አምነዋል ስትል የቢቢሲዋ ዘጋቢ ኬቲ ዋትሰን ፅፋለች።
ተቃውሞውን ተከትሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን ማክሮን በሚቀጥሉት ቀናት አዋጁ ሊነሳ እንደሚችል ጠቁመዋል።
ኒው ካሌዶኒያ የሕዝብ ቁጥሯ 300 ሺህ ገደማ ሲሆን 112 ሺህ የሚሆኑ ካናክ የተባሉት ጥንታዊ ሕዝቦች ናቸው።
በአውሮፓውያኑ 1998 በተፈረመው የኑሜያ ስምምነት መሠረት ፈረንሳይ የበለጠ ፖለቲካዊ ነፃነት ለመስጠት እንዲሁም የመምረጥ መብት ያላቸው በወቅቱ ነዋሪዎች የሆኑ ብቻ እንዲሆኑ ለማድረግ ቃል ገብታ ነበር።
ከዚህ ስምምነት በኋላ 40 ሺህ ያክል ፈረንሳዊያን ዜጎች ወደ ኒው ካሌዶኒያ ሄደው መኖር ጀምረዋል።
ባለፈው ሳምንት ፓሪስ የሚገኘው ብሔራዊ ጉባዔ በግዛቷ ለ10 ዓመታት የቆዩ ነዋሪዎች የመምረጥ መብት ሊኖራቸው ይገባል የሚል ረቂቅ ይፋ አድርጓል።
ስምምነቱ ሶስት ሕዝብ ውሳኔዎች እንዲደረጉ ቢፈቅድም ነፃነት ማወጅ የሚለውን ሐሳብ ሶስት ጊዜ ውድቅ ሆኗል።
ሁለት ጊዜ በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ከፈረንሳይ ጋር መቆየት የሚለው ሐሳብ በጥቂት ድምፅ አሸናፊ ሲሆን ታኅሣሥ 2021 የተካሄደውን የመጨረሻው ሕዝበ ውሳኔ ተገንጣይ ኃይሎች በኮቪድ ወቅት መሆን የለበትም ሲሉ ውድቅ አድርገውታል።












