ኢራናውያንን በሐሳብ የከፋፈለው የፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ሕልፈተ ሕይወት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ባለፈው እሁድ በሄሊኮፕተር አደጋ ሕይወታቸው አልፎ ዛሬ ቀብራቸው የሚፈጸመው የኢራን ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራኢሲ ለአገሪቱ ሃይማኖታዊ መሪ ባላቸው ታማኝነት እና ታዛዥነት በሪፐብሊኩ ደጋፊዎች ይወደሳሉ።
እአአ በ1980ዎቹ በፖለቲካ እስረኞች ላይ በተፈጸመው የጅምላ ግድያ ደግሞ በብዙ ኢራናዊያን ዘንድ ይጠላሉ።
ግድያው የተፈጸመው ራኢሲ በፍትሕ እና በፀጥታ ቢሮዎች ውስጥ ለአራት አስርት ዓመታት በሠሩበት ወቅት መሆኑን ልብ ይሏል።
እናም ከአራት አስርት ዓመታት በላይ በቆየው የፀጥታ እና የፍትሕ ሥርዓቶች ውስጥ በመሳተፋቸው፣ የእስላማዊው መንግሥት ተቃዋሚዎችን እና ተቺዎችን በማፈን በብዙ ኢራናውያን ዘንድ ይጠላሉ።
የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ መሥራች አያቶላህ ሩሆላህ ኾሜኒ ናቸው። ራኢሲ የፖለቲካ እስረኞችን በሚመለከት ኮሚቴ ውስጥ አባል ሆነው በኾሜኒ ነበር የተሾሙት።
የኋላ ኋላ ይህ ኮሚቴ “የሞት ኮሚቴ” በመባል ታውቋል። ምክንያቱ ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሞት ፍርድ ውሳኔዎችን በማስተላለፉ ነው።
ከአምስት ሺህ በላይ የፖለቲካ እስረኞች ተገድለዋል። ቤተሰቦቻቸው ግን እንዴት፣ መቼ እና የት እንደተቀበሩ የሚያውቁት ነገር የለም።
“በሞት ኮሚቴው” ፍርድ ቤተሰቦቻቸው በሞት የተቀጡ አንዳንድ ሰዎች ራኢሲ ድንገተኛ ሞት አዝነዋል።
አንድ ቀን በሰብአዊነት ላይ በተፈጸሙ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ፍርድ ቤት ይጠየቃሉ የሚለው ተስፋቸው በመምከኑ ነው ያዘኑት።
አሁን ይህ ፈጽሞ ሊሳካ አይችልም።
የራኢሲ ደጋፊዎች ደግሞ የኢራን መንግሥት መገናኛ ብዙኃን የድሆች እና የተገፉት ፕሬዝዳንት አድርገው መሳላቸውን ይስማሙበታል።
ራኢሲ እአአ በ2021 ለመጀመሪያ ጊዜ ፕሬዝዳንት ሆነው ተሾሙ። በፍጥነትም በርካታ የኢራን ግዛቶችን ጎበኙ። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ርካሽ ቤቶችን ለመገንባት፣ የዋጋ ግሽበትን እና ሙስናን ለመዋጋት ቃል ገቡ።
በሥልጣን ዘመናቸው ተከማችተው የነበሩ የሕግ ጉዳዮችን ውሳኔ ለማሰጠት ሞክረዋል። የአንዳንድ ባለሥልጣናትን ዘመዶችም በሙስና ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል።
የኢራን ምጣኔ ሀብት ግን ከድጡ ወደ ማጡ ሆነ። አክራሪዎች የመናገር ነፃነት ሲገድቡ እና ሴቶች ጥብቅ የሆነ የአለባበስ ሥርዓት እንዲከተሉ ወሰኑ።

የፎቶው ባለመብት, EPA
የ22 ዓመቷ ማህሳ አሚኒ እአአ በ2022 የተላለፈውን ጥብቅ የአለባበስ ሥርዓትን በመጣስ ፀጉሯን ባለመሸፈኗ በመዲናዋ ቴህራን በሥነ ምግባር ፖሊሶች ቁጥጥር ሥር ከዋለች ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
ሕልፈተ ሕይወቷ ከፍተኛ አገር አቀፍ ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር።
ማህሳ አሚኒ በእስር ላይ እያለች ድብደባ እንደተፈፀመባት የዐይን እማኞች ተናግሩ። ባለሥልጣናት ግን ይህንን በማስተባበል “ድንገተኛ የልብ ድካም” ለሞቷ ምክንያት ነው ሲሉ አስተባብለዋል።
ተቃዋሚዎች አብዛኛውን ቁጣቸውን የሰነዘሩት ወደ ሃይማኖታዊው መሪ እንጂ ወደ ፕሬዝዳንት ራኢሲ አልነበረም።
በተቃዋሚዎች እና በተቺዎች ዐይን ፕሬዝዳንቱን በይስሙላ ምርጫ ኃላፊነት እንደተሰጣቸው አሻንጉሊት መቆጠራቸው ነው ቁጣውን ያረገበላቸው።
ራኢሲ የኢራንን ሕዝብ ሕይወት ማሻሻል አልቻሉም ሲሉ ብዙዎች ያምናሉ።
የኢራን መገበያያ ገንዘብ ከአሜሪካ ዶላር አንጻር በከፍተኛ ደረጃ ማሽቆልቆሉ፣ በእስላማዊዋ ሪፐብሊክ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ከፍተኛ የዋጋ ንረት መፈጠሩ እና ቃል የገቡት ርካሽ ቤቶች ግንባታ መና መቅረትን ያነሳሉ።
የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ (አይአርጂሲ) አምስት ቅርንጫፎች አሉት።
የቁድስ ኃይል አንደኛው ነው። ይህ ኃይል በራኢሲ ሥር ስትራቴጂካዊ ፖሊሲውን በመቀጠል በኢራቅ፣ በሊባኖስ፣ በየመን እና በጋዛ ደግሞ እንደ ሐማስ ያሉ የውጭ ቡድኖችን ለመደገፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር ፈሰስ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል።
በርካታ ኢራናውያን ይህ ገንዘብ ሕይወታቸውን ለማሻሻል መዋል ይችል እንደነበር ያምናሉ።
የራኢሲ ሄሊኮፕተር መከስከስ ዜና ሲሰማ ብዙ ደጋፊዎቻቸው ለደኅንነታቸው ሲጸልዩ ነበር። በርካታ ኢራናውያን ደግሞ በሞታቸው የተሰማቸውን ደስታ በማኅበራዊ ድረ-ገጽ ገልጸዋል።
የሚቃወሟቸው ደግሞ ፕሬዝዳንቱ የሕዝቡን የልብ ትርታ ከማዳመጥ ይልቅ ለሃይማኖታዊ መሪው ብቻ ያደሩ ናቸው ብለዋቸዋል።












